7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ላይ ጥላ ያጠላው የጸጥታ ጉዳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ቁሳቁሶች ዝግጅት እና የምርጫ አስፈጻሚዎችን ሥልጠና መጠናቀቅን ተከትሎ የ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከቅዳሜ የካቲት 28 ቀን ጀምሮ እንደሚከናወን አስታውቋል። ሆኖም፣ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር የምርጫው ሂደት ላይ ጥላ ያጠላ ጉዳይ ሆኗል። የምርጫ ባለድርሻ አካላት፣ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ አካታችና ፍትሃዊ ምርጫን ለማካሄድም ሆነ ተያያዥ የፖለቲካ እንቅስቃሴን ለማድረግ እክል እንደሆነባቸው ይጠቁማሉ።

የተለያዩ ዘገባዎች በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ጉዳይ አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑንና ምርጫን ለማካሄድ አዳጋች እንደሆነ ይጠቁማሉ። በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል እጅግ ብዙ ያልተፈቱ የጸጥታና ተያያዥ ጥያቄዎች መኖራቸው፣ በክልሉ በተያዘለት ቀነ ገደብ ምርጫ እንደማይካሄድ የሚጠቁሙ ናቸው። በተጨማሪም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች አሁንም በመንግሥትና በታጠቁ ኃይሎች መካከል ግጭቶች መኖራቸው ምርጫው በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች መካሄዱ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል።

ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ እና የቦርዱ ዝግጅት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባሳለፍነው ወር መባቻ ሀገራዊ ምርጫን እና የጸጥታ ጉዳዮችን አስመልክቶ የክልል መንግሥታት ርዕሰ መስተዳደሮች፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች፣ የጸጥታ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሀገር አቀፍ የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች የተሳተፉበትን የምክክር መድረክ አካሂዷል።

ቦርዱ ከክልልና ከተማ መስተዳደሮች እንዲሁም ከጸጥታ አካላት መሬት ላይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን በአረንጓዴ፣ በቢጫ እና በቀይ መድቦ መረጃ እንዲላክለት ማድረጉን ገልጿል። በሀገሪቱ በአጠቃላይ በተለይም በክልሎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ ምርጫን ለማካሄድ አስቻይ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን አስመልክቶም ቦርዱና ባለድርሻ አካላቱ በዝግ ውይይት አከናውነዋል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በቅርቡ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በምርጫ ቦርድ አሰራርና ግምገማ መሰረት በአረንጓዴ የተመደቡት አካባቢዎች “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ” የሚቻልባቸው ናቸው። በቢጫ የተመደቡት “ከጥንቃቄ ጋር ምርጫ ማካሄድ” የሚቻልባቸው ሲሆኑ፤ በቀይ የተመደቡት ደግሞ “ምርጫን ማካሄድ የማይቻልባቸው” እንደሆኑ ገልጸዋል።

ሆኖም የጸጥታውን መረጃም ሆነ የትኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ስር እንደተካተቱ እስከ የምርጫው ቀን ድረስ ተቀያያሪ ሊሆን ስለሚችል ቦርዱ ሙሉ ለሙሉ ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል። ስለዚህ እስከመጨረሻው የምርጫ ቀን ድረስ የጸጥታ ግምገማው የሚቀጥል እንደሆነ ሰብሳቢዋ ጠቅሰዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን አሉ?

አላምረው ይርዳው፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፕሬዚዳንትና የስምንት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው የ“ሰላም ለኢትዮጵያ” የፖለቲካና የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ ናቸው። አላምረው ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት አሁን ባለው የሀገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ብዙ ለምርጫ አስቻይ ያልሆኑ ሁኔታዎች አሉ። “ለምሳሌ አሁን ትግራይ ሙሉ ለሙሉ ምርጫው ይካሄድ ወይም አይካሄድ የተረጋገጠ ነገር የለም። አማራ ክልል በተመሳሳይ አብዛኛው ቦታ ላይ ስጋት አለ” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

አላምረው ከፓርቲያቸው ተሞክሮ ተነስተው በተለይ በአማራ ክልል በሚገኙ አንዳንድ የምርጫ ክልሎች በዝቅተኛው እርከን የሚገኙ የመንግሥት አካላት በምርጫ ልንሸነፍ እንችላለን ብለው በሚያምኑባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ እንዳይሆን እና ስጋት እንዲኖር ይሰራሉ ሲሉ ከሰዋል። አንዳንድ የዞን አስተዳዳሪዎች ቀጥታ በግጭት ውስጥ ባይሳተፉም የግጭት “ሁኔታን የማመቻቸት” ስራ ሲሰሩ ታዝበናል ያሉት አላምረው፣ በዚህም ሂደት “ከተሞች ወድመዋል፤ ንቁ የሆኑ ተሳታፊዎች ተገድለዋል” ብለዋል።

