ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለፓርላማ አባልነት በድጋሚ እንደማይወዳደሩ አስታወቁ 

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) በመወከል በባህር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል ተመርጠው ላለፈው አራት ዓመት ተኩል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቆዩት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ በመጪው ምርጫ እንደማይወዳደሩ አስታወቁ። ዶ/ር ደሳለኝ ራሳቸውን ለምርጫ በዕጩነት ላለማቅረብ የወሰኑት ነጻ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል “ምቹ መደላድል ባለመኖሩ” ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል። 

የፓርላማ አባሉ ይህን የገለጹት፤ የመጪው ምርጫ ተሳትፏቸውን በተመለከተ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው ዛሬ አርብ ጥር 29፤ 2018 ባሰራጩት መግለጫ ነው። ዶ/ር ደሳለኝ ባለፉት ዓመታት የባህር ዳር ከተማ በመወከል፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህዝቡ “ሀቀኛ ድምጽ” በመሆን ማገልገላቸውን በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።

በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ ለሚካሄደው ሰባተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ፤ የተወዳዳሪዎች ምዝገባ እየተከናወነ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በዕጩነት መመዝገብ አለመመዝገባቸውን በተመለከተ “ተደጋጋሚ” ጥያቄዎች ሲቀርብላቸው እንደቆየ ዶ/ር ደሳለኝ በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ይፋዊ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ ጥር 1 የተጀመረው የዕጩዎች ምዝገባ ከነገ በስቲያ እሁድ ይጠናቀቃል።

ዶ/ር ደሳለኝ በመጪው ምርጫ ለመወዳደር በባህር ዳር አሊያም በአዲስ አበባ በዕጩነት እንዲቀርቡ ከ“አንዳንድ ፓርቲዎች” ዕድሉ ተሰጥቷቸው እንደነበር በዛሬው መግለጫቸው ላይ አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ከሚመሩት አመራሮች ጋር ቅራኔ ያላቸው የፓርላማ አባሉ፤ ዕድሉን የሰጧቸውን ፓርቲዎች በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

በፖለቲካ ፓርቲ ውክልና ለምርጫ ከመቅረብ በተጨማሪ በግል የመወዳደርን አማራጭ “በጥልቀት” እንዳሰቡበት የገለጹት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ሆኖም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ካለው “ተጨባጭ ነባራዊ  ሁኔታ” ጋር በተያያዘ ራሳቸውን ለምርጫ በዕጩነት ላለማቅረብ መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል። የፓርላማ አባሉ ለዚህ ውሳኔያቸው በምክንያትነት ያስቀመጡት “ነጻ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ” ለማካሄድ የሚያስችል “ምቹ መደላድል አለመኖሩን” ነው።

በዚህ ሁኔታ “በፖርላማ ውስጥ ተጨማሪ 5 ዓመታትን መቆየቴ ለህዝቤ የሚያበረክተው የረባ ጥቅም የሌለው መሆኑን ተረድቻለሁ” ሲሉ ዶ/ር ደሳለኝ በዛሬው መግለጫቸው ላይ አስረድተዋል። መጪውን ምርጫ በተመለከተ ተመሳሳይ መልዕክት ያዘሉ እና ስጋት የተጫናቸው ጥያቄዎች ባለፈው ማክሰኞ በፓርላማ ቀርበው ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቀርበውላቸው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው የዘንድሮ ምርጫ “ሰላማዊ”፣ “ፍትሐዊ”፣ “አካታች” እና “ከባለፈው ምርጫ በሁሉም መስፈርት የተሻለ እንዲሆን አበክረን እየሰራን ነው” ብለዋል። “አንዳንዶች ሰግታችኋል። ለኢትዮጵያ ህዝብ መልሴ በውጤት እንየው ነው። የእኔ እምነት ይሄ ፓርላማ አሁን ካሉ አምስትና አስር ሰዎች፣ በአምስት እና አስር እጥፍ ያደገ ድምጾች ይሰማሉ ብዬ አምናለሁ፣ እፈልጋለሁ” ሲሉ አብይ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። 

እርሳቸው ይህ ቢሉም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች ንቁ ተሳትፎ በማሳየት እና ሞጋች ጥያቄዎች በማቅረብ የሚታወቁት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ከሁለት ቀናት በኋላ ራሳቸውን ከመጪው ምርጫ ውድድር ውጭ አድርገዋል። ዶ/ር ደሳለኝ “የስድስተኛ ዙር ፓርላማ እስኪጠናቀቅ ድረስ ባሉት ጥቂት ወራት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደራሴነት ስራዬን ቀጥዬ ሰኔ መጨረሻ ላይ የእዚህን ዙር የአገልግሎት ዘመኔን የማጠናቅቅ [ይሆናል]” ሲሉ በዛሬው መግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።

ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን ወደፊት “እንዴት ማገልገል እንደሚፈልጉ” እንደሚያሳውቁ የገለጹት የፓርላማ አባሉ፤ እስካሁን ድረስ በጽናት አብረዋቸው ለቆሙ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በፓርላማ አባልነታቸው ያለመከስስ መብት ያላቸው ዶ/ር ደሳለኝ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ለአንድ ወር ከ12 ቀናት በእስር ቆይተው መፈታታቸው ይታወሳል።

የኢፌዲሪ ህገ መንግስት “ማንኛውም የምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፈንጅ ካልተያዘ በስተቀር፤ ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ እንደማይያዝ እና በወንጀል አይከሰስም” ሲል ይደነግጋል። ዶ/ር ደሳለኝ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የነበረው ያለመከሰስ መብታቸው በፓርላማ ሳይነሳ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]