የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ-ኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ሀገርን ለማሻገር መጪው 7ተኛ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች “ወንበር የሚጋሩበት እንጂ” እንደ በፊቱ ብልጽግና ፓርቲ “99 በመቶ አሸነፍኩ” የሚልበት መሆን እንደሌለበት አሳሰቡ።ኢዜማ ትላንት የካቲት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ እስከ እኩለ ለሊት የዘለቀ “ሀገራዊ ወቅታዊ
ሁኔታ እና ምርጫ” በሚል ርዕስ የበይነመረብ ውይይት አካሄዷል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ የውይይት መነሻ አቅራቢ የነበሩት የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ እንዳሉት ምርጫው በ5 ዓመት አንድ ጊዜ የሚደረግ የሐይማኖታዊ በዓል ክንውን ሳይሆን “ካለንበት የፖለቲካ ውጥንቅጥ የምንወጣበት” ብቸኛው መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም “በዚህ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወንበር ተጋርተው የሚሻገሩበት እንጂ እንደድሮው ብልፅግና ፓርቲ 99 በመቶ አሸነፍኩ ብሎ መቀጠል ሀገርን ወደ ሚፈለገው እድገት አያሻግርም” በማለት አሳስበዋል።
ኢዜማ ለህዝብ ክፍት ባደረገው የበይነመረብ (የዙም) ውይይት ከደጋፊዎቹና ከተሳታፊዎች ለተነሱት በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የድርጅቱ መሪና የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።
“የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስቀደም ተቀዳሚ ተግባራችን ነው” ያሉት ፕሮፌሰሩ 50 ዓመታት የመጣንበትን አስከፊ የብሔር ፖለቲካ ልምምድ ለመጣል ምርጫ ወሳኙ መንገዳችን ነው በማለትም ገልፀዋል።
“ፖለቲካ መጋጨት፣ መሳደብና፣ መገፋፋት ነው የሚል አስተሳሰብን ለመቀየር ፖለቲካው በብሔር በሚዘወርበት በዚህ ግዜ ከባለፈው የምርጫ ወቅት እስካሁን ኢዜማ አቋሙን ይዞ ቆይተል” ሲሉም አክለዋል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ፕ/ር ብርሀኑ“ኢዜማን ለማፍረስ ብዙዎች ሞክረዋል፣ ጠንካራ ተቋም ስለሆነ አልቻሉትም” ብለዋል።
ከእስር ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸውም ጥያቄ “በአሁኑ ሰዓት የታሰሩብን አባሎቻችን ባይኖሩም እንኳን የገዢው ፓርቲ የታችኛው መዋቅር ላይ ያሉ አመራሮች በደመ-ነፍስ ያስሩ ነበር” ያሉ ሲሆን ሆኖም ግን “ሆን ተብሎ አባሎቻችን ላይ እስር እምብዛም እስካሁን አይስተዋልም” በማለት አብራርተዋል።
“አሁንም ለወደፊትም የዘር ፖለቲካን ነው የምንቃወመው፣ ውክልና በዘር ከሆነ ማንንም አልወከልንም” ያሉት ፕ/ር ብርሀኑ “ፖለቲካና ዘርን መቀላቀል ውሃና ዘይትን እንደመቀላቀል ነው፣ የዘር ፖለቲካ ኤሊቱን[ለሂቃኑን] እንጂ ማህበረሰቡን ሲጠቅም አይተን አናውቅም” ሲሉም ተደምጠዋል።
መጪው ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወንበር በመጋራት ሀገርን ወደ ተፈለገው እድገት ለመምራት አስተዋጻኦ የሚያረጉበት መሆን እንዳለበትም ፕሮፌሰር ብርሀኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢዜማ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ በአሁኑ ሰዓት ፓርቲው 1100 ዕጩዎችን ማስመዝገብንና በመጪዎቹ ቀሪ የዕጩዎች የምዝገባ ቀናት የዕጩዎቹን ቁጥር ለመጨመር እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ለምርጫው ማካሄጃ የሀብት ማሰባሰብ ስራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመጪዎቹ ቀናት የሚንቀሳቀስ ሲሆን በተጨማሪም መዋቅርን ማጠናከር፣ ፖሊሲና ማኒፌስቶዎችን ማዘጋጀት፣ እንዲሁም ለምርጫ ክርክር ራስን ማዘጋጀት ላይ በንቃት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ዶ/ር ሙሉዓለም ለስብሰባው ተሳታፊዎች ገልጸዋል።
[በ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የቀረበ]




