“ያስቀመጥኳቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ በምርጫው መወዳደር ከአጃቢነት የዘለለ ትርጉም አይሰጠኝም” – ኢሕአፓ

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እንዲፈጸሙ የጠየቀው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ መንግሥት እነዚህን ጥያቄዎች ካልመለሰ በምርጫው መሳተፉ “ከአጃቢነት የዘለለ ትርጉም የለውም” ብሎ እንደሚያምን አስታውቋል። ፓርቲው ከምርጫው በፊት እንዲፈጸሙ ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል “ግጭቶች ቆመው እውነተኛ ድርድር መደረግ” እንዳለበት እና “የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ” የሚሉት በዋናነት ተጠቅሰዋል።

ከ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢሕአፓ ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ኃይማኖት እና የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ምሥጢረሥላሴ ታምራት፤ ስለ ምርጫ ዝግጅታቸውና ቀጣይ ዕቅዳቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል። “በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” በተሰኘው ቅንጅት ሥር ሆኖ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደረው ኢሕአፓ፣ በተደጋጋሚ የጠየቃቸው ጥያቄዎች እስካሁን ባለመመለሳቸው ሂደቱ ፈታኝ እንደሆነበት ገልጿል።

ፓርቲው ስድስት ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ እነሱም፦ ግጭቶች ቆመው እውነተኛ ድርድር ማድረግ፣ እንደ አቶ ክርስቲያን ታደለና አቶ ዮሃንስ ቧያለው ያሉ የፖለቲካ እስረኞች እንዲሁም ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፣ በምርጫው ላይ ዓለም አቀፍ ታዛቢ እንዲኖር፣ የድጋፍ ሰልፎችን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ እንዲሁም የሚዲያ ነፃነትንና የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች እንዲሠሩ የሚሉ ናቸው።

በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶች በምርጫ ዝግጅቱ ላይ እንቅፋት እንደፈጠሩበት የገለጸው ኢሕአፓ፣ በአፋር ክልልና በመተከል አካባቢዎች በአባላቱ ላይ እስርና እንግልት መድረሱን ጠቅሷል። ፓርቲው ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ለመወዳደር እንደሚቸገር ማሳወቁ ይታወሳል።

የፓርቲው ዋና ጸሐፊ ምሥጢረሥላሴ ታምራት፤ “የትጥቅ ትግል ከሚያደርጉ አካላት ጋር የትግል መሥመራችን ቢለያይም፣ ወደ ትጥቅ የገቡበት ምክንያት ግን አሳማኝ ነው” ብለዋል። “የአማራ ክልል ሕዝብ የህልውና አደጋ ላይ መሆኑን እናምናለን” ያሉት ዋና ጸሐፊዋ፤ መንግሥት እነዚህ አካላት ለምን የትጥቅ ትግልን መረጡ ብሎ ማሰብ እንጂ “ለምን ታገሉኝ” ሊል አይገባም በማለት ለጥያቄዎቻቸው ዕውቅና ሰጥተዋል። መንግሥት ሁሉንም አካላት ያሳተፈ ድርድር ካላደረገ የምርጫ ቅስቀሳቸው ላይቀጥል እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥተዋል። ተቀዳሚ ፕሬዝዳንቱም መንግሥት ከሕወሃት ጋር በፕሪቶሪያ እንዳደረገው ዓይነት ድርድር በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል “ኢሕአፓ ከተለያዩ ፓርቲዎች ቅሬታ ተሰምቷቸው የመጡ ሰዎች መሰባሰቢያ እየሆነ ነው” ለሚለው አስተያየት አመራሮቹ ሲመልሱ፣ ኢሕአፓ በበርዕዮተ ዓለሙና በሐሳቡ የተገዙ ሰዎች ያስቀጠሉት አንጋፋ ፓርቲ እንጂ የ“አኩራፊ ፖለቲከኞች” መሰባሰቢያ አለመሆኑን ገልጸዋል። ይልቁንም በኢሕአዴግም ሆነ በብልፅግና መንግሥት ውስጥ ሥልጣን የያዙ የነበሩ እንደ አቶ በረከት ስምዖንና የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴን በመጥቀስ ጉምቱ ፖለቲከኞችን ያፈራ ድርጅት ነው በማለት ተናግረዋል።

ኢሕአፓ የ50 ዓመት ታሪክ ያለው ድርጅት ቢሆንም፣ በስሙ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች አመራሮቹ ሲመልሱ፤ ፓርቲው በጽናት የቆመና ከዘመኑ ጋር ራሱን እያጣጣመ የመጣ መሆኑን ተሟግተዋል። ፓርቲው በ1972 ዓ.ም በቋረ ጉባኤው ወቅት ራሱን ከ“ሶሻሊስት” ርዕዮተ ዓለም ወደ “ሶሺያል ዴሞክራት” መቀየሩን መጋቢ ብሉይ አብርሃም አስታውሰዋል።

ኢሕአፓን በውስጡ የያዘው “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” መጋቢት 19 ቀን 2018 ዓ.ም ማኒፌስቶውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ትብብሩ በብሔር ላይ የተመሠረተውን ፌዴራሊዝም በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለመተካት ማቀዱን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ፤ የኢሕአፓ ዋና ጸሐፊ ምሥጢረሥላሴ “የብሔር ፖለቲካ ዜጎችን ከጭቆና አያስጥልም፤ ይህንን ጥያቄ መመለስ የሚቻለው ፍትህን በማስፈንና ሰው በማንነቱ የማይገደልበትን ሥርዓት በመፍጠር ነው” ብለዋል። መጋቢ ብሉይ አብርሃም በበኩላቸው አሁን ያለው ሕገ መንግሥት “ለመሬቱም ጭምር ብሔር የሰጠና እርስ በእርስ የሚያጋድል” መሆኑን ገልጸው፤ የትብብሩ ማኒፌስቶ በክልሎች ፋንታ የአሜሪካን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ መልክዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን መሠረት ያደረጉ “ክፍለ አገራት” እንደሚፈጠሩ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የቋንቋ ፖሊሲን በተመለከተ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ አልባ ሆና መቆየቷ “አገሪቱን አዋርዷታል” ያሉት መጋቢ ብሉይ፣  ትብብሩ አማርኛን ብሔራዊ ቋንቋ እንደሚያደርግና የሥራ ቋንቋ ደግሞ በሕዝብ እንደሚወሰን ተናግረዋል። እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊው “ሕዝቦች” የሚለው አጠቃቀም በአንድ አገር ውስጥ አንድ ሕዝብ ብቻ በመኖሩ ምክንያት እንደሚቀየር ገልጸው፤ ሆኖም ይህ አቋማቸው “አሃዳዊ ሥርዓት” መከተል ወይም ቋንቋና ባህልን መጫን አለመሆኑን አብራርተዋል።

“ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” መኢአድ፣ እናት ፓርቲ፣ ኢሕአፓ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ የተባሉ አምስት ፓርቲዎች የመሠረቱት ቅንጅት ነው። ትብብሩ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 1,700 ዕጩዎችን ለማስመዝገብ አቅዶ እስካሁን 1,223 ዕጩዎችን ያስመዘገበ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው አቤቱታ የምዝገባ ሂደት ላይ ያሉ 177 ዕጩዎች ሲታከሉ ቁጥሩ ወደ 1,400 ከፍ ሊል እንደሚችል ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]