“የሶማሊላንዱ የባሕር በር ስምምነት ነገሮችን አበላሽቶ ኢትዮጵያ እንዳትታመን አድርጓል” – ዶ/ር አብዱልቃድር አደም

ከ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር አንድ ለአንድ ቆይታ ያደረጉት የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የባሕር በር ስምምነት “ነገሮችን ያበላሸ ነው” ብለዋል። በሥልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅቡልነት ካላቸው አገራት ጋር መደራደር ሲገባው፣ ገና የአገርነት ዕጣ ፈንታዋ ካልተረጋገጠው ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት ውስጥ መግባቱ ጎረቤት አገራት ኢትዮጵያን በጥርጣሬ እንዲመለከቱ አድርጓል ሲሉ ዶ/ር አብዱልቃድር የፓርቲያቸውን ግምገማ ገልጸዋል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ስምምነት ሲፈራረም ፓርቲያቸው ተቃውሞ እንደነበረው ያስታወሱት ሊቀመንበሩ፤ “የባሕር በር ፍላጎቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ መንግሥት የተከተለው አካሄድ ጎረቤት አገራትን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ያስከፋ በመሆኑ፣ አንድም የባሕር በር ሳናገኝ ቀርተናል” በማለት የመንግሥትን አካሄድ ተችተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ የሆነ ስትራቴጂ ቢከተል ኖሮ ብዙ ዕድሎች እንደነበሩ የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ የሶማሊላንዱ ስምምነት አንካራ ላይ ሲፈርስ ሶማሊያ ‘የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ አጤነዋለሁ’ እስከማለት ደርሳ እንደነበር ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም ጅቡቲ የታጁራን ወደብ ኢትዮጵያ እንድትጠቀም ፈቅዳ እንደነበርም አውስተዋል።

ነእፓ ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው የምርጫ 2018 ማኒፌስቶው ላይ እንደጠቀሰው፣ ፓርቲው ምርጫውን የሚያሸንፍ ከሆነ ኢትዮጵያ አምስት የባሕር በሮች እንዲኖራት ከጎረቤት አገራት ጋር በቅርበት እንደሚሠራ አሳውቋል። እነዚህም ጎረቤት አገራት ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያ እንደሆኑ አመልክቷል። ይህንንም ለማሳካት ከሁሉም የጎረቤት አገራት ጋር በ“ሰጥቶ መቀበል” መርህ እንደሚሠራ የጠቀሰው ነእፓ፤ አገራቱ ከኢትዮጵያ የሚፈልጉትን እንደ ውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እንደሚመልስ ቃል ገብቷል።

አሁን ኢትዮጵያ የጅቡቲን ወደብ በምቹ ሁኔታ እየተጠቀመች እንዳልሆነ የጠቀሱት ዶ/ር አብዱልቃድር፣ ሰላማዊ ትብብር ቢኖር፣ አሰብና ምፅዋንም ጨምሮ መጠቀም ይቻል እንደነበር ተናግረዋል። ሆኖም “ለእያንዳንዱ ጥፋት የኢትዮጵያን መንግሥትን ብቻ ተጠያቂ አናደርግም፤ ምክንያቱም በዚያኛው ወገን ያለው አካልም ለመተባበር በሩን መክፈት አለበት” ብለዋል።

ሌላው “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለነእፓ ሊቀመንበር ያነሳችላቸው ጥያቄ በፓርቲው ማኒፌስቶ የተገለጸው በዓመት 500 ሺሕ ቤቶችን የመገንባት ጉዳይ ነው። “ይህንን የተለጠጠ ዕቅድ እንዴት ማከናወን ትችላላችሁ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ዶ/ር አብዱልቃድር “ይህንን የምናሳካው የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ነው” ብለዋል። “ይህ ቁጥር የተጋነነ አይደለም” የሚሉት ሊቀመንበሩ፣ ለ150 ሚሊዮን ሕዝብ በዓመት 500 ሺሕ ቤት ማቅረብ እንደ ትንሽ ግብ ሊወሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከእምነት ጋር ተያይዞ በነእፓ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ሊቀመንበሩ “ጥያቄው መሠረተ ቢስና ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲሉ አጣጥለውታል። ፓርቲው እምነትን መሠረት አድርጎ እንደማይንቀሳቀስ የገለጹት ዶ/ር አብዱልቃድር፤ “ምንም እንኳን በፓርቲው የአመራርነት ቦታ ሙስሊሞች ብንበዛም፣ የአባሎቻችንን ቁጥር ስናይ ግን ከሁሉም እምነቶች የተወጣጡ ናቸው” የሚል መልስ ሰጥተዋል። አክለውም፣ እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ በተማረው አካል ወይም በ“ኤሊቱ” ዘንድ ደጋግሞ መነሳቱ እንደሚያሳዝናቸው ገልጸው፣ ፓርቲው የሙስሊሞች ነው የሚባለውን ወሬ ሐሰት መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል።

ዶ/ር አብዱልቃድር ፓርቲያቸው “የኢትዮጵያን ዐውድ ያገናዘበ ሚዛናዊ ሊብራል ዴሞክራሲ” ለምን እንደመረጠ ሲያስረዱ “አንደኛ የመንግሥትንና የግል ዘርፉን ተሳትፎ የሚመጥን በመሆኑ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የአውሮፓውያንን ርዕዮተ ዓለም ሙሉ በሙሉ የሚተገብር ሳይሆን የኢትዮጵያን ባሕል መሠረት ያደረገ ስለሆነ ነው” ብለዋል። ነእፓ ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ በድምሩ 844 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በዕጩዎች ብዛት በአገር ዐቀፍ ደረጃ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ፓርቲ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ 200 ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ እንዲሁም 644ቱን ለክልል ምክር ቤቶች ማቅረቡን አስታውቋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]