በሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የግል ተወዳዳሪ ዕጩዎች ቁጥር ከስድስተኛው ምርጫ አንፃር በግማሽ ቀነሰ
የምርጫ ተሳታፊ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች ቁጥር በከፊል ሲቀንስ፣ የጠቅላላ ዕጩዎች ብዛት ግን ጭማሪ ማሳየቱን የስድስተኛው እና ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫዎች ንፅፅር አመላከተ። በዘንድሮው ምርጫ 47 ፓርቲዎች ዕጩዎችን ለክልሎች ምክር ቤቶች እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያስመዘገቡ፣ በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ 50 ፓርቲዎች መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል። በተመሳሳይ በምርጫ 2013 የግል ተወዳዳሪዎች ቁጥር 183 የነበረ ሲሆን፣ ዘንድሮ በ110 በመቀነስ 73 ብቻ የግል ዕጩዎች መቅረባቸው ተነግሯል።
በሌላ በኩል የጠቅላላ ዕጩዎች ቁጥር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቶ ያህል፣ ለክልሎች ምክር ቤቶች ደግሞ አንድ ሺሕ ያህል የሚበልጡ ዕጩዎች በመመዝገባቸው የዘንድሮው ምርጫ ከስድስተኛው ምርጫ አንፃር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተወዳዳሪዎች ያሉበት ሆኗል። የሴት ዕጩዎችም ቁጥር ከስድስተኛው ምርጫ አንፃር 704 ብልጫ በማሳየት፣ በሰባተኛው ምርጫ 2,760 ሴት ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልሎች ምክር ቤቶች ተወዳዳሪ ሆነው ቀርበዋል።




