የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ አምስት የምርጫ ክልሎች ከትግራይ ክልል ውጭ ሆነው በቀጥታ የፓርላማ ምርጫ እንዲካሄድባቸው በተላለፈው ውሳኔ ላይ ጊዜያዊ የእግድ ውሳኔ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ እግዱን ያስተላለፈው ከዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ የቀረበውን የእግድ አቤቱታ ተከትሎ ነው።
ስምረት ፓርቲ አቤቱታውን ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው በፕሬዝዳንቱ አቶ ጌታቸው ረዳ በኩል ነው። ዛሬ ሐሙስ የካቲት 19፤ 2018 ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ለቀረበው አቤቱታ ተከሳሽ ወይም ተጠሪ የተደረገው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑን አቶ ጌታቸው በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ያጋሩት የፍርድ ቤት ሰነድ አመልክቷል።
ምርጫ ቦርድ በፍርድ ቤት አቤቱታ የቀረበበት፤ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል “አከራካሪ ሆነው” የቆዩ የተባሉ አምስት የምርጫ ክልሎችን በተመለከተ ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው ውሳኔ ነው። እነዚህ የምርጫ ክልሎች ሁመራ፣ አዲ ረመጽ፣ ጠለምት፣ ኮረም ኦፍላ እና ራያ አላማጣ ናቸው።
በአምስቱ የምርጫ ክልሎች የሚደረገው የፓርላማ ምርጫ “በቀጥታ” እንዲሆን እና ለክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች የሚደረገው ምርጫ “አመቺ ጊዜ ተመርጦ ወደፊት እንዲካሄድ” በመጀመሪያ የወሰነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን ቦርዱ በወቅቱ አስታውቆ ነበር። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔውን ያስተላለፈው በአማራ እና በትግራይ ክልል ያለው “የይገባኛል ጥያቄ በሕገ መንግስት ውሳኔ እስከሚፈታ” ድረስ መሆኑም ተገልጿል።
በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ የሚደረገውን ሀገር አቀፍ ምርጫ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት እንደሚያስፈጽም ምርጫ ቦርድ ይፋ ካደረገ በኋላ፤ ስምረት ፓርቲን ጨምሮ የትግራይ ክልል የተለያዩ አካላት ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተዋል። ስምረት ፓርቲ በዕለቱ ባወጣው መግለጫ ውሳኔ “የሀገሪቱን ሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረት የሚንድ”፣ “ተቋማዊ ነጻትን የሚደፈጥጥ” እና “ሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓት አልበኝነትን የሚያውጅ ነው” ሲል አውግዟል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ምርጫ ቦርድ ባስተላለፏቸው ውሳኔዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ካልተወሰደ “በምርጫ እንደማይሳተፍ” ያስጠነቀቀው ስምረት ፓርቲ፤ ከሁለት ቀን በኋላ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል። ጉዳዩን በዛሬው ዕለት የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በስምረት ፓርቲ እና ምርጫ ቦርድ መካከል የሚደረገው ክርክር ታይቶ “ተለዋጭ ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስ” ውሳኔው “ለጊዜው ታግዶ” እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ይህን ትዕዛዝ የሰጠው፤ ምርጫ ቦርድ የሰጠው ውሳኔ የሚፈጸም ከሆነ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገው ክርክር “ውጤት የሚያጣ ስለሆነ” እንደሆነ ገልጿል። በፍርድ ቤት አቤቱታ እና ክስ የቀረበበት ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ፤ እርሱን የሚመለከት ትዕዛዝ በተላለፈበት በዛሬው የችሎት ውሎ ላይ አለመገኘቱን ተቋሙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።
የስምረት ፓርቲ ያቀረበው ክስ እና የማስረጃ ግልባጭ፤ ለምርጫ ቦርድ ደርሶ መልሱን እንዲሰጥ የታዘዘው ለመጪው ረቡዕ የካቲት 26፤ 2018 ነው። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት ያስተላለፈው ትዕዛዝ ለምርጫ ቦርድ እንዲደርስም ተጨማሪ ትዕዛዝ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




