በ6,395 የምርጫ ጣቢያዎች በጸጥታና በቁሳቁስ ስርጭት እክሎች ምክንያት የመራጮች ምዝገባ እንዳልተጀመረ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

በ6,395 የምርጫ ጣቢያዎች በጸጥታና በቁሳቁስ ስርጭት እክሎች ምክንያት የመራጮች ምዝገባ እንዳልተጀመረ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

​የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዋነኝነት ከጸጥታ ችግርና ከቁሳቁስ ስርጭት መዘግየት ጋር በተያያዘ ለ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በ6,395 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ አለመጀመሩን አሳወቀ።

​የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ትላንት መጋቢት 4 ቀን 2018 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ቦርዱ በ52,773 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ 7ኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ እቅድ የያዘ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በ46,757 የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭት ተከናውኖና ጣቢያዎች ተከፍተው የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል።

​ሆኖም በ6,395 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ አለመጀመሩን ሰብሳቢዋ ይፋ አድርገዋል። ከእነዚህም ውስጥ “አንዳንዶቹ በጸጥታ ምክንያት ያልጀመሩ አሉ” ያሉት የቦርድ ሰብሳቢዋ፣ “አንዳንዶቹ ደግሞ ቁሳቁስ ዘግይቶ በመድረሱ ምክንያት በሂደት ላይ ያሉ” መሆናቸው ለምዝገባው አለመጀመር ዋና ምክንያቶች መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ስልጠና በማጠናቀቅና የምርጫ ጣቢያዎችን በመክፈት ረገድ ቦርዱ የዘገየባቸው ጣቢያዎች እንደነበሩ ሜላትወርቅ ገልጸዋል።

​የጎደሉ የምርጫ አስፈጻሚዎችን የመተካቱ ሂደት በተወሰነ መልኩ ስራ እንዳጓተተም ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል። በአንዳንድ ቦታዎች የእጩዎች ምዝገባ ይፋ ከተደረገ በኋላ “እጩ ሆነው ሳለ እንደገና ለምርጫ አስፈጻሚነት ተመዝግበው የተገኙ አሉ” ያሉት ሜላትወርቅ፣ እነዚህም እንደታወቁ ወዲያውኑ እንዲሰናበቱ ተደርጓል ብለዋል።

​ሰብሳቢዋ ባለፈው ሳምንት የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረውን የመራጮች ምዝገባ ሂደት ሲያብራሩ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ቦርዱ እስከ ምርጫ ክልል ድረስ ቁሳቁሶችን ቢያሰራጭም፣ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ለማድረስ የተሽከርካሪና የነዳጅ እጥረት እንዳጋጠመ እንዲሁም “ከአንዳንድ የክልል መንግስታት” አስፈላጊውን ድጋፍ ማግኘት እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

​ባልተጠበቀ መልኩ በአንዳንድ አካባቢዎች የጣለው ዝናብ የምርጫ ቁሳቁሶችን እንዳበላሸና በአፋር ክልል በዳሎል ምርጫ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ቁሳቁሶች በእሳት መቃጠላቸውን ጠቅሰዋል። ቦርዱ እነዚህን ለመተካት ተጨማሪ የቁሳቁስ ስርጭት ለማድረግ መገደዱን ሜላትወርቅ አብራርተዋል።

​የዲጂታል መራጮች ምዝገባን በተመለከተ ቦርዱ ካለማው ሲስተም ጋር የተያያዘ የአቅም ችግር እንዳጋጠመውና በየጊዜው ሲስተሙን “ማሻሻልና ማስተካከል” እንዳስፈለገ ተገልጿል። በተለይም ምዝገባው ከተጀመረ ከሶስት ቀናት በኋላ የመራጮች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የሲስተም መጨናነቅ አጋጥሟል። ከዚህ ቀደም ቦርዱ የዲጂታል ምዝገባው ኢንተርኔት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የምርጫ ጣቢያዎችን ዝርዝር ለኢትዮ ቴሌኮም በመላክ የኢንተርኔት ሽፋን መረጃ ሰብስቦ እንደነበር ይታወሳል። በዚህም መሰረት የዲጂታል ምዝገባ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች ቢያንስ 3ጂ (3G) እና ከዚያ በላይ የኢንተርኔት ሽፋንና የመብራት አገልግሎት ያላቸው መሆን እንደሚገባቸው አሳውቆ ነበር።

​ሆኖም እንደ ሜላትወርቅ ገለጻ፣ ምዝገባው ከተጀመረ በኋላ የኢንተርኔት ግንኙነት መቆራረጥና የመብራት መጥፋት ችግሮች አጋጥመዋል። ይህንንም ለመፍታት ቦርዱ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል። በተጨማሪም ሲስተሙ የአያት ስም የሚጠይቅ ቢሆንም፣ መራጮች ስምና የአባት ስም ብቻ መሙላታቸው በሲስተሙ ላይ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል። የአካባቢ ቋንቋን አለመጠቀምና የቋሚ መራጭ ቁጥር ከወሰዱ በኋላ ምዝገባውን አለማጠናቀቅ ከታዩት ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ። ቦርዱ መረጃ ሰብስቦ ለእነዚህ መራጮች መልዕክት እንደሚልክም አሳውቀዋል።

​እስከ ትላንት ድረስ 9,036,994 መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 600,000 ገደማ የሚሆኑት በዲጂታል አማራጭ የተመዘገቡ ናቸው።

​ሜላትወርቅ አክለውም፤ መራጮች ተመዝግበው ሲወጡ ተከታትለው ጥያቄ የሚጠይቁ፣ የመራጭ ካርድ ፎቶ የሚያነሱና የምርጫ አስፈጻሚዎችን በተለያዩ ማባበያዎች መረጃ ለመጠየቅ የሚሞክሩ አካላት መኖራቸውን ቦርዱ ማስተዋሉን ገልጸዋል። ቦርዱ ለነዚህ አካላት ማስጠንቀቂያ መላኩንና እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል።

​በመኖሪያ ቤት እየዞሩ ቅስቀሳ የሚያደርጉና የምርጫ ካርድ መውሰድን ለመሰረታዊ አገልግሎቶች እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚጠይቁ አካላት መኖራቸውን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ድርጊቱ መፈጸም እንደሌለበት ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቃቸውን ገልጸዋል። “መራጩ ህብረተሰብ በነጻነትና በራሱ ፈቃድ ይወጣል እንጂ በማንም ተጽዕኖ ሊወጣ አይገባም፤ መምረጥ መብት እንጂ ግዴታ አይደለም” ሲሉ አስምረውበታል።

​በመጨረሻም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጸጥታ ሁኔታን የተመለከተ ግምገማቸውን እንዲያቀርቡ ተጠይቀው ከ15 የማይበልጡ ፓርቲዎች ብቻ ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል። ግምገማ ካቀረቡት ጋር በተደረገ ስብሰባ በ7 ክልሎች ላይ የጸጥታ ስጋት መኖሩ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ቦርዱ የግምገማ ቡድን በመላክ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ እንደሚያጣራ አስታውቋል። [ምርጫ 2018 – በኢትዮጵያ ኢንሳይደር]