“የታችኛው ኃይል በተለይ ከዞን ጀምሮ ወደ ታች ያለው ሁኔታዎች አላመቸው በሚልበት ጊዜ፣ ወይም ደግሞ የህዝቡ ድጋፍ ለእሱ እንዳልሆነ ሲያረጋግጥ እንዲህ አይነት ሴራዎችን ሲሰራ አይተናል” ያሉት አላምረው፤ “አሁንም ከምርጫው በፊት ያሉ እንቅስቃሴዎች አልጥመው ሲሉ” ወደእንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ሆኖም “መንግስት አቋም ወስዶ ያስተካክለዋል ብለን እናስባለን” ያሉት አላምረው፤ “ህዝባችን ባልመረጠው እንዳይመራ እና ዴሞክራሲያዊ ልምምዱን ለማሳደግ በማሰብ በቻልነው መጠን የጥምረቱ አባል ፓርቲዎች በሚንቀሳቀሱባቸውና ዕጩ ለማቅረብ በቻልንባቸው አካባቢዎች ሁሉ ለመወዳደር ዝግጅታችንን አድርገናል” ሲሉም አክለዋል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ህዝብ ንቅናቄ (አዴህን) ሊቀመንበርና የአማራ ክልል የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተስፋሁን አለምነህ በአማራ ክልል ለሀገር አቀፍ ምርጫው የሚደረገው ዝግጅት እንደ የወረዳዎቹና ከተሞቹ የጸጥታ ሁኔታ ይለያያል ብለዋል። በክልሉ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በሚመለከት የመንግስት ጉዳይ መሆኑንና በቀጣይ የመሻሻል ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከምንጮች ባገኘችው መረጃ በአንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት የምርጫ እንቅስቃሴ ለማካሄድ አስቸጋሪ ሆኗል። ለምሳሌ በምዕራብ ጎንደር ወደ ሚገኘው ቋራ የምርጫ ክልል በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት የተመደቡ ባለሙያዎች ለጊዜው ወደ ቦታው እንዳልሄዱ ምንጮቻችን ነግረውናል። በተጨማሪም ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ መረጃ ሰጪዎች በደብረ ታቦርና ደብረ ማርቆስ አካባቢዎች ያለው የምርጫ እንቅስቃሴ በጸጥታው ምክንያት የተቀዛቀዘ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚንቀሳቀሰው የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ከፍተኛ አመራር የሆኑት መኮነን ጉላሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት ፓርቲያቸው ቡልንን ጨምሮ በሦስት ወረዳዎች ላይ በጸጥታ ችግርና በታጠቁ ኃይሎች ምክንያት የምርጫ እንቅስቃሴ ለማድረግ እክል እንደገጠመው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ፓርቲው በመተከል እና ካማሺ ዞኖች እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፣ 68 ዕጩዎችንም ለክልልና ለፌደራል ምክር ቤቶች ተወዳዳሪ አድርጎ እንዳስመዘገበ ጠቁመዋል።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ክፍለማርያም ሙሉጌታ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በህገ መንግስቱ መሰረት ምርጫን ማካሄድ መንግሥት ለመመስረት ግዴታ ስለሆነ የጸጥታ ጉዳዩን ለመንግስትና ለጸጥታ ኃይሎች በመተው ለምርጫው ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

መንግሥት ሀገር ሰላም መሆኑንና ምርጫን ማካሄድ እንደሚቻል፣ ካልሆነም “በወታደርም” ቢሆን ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ብሎ ባሳወቀው መሰረት ፓርቲው ወደ ምርጫ መግባቱን ገልጸዋል። “መንግስት አስቻይ ሁኔታ አለ ብሏል። በተለያዩ አካባቢዎች አንዳንድ መንገራገጭ ይኖራል፤ ይህ ነው ብሎ መናገሩም ጉንጭ ማልፋት ነው፣ ትርጉም የለውም” ሲሉም አክለዋል። ሆኖም አጠቃላይ ሁኔታውን ለመገምገም ከ52,700 በላይ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የሚካሄደው የመራጮች ምዝገባ ትልቁን ሥዕል ሊሰጥ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ክፍለማርያም ገልጸዋል።

የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አማኑኤል ሞጊሶ በበኩላቸው እንደገለጹት ሀገሪቱ ምርጫን ለማካሄድ በምትዘጋጅበት ጊዜ ግጭቶች ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል። “ጦርነትና ምርጫ በታሪክ ተፃራሪ ጉዳዮች ናቸው” ሲሉም አክለዋል።

“ዜጎች በፍርሃትና ቀውስ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ የሞራል ኤጀንሲያቸውን ያጣሉ። የመጀመሪያው የሰው ጥያቄ የሚሆነው የሰርቫይቫል [ህልውና] ጉዳይ ነው። ዴሞክራሲንና ነፃነትን እንደ ሁለተኛ ጉዳይ የሚያዩ ይሆናል” ሲሉም ያብራራሉ።

በተጨማሪም አማኑኤል የጸጥታውን ሁኔታ፣ እንዲሁም ምርጫ ማካሄድ የሚቻልባቸውና የማይቻልባቸውን አካባቢዎች በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ተደርጎ በጂኦግራፊ የተከፋፈለበትን ሁኔታም ተችተዋል። በምርጫ ሂደት የጸጥታ ሁኔታ “በጂኦግራፊ አይከፋፈልም፣ ሀገር ማለት እንደ አንድ ኦርጋኒዝም ነው” ያሉት አማኑኤል፤ “አንዱ ጋር ያለው ክፍተት ሌላው ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም” ሲሉ አክለዋል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በፓርላማ ቀርበው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫንና ጸጥታን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ 88 ሺህ መረጃ ሰብሳቢዎች በ19,650 ቀበሌዎች ጸጥታን በተመለከተ መረጃ ሲሰበስቡ እንደነበር ገልጸዋል። በዚህም መሰረት የጸጥታ አካላቱ መረጃ እንዳሳየው ከ19 ሺህ በላይ በሚሆኑ ቀበሌዎች አሁን ላይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከነበረው የተሻለ እንደሆነ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የምርጫ ቦርድ የጸጥታ ሁኔታን በተመለከተ ያለው መረጃ ተለዋዋጭ በመሆኑ ምክንያት ሙሉ ዝርዝሩን ይፋ ባያደርግም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ምርጫ የመካሄዱ ጉዳይ ግን የጥያቄ ምልክት ውስጥ የገባ ጉዳይ ነው። የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እንደጠቆሙት የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ የጸጥታ ሁኔታውን አስመልክቶ የበለጠ ግልጽ እይታ ሊሰጥ ይችላል።

በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በጸጥታ ምክንያት ውክልና ያላገኙ የምርጫ ክልሎች

በሰኔ ወር 2013፣ ቀጥሎም መስከረም 2014 ዓ.ም በተካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በፌደራል ደረጃ ካሉት 547 የምርጫ ክልሎች መካከል ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በትግራይ 38 (በሁሉም ምርጫ ክልሎች )፣ በአማራ 19፣ በኦሮሚያ 8፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 6 እንዲሁም በአፋር 2 የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ አልተካሄደም ነበር።

ምንም እንኳን በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአፋር ክልሎች በሚገኙት የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ የተካሄደ ቢሆንም በትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ በድምሩ 65 የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ ሳይካሄድ ቀርቷል።

በሀገሪቱ ካሉት አጠቃላይ 684 የክልልና የከተማ የምርጫ ክልሎች መካከል 92 የምርጫ ክልሎች ላይም በተመሳሳይ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ አልተካሄደም። ሰኔ 16 2016 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በ15፣ በአፋር 9 እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያና ሶማሌ ክልሎች በሚገኙ ሁለት የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ ተካሄዷል። በዚህም መሰረት በአጠቃላይ በ66 የክልል እና የከተማ የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ ሳይካሄድ ቀርቷል።

ይህም በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በፌደራልና በክልል ምክር ቤቶች በሚተላለፉ ውሳኔዎች ድምጻቸውን እንዳያሰሙና እንዳይወከሉ አድርጓል። በአሁኑ ሰዓትም እየተከሰቱ ያሉ የጸጥታ ችግሮች በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ተመሳሳይ ክፍተት እንዳይፈጥሩ ስጋትን ጭሯል። [ምርጫ 2018 – በኢትዮጵያ ኢንሳይደር]