የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለመወዳደር የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክት ማስተዋወቂያና የዕጩዎች ሥነ ምግባር ደንብ መፈራረሚያ መርሐ ግብርን ዛሬ የካቲት 14 ቀን 2018 ዓ.ም አካሄደ። በመርሐ ግብሩ የመክፈቻ ንግግራቸው የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ እንዳሉት የዕለቱ ትልቅ ሁነት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩባቸውን ምልክቶች ይፋ ማድረግና ለሕዝብ ማስተዋወቅ እንደሆነ ገልጸዋል። የምርጫ ምልክት ይፋ የማድረግያ መርሐ ግብሩ ዋና ዓላማ መራጩ ሕዝብ የሚመርጠውን ለይቶ ማወቅ እንዲችል ከምርጫ ምልክቱ ጀምሮ መረዳትና ማወቅ ስላለበት መሆኑንም ሜላትወርቅ ገልጸዋል። “በተለይም ሚዲያዎች የፓርቲዎችን የምርጫ ምልክት አካታችና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንድታስተዋውቁና እንድታሳዩ ይጠበቅባቹሃል” ሲሉ አሳስበዋል፡፡ በመርሐ ግብሩም ቦርዱ በ7ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የሚካፈሉና እጩዎቻቸውን ያስመዘገቡ 48 የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመወዳደሪያ ምልክትና ስያሜን በቅደም ተከተል በተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም የዕጩዎች ሥነ ምግባር ደንብ መፈራረሚያ መርሐ ግብር ተያይዞ ተካሄዷል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ሜላትወርቅ “የሠለጠነ ምርጫ ለማካሄድ ሥርዓትና ደንብ ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ በምርጫው የሚወዳደሩ ዕጩዎችና ፓርቲዎች የሥነ ምግባር ደንቡን መፈረማቸው አስፈላጊ ነው” ብለዋል፡፡

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ ንዋይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የዕጩዎች ሥነ ምግባር ደንብ ያስተዋውቁ ሲሆን፥ በንግግራቸው እንደጠቀሱትም ሰነዱ የተዘጋጀው በዋናነት በአዋጅ ቁጥር 1162 ከአንቀጽ 127 ጀምሮ በሰፈሩ የሥነ ምግባር ድንጋጌዎች ላይ ተመርኩዞ ነው። እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ ድንጋጌዎቹም ፖለቲካ ፓርቲዎችና ዕጩዎች የምርጫ ውድድርና ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት በምን አግባብ መንቀሳቀስ አለባቸው የሚሉ ዝርዝሮችን የያዙ ሲሆን እንዲሁም ድንጋጌዎቹ ከተጣሱ ተጠያቂነት ሊረጋገጥበት የሚችልበትን አግባብም አካተዋል። ምክትል ሰብሳቢው እነዚህ የሥነ ምግባር ድንጋጌዎች ከፖለቲካ ፓርቲዎችና እጩዎች ባለፈ ደጋፊዎችና አባላትም ሊያከብሩዋቸው እንደሚገባ ታሳቢ በማድረግ የሥነ ምግባር ደንብ ሰነዱ እንደተዘጋጀ ገልጸዋል፡፡

ሰነዱን ሲያዘጋጅ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አንደኛና መሰረታዊ ዓላማ የምርጫ ቅስቀሳና ውድድር ሰላማዊ በሆነ መንገድ መከናወን ያለበት ስለሆነ፥ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ የግል እጩዎች በምን አግባብ የምርጫ ቅስቀሳና ክርክር ማድረግ እንዳለባቸውና፣ በምን አግባብ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ታሳቢ በማድረግ ነው ሲሉ አቶ ተስፋዬ አብራርተዋል። በሁለተኛ ደረጃ በምርጫ ቅስቀሳና ውድድር ወቅት ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እኩልና ፍትሃዊ የሆነ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲያገኙ ሰነዱ አስፈላጊ ነው ሲሉም አቶ ተስፋዬ አክለዋል፡፡

በተጨማሪም አቶ ተስፋዬ እንዳሉት መራጮች ነጻ ሆነው የሚፈልጉትን ፓርቲ የመምረጥ ነጻነታቸውን ማረጋገጥንም የሥነ ምግባር ሰነዱ ዓላማ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ተስፋዬ “ማናቸውም የምርጫ ውድድሮችና እንቅስቃሴዎች የሥነ ምግባር ደንቡን የተከተሉ ከሆኑ ሂደቱም ሆነ ውጤቱ ተዓማኒ እንዲሆን ያደርጋል” ብለዋል፡፡ በኋላም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች በቡድን በቡድን በመሆን የሥነ ምግባር ደንብን ፈርመዋል፡፡ በተያያዘም ከዚህ በፊት ምርጫ ቦርድ በተለይም ለምርጫ አስፈጻሚዎች እንዴት የመራጮች ምዝገባ እንደሚካሄድ ሥልጠና መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጾ ነበረ፡፡ የሥልጠና ሂደቱም በአራት ደረጃ የተከፋፈለ ሲሆን በየደረጃው መሪ አሰልጣንኞችን፣ ዋና አሰልጣኞችን፣ የመስክ አሰልጣኞችንና የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎችን ለመድረስ እቅድ ተይዞ ነበር፡፡

በዕለቱ መድረክ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ እንዳሉት በሥልጠና መርሐ ግብሩ መሰረት ባለፈው ሳምንት ወደ 30 ለሚጠጉ የመሪ አሰልጣኞች የሥልጠና ፕሮግራም ተካሄዷል፡፡ በተጨማሪም በትላንትናው ዕለት የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. የጀመረውንና በዛሬው ዕለት በሚጠናቀቅው የዋና አሰልጣኞች ስልጠናም ወደ 300 የሚጠጉ ሰልጣኞች እንደተካፈሉ ገልጸዋል፡፡ ዋና አሠልጣኞቹ በምን አግባብ የማንዋል እና በቴክኖሎጂ የታገዘው የመራጮች ምዝገባ መከናወን እንዳለበት በዝርዝር የሚሠለጥኑ ሲሆን፥ በየሥልጠና ማዕከላቱ በመሠማራት ከ5,000 በላይ የመሥክ አሠልጣኞችን የሚያሠለጥኑ ይሆናልም ብለዋል። እንደቦርዱ ገለጻ የመሥክ አሠልጣኞችም በተዋረድ ከ214,000 በላይ ለሚሆኑ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ሥልጠናውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

[በ“ምርጫ 2018-ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠናቀረ]




