እናት ፓርቲ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሊካሄድ በታቀደው 7ኛ ሀገራዊ ምርጫ በትግራይና አማራ ክልሎች በጸጥታ ችግር ምክንያት እጩዎችን ማስመዝገብ አለመቻሉን አስታወቀ። ይሁን እንጂ ፓርቲው “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” በሚል አዲስ የፓርቲዎች ቅንጅት ማዕቀፍ ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በመጪው ምርጫ ተወዳዳሪ ኃይል ለመሆን እንደሚሰራም ገልጿል። የእናት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ጌትነት ወርቁ ፓርቲያቸው ለመጪው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ክልሎች ተወዳዳሪ እጩዎችን ማስመዝገቡን አስታውቀዋል። አቶ ጌትነት ‘ለምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር’ እንዳብራሩት፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ግን ፓርቲያቸው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የዕጩዎች የምዝገባ ጊዜ ሰሌዳ የመጨረሻ ቀነ ገደብ (የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም) ድረስ ተወዳዳሪ እጩዎችን ማስመዝገብ አልፈለገም። በሁለቱ ክልሎች በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ፓርቲያቸው ዕጩዎችን ማስመዝገብ አለመፈለጉን የገለጹት አመራሩ፤ ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደቱ ሁሉን አቀፍ እና ሀገራዊ እንዲሆን፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊ መፍትሄዎችን በማመንጨትና አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር ሂደቱን መደገፍ እንዳለበት አሳስበዋል።

አቶ ጌትነት አክለውም፣ “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ለኢትዮጵያ)” የተሰኘው አደረጃጀትና ቅንጅት በአነስተኛ ቡድኖች መካከል በሚኖር ፉክክር ሳይሆን፣ በቅንጅት የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ኃይሎች እና አማራጭ የፖለቲካ ምህዳርን እንደገና በመቅረጽ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሻለ አማራጭ የሚያቀርብ አዲስ አሰላለፍ መሆኑን አብራርተዋል። ፓርቲያቸው ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቅንጅት ለመፍጠር መወሰኑ ስትራቴጂክ [ስልታዊ] ውሳኔ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌትነት፤ ይህ ውሳኔ የተላለፈው በሀገሪቱ ተለዋዋጭ የዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ለሚታዩ ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ አስረድተዋል። እነዚህ ተግዳሮቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች መከፋፈል፣ የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት እና በዚህም ምክንያት ሊፈጠር የሚችለውን ትርምስ ያካትታሉ። በመሆኑም እናት ፓርቲን ጨምሮ “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት”ን የመሰረቱት ፓርቲዎች ወደዚህ ውሳኔ የደረሱት ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት እና የተረጋጋ የፖለቲካ አማራጭ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል። “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ለኢትዮጵያ)” የተባለው የፓርቲዎች ቅንጅት ባለፈው መስከረም ወር የተመሰረተ ሲሆን፣ ከእናት ፓርቲ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ አባል የሆኑበት ነው።

