ብልጽግና ፓርቲ በመጪው ምርጫ የሚጠቀምበትን ምልክት እና ማኒፌስቶውን አስተዋወቀ

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ለመጪው ምርጫ ያዘጋጀው ማኒፌስቶ በዋናነት ትኩረት ያደረገው፤ “በመግባባት፣ በመፍታት፣ በማስፋት እና በመገንባት” ላይ መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ። የምርጫ ማኒፌስቶዉ ዋነኛ እሳቤ “ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር መትጋት” እንደሆነም ገልጸዋል። 

አቶ አደም ይህን የገለጹት፤ የሰባተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ የማኒፌስቶ እና የምርጫ ምልክት ይፋ ባደረገበት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 3፤ 2018 በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ ከፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንቶች አንዱ የሆኑት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተገኝተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ እና ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም የፓርቲው የኢንስፔክሽንና ስነምግባር ኮሚሽን አመራሮች በታደሙበት በዚህ መድረክ፤ ገዢው ፓርቲ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱ “የስንዴ ነዶ” መሆኑን ይፋ አድርጓል። ፓርቲው በባለፈው ምርጫ የተጠቀመበት ምልክት አምፖል እንደነበር ይታወሳል።

በስድስተኛው ዙር ምርጫ ወቅት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን የሚያቀርቡበት እና የሚያስወስኑበት ጊዜ በምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ተካትቶ ነበር። ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ይፋ የተደረገው የዘንድሮው ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ግን ይህ ተግባር አልተካተተም። 

ብልጽግና ፓርቲ የስንዴ ነዶን ለምርጫ መወዳደሪያ ምልክትነት የመረጠው፤ “የመደመር፣ የትብብርና እና የአንድነት ተምሳሌት” በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ነው በዛሬው መድረክ ላይ አስታውቋል። ከብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳትነታቸው በተጨማሪ የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አደም፤ “የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታችን የሆነው የስንዴ ነዶ የመደመር፣ የምርታማነት፣ የተምሳሌትነት፣ የልዕልና፣ የሉዓላዊነት፣ የበረከት እና የብልጽግና ምልክት ነው” ሲሉ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። 

ገዢው ፓርቲ በዛሬው መድረክ፤ የምርጫ ቅስቀሳ ሂደቱን በይፋ መጀመሩን አስታውቋል። በይፋዊው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ የምረጡኝ ቅስቀሳ ወይም የምርጫ ዘመቻ የሚካሄደው ከጥር 1 እስከ ግንቦት 19 ድረስ ባሉት ሶስት ወር ተኩል ገደማ ጊዜያት ውስጥ ነው። 

ፎቶ፦ ብልጽግና ፓርቲ

ሌላው በዛሬው መድረክ ይፋ የተደረገው የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶ ነው። “ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” የሚል ስያሜ የተሰጠው የፓርቲው ማኒፌስቶ፤ “ትናንትን ማከሚያ፣ ዛሬን በሚገባ መጠቀሚያ፣ ነገን  መተለሚያ እና ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ማሻገሪያ መመሪያችን ነው” ብለዋል አቶ አደም።

በፖለቲካ እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረውን የማኒፌስቶውን ክፍል ያቀረቡት አቶ አደም፤ በዚህ ክፍል ውስጥ በአራት “መ”ዎች ላይ የተደራጁ 13 ነጥቦችን መካተታቸውን ገልጸዋል። አራቱ “መ”ዎች “መግባባት”፣ “መፍታት”፣ “ማስፋት እና “መገንባት” መሆናቸውን ተናግረዋል።

የፓርቲው የምርጫ ማኒፌስቶ እሳቤ “ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር መትጋት” መሆኑን አቶ አደም አመልክተዋል። ብልጽግና ፓርቲ በሚቀጥሉት አመታት ሊተገብራቸው ካቀዳቸው ጉዳዮች መካከል “ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር፣ ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታት፣ የሽግግር ፍትህ ሥርዓትን መዘርጋት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት” እንደሚገኙበት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ዘርዝረዋል።

ፎቶ፦ ብልጽግና ፓርቲ

“የኢትዮጵያን የተጠቃሚነት እና የተጽእኖ አድማስ ማስፋት”፣ “ሀገራዊ ስሜትን፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን እና የሥርዓት ለውጥን የሚሻገሩ ተቋማትን መገንባት” ሌላኛዎቹ የፓርቲው መጪ ተግባራት መሆናቸውን አቶ አደም አብራርተዋል። ከፓርቲው ዕቅዶች ውስጥ “ኢትዮጵያ የባህር በር ልታገኝበት የምትችልበትን ሁኔታ መፍጠር እና ማመቻቸት” የሚለው እንደሚገኝበትም አክለዋል። 

በዛሬው መድረክ ላይ ሌላኛው የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተመስገን፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ የማኒፌስቶውን ክፍል ጥቅል ሃሳብ ለታዳሚያን አቅርበዋል። ብልጽግና ፓርቲ “ከትላንት የሚወሰዱ እሴቶችን በአግባቡ በመገንዘብ”፣ “ሊወረሱ የሚችሉትን አምዶች በመለየት”፣ “አዋጭ የሆነውን” ቀጣዩን የኢትዮጵያ ጉዞ መተለሙን አቶ ተመስገን ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)