ነእፓ ራሱን “ዕጩ መንግሥት” አድርጎ እንደሚቆጥር የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነቢሃ መሐመድ ገለጹ

በመጪው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤቶች ወደ 1,500 የሚጠጉ ዕጩዎችን ያቀረበው የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)፤ ራሱን “ዕጩ መንግሥት” አድርጎ እንደሚቆጥር የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነቢሃ መሐመድ ገለጹ።

ነቢሃ በተለይ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፤ ፓርቲው “ከተፎካካሪነት ወደ መሪነት” በሚል መርህ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ራዕዩን እውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

ጠንካራ ሀገርና መንግሥት መገንባት የፓርቲው ዓላማ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ፤ ይህን እውን ለማድረግ ምርጫ ወሳኝ በመሆኑ ፓርቲው “በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤታማ ለመሆን የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን በተቀናጀ መልኩ እያከናወነ ይገኛል” ሲሉ አክለዋል።

ፓርቲው ለምርጫው ይረዳው ዘንድ የምርጫ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ይፋ ማድረጉንም ነቢሃ ጠቁመዋል። መሰል የምርጫ ስትራቴጂ “ከዚህ ቀደም ተዘጋጅቶ አያውቅም ወይም አልተለመደም” ያሉት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ፤ ሰነዱ አጠቃላይ የፓርቲውን የምርጫ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ትልቅ ፍኖተ ካርታ መሆኑን ገልጸዋል።

የስትራቴጂው ዋና ዓላማ “በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በክልል ምክር ቤቶች በቂ ወንበር ለማሸነፍ የሚያስችለንን ሥራ እንዴት እንደምንሠራ የሚያሳይ ነው” ያሉት ኃላፊዋ፤ ስትራቴጂው በአራት ክፍሎች የተከፈለ መሆኑንም አብራርተዋል።

የስትራቴጂው ዋና ዋና ነጥቦች በምርጫው የሚጠበቁ ውጤቶችን፣ ወቅታዊ ድርጅታዊና ሀገራዊ ሁኔታዎችን፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ቁመና እና አጠቃላይ አስቻይ ሁኔታዎችን የዘረዘሩ መሆናቸውን ነቢሃ ገልጸዋል። በተጨማሪም የነእፓን የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ግቦች እና መልእክቶች፣ እንዲሁም የዕጩዎች ምልመላና ሥልጠና እንዴት እንደሚካሄድ በዝርዝር ማስቀመጡን ጠቁመዋል። ሰነዱ ለምርጫ እንቅስቃሴ የሚሆኑ የሀብት ምንጮችንና የማሰባሰቢያ መንገዶችን ማካተቱንም አክለዋል።

ፓርቲው ይህንን ስትራቴጂ ለማዘጋጀት የተለያዩ ሰነዶችን፣ ሪፖርቶችን፣ ህጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን እንደ ግብዓት መጠቀሙንም አብራርተዋል።

በተጨማሪም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ እንዲሁም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ፤ ፓርቲው የ7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም መላው ኢትዮጵያውያንን ባሳተፈ መልኩ የዳሰሳ ጥናት ማድረጉን ጠቁመዋል።

“ምርጫ ይደረግ አይደረግ ምን ትላላችሁ?” በሚል “ከእኛ ደጋፊዎችና አንባቢያን [የፓርቲውን ማህበራዊ ድህረ ገጾችና ዌብሳይት ተከታዮችና ጎብኚዎች]” ሀሳብ ሰብስበናል ያሉት ነቢሃ፤ ይህም ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ የምርጫ ስትራቴጂውን ለማዘጋጀት እንደጠቀማቸው ገልጸዋል።

የዕጩዎች ምልመላን አስመልክቶ በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት የጸደቀ “የዕጩዎች መመልመያ መመሪያ አዘጋጅተናል” ያሉት ነቢሃ፤ ፓርቲው ከማኒፌስቶ ባሻገር የምርጫ ስነ-ምግባር ደንብ ማርቀቁንም ገልጸዋል። ነእፓ ምርጫውን ለማስፈጸም ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታች ዞን ድረስ “በትይዩ የሚደራጅ ብሔራዊ የምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ” ማቋቋሙንም አክለዋል።

መጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ.ም የተመሰረተው ነእፓ፤ ለዘብተኛ ሊበራሊዝምን እንደ ርዕዮተ-ዓለም እንደሚከተልና ሌሎች ርዕዮተ-ዓለሞችን እንደ አስፈላጊነቱ እንደሚያካትት በተደጋጋሚ አሳውቋል። በመጪው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ፣ ከጋምቤላ ክልል ውጭ በሁሉም ክልሎች ዕጩዎችን እንዳስመዘገበ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ነቢሃ መሐመድ ጨምረው ገልጸዋል።

በቅርቡ የነእፓ ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም በፓርቲው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ባጋሩት መልእክት፤ ፓርቲው ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መስራት እንዳለበት በፕሮግራሙ ውስጥ መካተቱን ገልጸዋል። ይህንን ለማሳካት መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ “ፓርቲዎች ምን ዓይነት ፕሮግራም አላቸው? ከየትኛው ፓርቲ ጋር አብረን መስራት እንችላለን?” የሚሉ ጥናቶችን እያከናወኑ እንደሆነ በማንሳት፤ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ያላቸውን እቅድ አብራርተዋል።

ምርጫ ፓርቲዎች አብረው እንዲሰሩ ምክንያት መሆኑን ያነሱት ዶ/ር አብዱልቃድር፤ በተለይ “በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ ያለው የአብላጫ [ድምጽ ሥርዓት] ድምጽ እንዳይበተን ለማድረግ፤ አንድ ላይ ሆኖ መሥራትን የተሻለ አማራጭ ያደርገዋል” ብለዋል።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንባር ወይም ጥምረት ለመፍጠር ውይይት ማድረግ መጀመራቸውን ያነሱት ሊቀመንበሩ፤ “እኛም በክልልም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተቋቋሙ ፓርቲዎች ጋር እየተነጋገርን ነው ያለነው። ምን ዓይነት ጥምረት ነው መፍጠር ያለብን? የጥምረቱ ይዘት ምን መሆን አለበት? ዓላማውስ ምን መሆን አለበት? በሚሉ ጉዳዮች ላይ የራሳችንን ዝግጅት እያደረግን ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

በዚህ ረገድ ነእፓ ትኩረት የሚሰጠው በጥምረቶች ቀጣይነት ላይ እንደሆነ ዶ/ር አብዱልቃድር አጽንኦት ሰጥተዋል። “ባለፉት 20 ዓመታት ብዙ ጥምረቶች ተፈጥረዋል። ታሪክ እንደሚያሳየው ግን ብዙዎቹ ስኬታማ አልነበሩም፤ ወይም ደግሞ የተቋቋሙበትን ዓላማ በሚገባ ተወጥተዋል ማለት አይቻልም” ሲሉም አክለዋል።

እንደ ዶ/ር አብዱልቃድር ገለጻ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ የሚችሉ ሲሆን፤ በዋናነት “ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማዳከም ሲያደርጋቸው የነበሩ የተለያዩ ሥራዎች” እንዲሁም “ጥምረቶቹ በሚቋቋሙበት አግባብ ላይ” ያሉ ክፍተቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን አብራርተዋል።

“ከአሁን በኋላ እኛ የምንፈጥረው ወይም የምንቀላቀለው ጥምረት ከዚህ ዓይነት ችግሮች ነጻ ሆኖ ምርጫንም በተሳካ ሁኔታ ማሸነፍ የሚችል፣ ከዚያም በድህረ ምርጫ ወቅት የጣምራ [ጥምር] መንግሥት መመስረትም ካስፈለገን ረጅም ጉዞ የሚሄድ ዓይነት ስብስብ እንዲሆን ነው የምናስበው” ሲሉ የፓርቲውን እቅድ አብራርተዋል። [ምርጫ 2018 – በኢትዮጵያ ኢንሳይደር]