እንደ አቶ ጌትነት ገለጻ፣ ይህ ቅንጅት ሀገራዊ እና ህዝብ-ተኮር እሴቶችን የሚጋሩ ፓርቲዎችን በማሰባሰብ፣ የአስተዳደር ተግዳሮቶችን በጋራ በመጋፈጥ እና የተበታተነውን የፖለቲካ ኃይል በማዋሃድ ወደ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም በመሰብሰብ የተበታተኑ የፖለቲካ ድርጅቶችን ቁጥር ለመቀነስ ያለመ ነው። በተጨማሪም፣ ቅንጅቱ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እና በምርጫ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመወዳደር እንደሚሰራም አክለው ገልጸዋል። ቅንጅቱ በምርጫ ስሌት የተወሰነ ብቻ ሳይሆን፣ የፖሊሲና የአስተዳደር ጉዳዮችን የሚነካ አንድ ወጥ የሆነ ብሔራዊ የፖለቲካ አማራጭ ለመፍጠር ትኩረት እንደሚሰጥ አመራሩ አብራርተዋል። የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፋንታን አስመልክቶ በብሔራዊ ስሜት ኃላፊነትን የሚጋሩ ፓርቲዎች መዋሃድ እና መቀናጀት ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚረዳም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እናት ፓርቲ “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” በሚል አዲስ አደረጃጀት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመቀናጀት ያቀረበውን ጥያቄ ከማጤኑ በፊት፣ በፓርቲው አመራሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት እንዲፈቱ ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር። በተለይም ከአመራር አባላቱ ስንብት ጋር በተያያዘ ትክክለኛውን ሂደት ያልተከተለ እንደሆነ ከዚህ በፊት ገልጿል። በተጨማሪም ፓርቲው 34 የላዕላይ ምክር ቤት አባላት የነበሩት ቢሆንም፣ “ወደ አዲሱ ጥምረት ለመቀላቀል የወሰነው ምልዓተ-ጉባኤ ሳይሟላ፣ ስንብታቸው በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ስለመሆኑ ሳይረጋገጥ፣ ቦርዱ ያልተቀበለውን የላዕላይ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ፣ ምክትል አፈ-ጉባኤና ሌላ አንድ አባል በመቀነስ የላዕላይ ም/ቤት አባላት 24 ነው በሚል” የቀረበ በመሆኑ፣ ቦርዱ የፓርቲውን ውሳኔ ባለመቀበል የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቆ ነበር። እናት ፓርቲ “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት”ን መልሶ በመቀላቀል ሂደት ላይ አንዳንድ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር በተደረገ ውይይት እነዚህን ችግሮች መፍታት መቻሉን አቶ ጌትነት አስታውቀዋል።

እንደ ከፍተኛ አመራሩ ገለጻ፣ የፓርቲው ጠቅላይ ምክር ቤትን መልሶ በማዋቀር ወቅት ውሳኔዎችን የሚያሳልፈው ከምክር ቤቱ አባላት የሁለት ሦስተኛውን አብላጫ ድምጽ በማግኘት ነው። በዚህ ሂደትም መጀመሪያ በላዕላይ ምክር ቤቱ ውስጥ ከነበሩት 34 አመራሮች፣ በተለያየ ምክንያት የሌሉትን 10 አመራሮች በመቀነስ 24 አመራሮችን በማካተት ውክልና መላኩን አብራርተዋል። ይሁን እንጂ ከላዕላይ ምክር ቤት አባልነት የተቀነሱት 10 አባላት መጀመሪያ ላይ በምርጫ ቦርድ ዘንድ እንደ ላዕላይ አመራሮች ይታወቁ የነበሩ በመሆናቸው፣ ያለቦርዱ እውቅና አመራሮችን መቀነስም ሆነ አዲስ አመራር ማካተት ተገቢ አለመሆኑንና እነዚህ አመራሮች የምክር ቤቱ አካል በመሆናቸው መካተት እንዳለባቸው ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውሰዋል። በዚህም ምክንያት ፓርቲው የውህደት ሂደቱን እንደገና በመገምገም የተቀሩትን አባላት ከቦርዱ የቁጥጥር መስፈርቶች ጋር በሚጣጣም መልኩ በሌሎች አመራሮች መተካቱን አቶ ጌትነት አብራርተዋል።

በምርጫ ቦርድ እና በእናት ፓርቲ መካከል ያለው የአሠራር ግንኙነት እየተሻሻለ በመምጣቱ፣ ቦርዱ ቋሚ ሰው በመመደብ ድጋፍና ክትትል በማድረግ፣ የሁሉንም አጀንዳዎች በትዕግስት ተቀብሎ በማስተባበር፣ እንዲሁም ያልተሟሉ የላዕላይ ምክር ቤት አባላትን እንዲሟሉ ክትትል በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል። አስፈላጊውን የምርጫ ቦርድ መስፈርት ማሟላት በመቻሉም፣ እናት ፓርቲ የካቲት 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትብብሩ መመለሱን አስታውቆ ነበር።

[ምርጫ 2018 – በኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




