“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ትላንት ሐሙስ፣ መጋቢት 16፤ “ገዢው ፓርቲ የኢዜማ መሪና ምክትላቸው ለፓርላማ በሚወዳደሩባቸው የምርጫ ክልሎች ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ሳያቀርብ ቀረ” በሚል ርዕስ ለንባብ ላበቃው ዜና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ያቀረበው ቅሬታ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
መጋቢት 16 ቀን 2018 ዓ.ም
ለኢትዮጵያን ኢንሳይደር
ጉዳዩ – በተሳሳተና የጋዜጠኝነት ስነምግባርን ባልተከተለ መልኩ አንባቢያን የተሳሳተ ግምት እንዲወስዱ በሚያደርግ መልኩ የወጣ ዘገባ እንዲታረም ስለመጠየቅ
ሚዲያው በመጋቢት 16፣ 2018 ባወጣው ዘገባ የኢዜማ መሪና ምክትል መሪ በሚወዳደሩባቸው ቦታዎች ብልፅግና እንደማይወዳደር በመግለፅ በሠራው ዘገባ ላይ ሚዲያው በፓርቲው ላይ የያዘውን የተዛባ አቋም በግልፅ የሚያሳይ እና ከአንድ ለእውነት እቆማለሁ ብሎ ከተነሳ ሚዲያ የማይጠበቅ እንዲሁም የጋዜጠኝነትን ስነምግባር ያልተከተለ ዘገባ ከፍተኛ ቅሬታ ተሰምቶናል።
አንድ ሚዲያ ስለአንድ ጉዳይ ሲዘግብ ማረጋገጥ ከሚጠበቅበት መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱ ሙሉ መረጃ መያዝ እና ሙሉ መረጃ ለተከታዮቹ ማጋራት ጥቂቱ ነው። ነገር ግን በዚህ ዘገባ ሙሉ እና እውነተኛ መረጃ ካለመሰጠቱም በላይ ቁንፅል መረጃን በመያዝ አንባቢዎች የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ ሆነ ተብሎ ተሰርቷል ብለን እናምናለን። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው፣
- በተጠቀሱት የምርጫ ክልሎች ሌሎች በርካታ ፓርቲዎች ተወዳዳሪ ዕጩዎችን አቅርበው እያለ እና ገዢው ፓርቲ ባይኖርም ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ውድድር እንደሚኖር እየታወቀ ለኢዜማ ተብሎ የተለቀቀ ለማስመሰል የተኬደበት ርቀት በጣም አሳዛኝ ነው። ለዚህም በስልክ የተሰጠን ምላሽ ሌሎች እንደሚወዳደሩ መረጃው ስላልነበረን ነው የሚል ሲሆን ሚዲያው ሙሉ መረጃ ባልያዘበት ሁኔታ ዘገባውን ሆን ብሎ የዘገባ አንግሉን በማሳሳት ፓርቲያችንን ለማጥቃት መጠቀሙ አሳፋሪ ነው።
- ከነዚህ የምርጫ ክልሎች በተጨማሪ ብልፅግና የማይወዳደርባቸው የክልል ምክር ቤቶችን ጨምሮ 513 ወንበሮች እያሉ ከነዚህ 513 ወንበሮች ውስጥም ኢዜማ በበርካታዎቹ ላይ ለውድድር ዕጩዎችን አላቀረበም ሚዲያው ግን መርጦ ኢዜማ ላይ ትኩረት ያደረገ ጎዶሎ መረጃ ላይ በመመስረት ይሄንን ብቻ መዘገቡም አላማውን ግልፅ ያደርገዋል።
ከዚህ በፊት ሚዲያው ይህንኑ ዘገባ የፓርቲያችን መሪ መረጃ እንደሰጡት አድርጎ በማቅረብ ሀሰተኛ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን እንዲታረም በማድረግ እንዲስተካከል አድርገን ነበር። ነገር ግን ከዚህ አይነት የጋዜጠኝነት ስነምግባርን ያልተከተለ አዘጋገብ እንዲታቀብ ስንጠብቅ በተመሳሳይ ያንኑ ከዚህ በፊት የሰራውንና ያስተካከልነውን መረጃ በሌላ አይነት ዘገባ መስራቱ ከልብ አሳዝኖናል። ሌሎች በተለይ የመንግስት ሚዲያዎች የሚዲያ ስነምግባርን እንዲጠብቁ እና የመረጃ ነፃነት እንዲከበር እሰራለሁ የሚል ሚዲያም በራሱ ይህንን ሙያዊ ስነምግባር የጎደለውን ስራ መስራቱ ሀዘናችንን ድርብ ያደርገዋል።
በዚሁ መሰረት ይህ በተሳሳተና ህዝብን በሚያሳስት መልኩ የቀረበ ዘገባ እንዲታረም እና የሀገሪቱ ህግ በሚያዘው መሰረት ይህንን የማስተካከያ ዘገባ በተመሳሳይ ገፅ ላይ እንድታወጡልን እንጠይቃለን።
—-
የዝግጅት ክፍሉ ማብራሪያ
“የምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዝግጅት ክፍል እውነታውን የሚያንፀባርቁ፣ ሥነ ምግባራቸውን የጠበቁ እና ከአድልዖ የነፁ ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚተጋ ተቋም ነው። በዘገባ ሒደቶች ውስጥ በተቻለ ጥረት የሁሉም አካላት ሐሳቦች እና መረጃዎች ለአንባቢዎቻችን እንዲደርሱ እናደርጋለን። ይሁንና የዘገባዎቻችንን የትኩረት አቅጣጫ (angle) የመምረጥ እና ለብዙኃን አንባቢዎች ይጠቅማል የምንለውን ዜና የማቅረብ ሙሉ የኤዲቶሪያል (የዝግጅት) ነጻነት እንዳለን ለማስታወስ እንወዳለን።




