የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሙሊሳ አብዲሳ፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር የዋለ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩ አለመኖሩን ተናገሩ። ምክትል ኮሚሽነሩ ይህንን የተናገሩት ቅዳሜ ሚያዝያ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. የፌዴራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ላቀረቡት መወያያ ሐሳብ የቀረበላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ ነው።
“የምርጫ ፍትሕ የዳኝነት፤ የፍትሕና የአስተዳደር አካላት ሚና” በሚል በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ “በኢትዮጵያ የምርጫ ፍትሕ የፖሊስ ሚና፣ የሕግ ማዕቀፍ እና አተገባበር” በሚል ርዕስ መወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ዕጩዎችን ከማሰር ጋር በተያያዘ ከመንግሥትም ሆነ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀረበ ምንም ዓይነት ጥቆማ የለም ሲሉ ተከራክረዋል። “ቀደም ሲል ምርጫ ቦርድ ዕጩዎችን አስራችኋል በሚል ይከሰን ነበር፤ አሁን ግን እንዲህ ዓይነት ግጭቶችን ወደ ዜሮ አውርደናል” ብለዋል። ፖሊስ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ አቅሙን ማሳደጉን የገለጹት ኃላፊው፣ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ገለልተኛ ሆኖ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ምክትል ኮሚሽነሩ “አንድም የታሰረ ዕጩ የለም” ይበሉ እንጂ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜያት የዕጩዎቻቸው መታሰር እና ወከባ እንደደረሰባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል። ለአብነትም ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዕጩ የሆኑት ወ/ት ኩሪ አሰፋ የካቲት 29 መታሰራቸውን ገልጾ በዚያው ዕለት ተፈተዋል። የትብብሩ አባል የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የድሬዳዋው ዕጩ አቶ ወንድወሰን ኪዳኔ መጋቢት 29 ታስረው ከቀናት በኋላ መፈታታቸውን ፓርቲው አስታውቋል። የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረትም በጋሞ ዞን የዲታ ምርጫ ክልል ዕጩ አቶ አብርሃም አዳሙ መታሰራቸውን በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል።
በተጨማሪም ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ እንዲሁም ሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ፣ በደቡብ ክልል (ጎፋ) እና በሌሎች አካባቢዎች በአባላቶቻቸው ላይ “ማዋከብ” እና “እስር” እያጋጠማቸው መሆኑን ለ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጡት ቃል ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
በዕለቱ በተካሄደው ውይይት ላይ ከፌደራል ፖሊስ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር እና ከፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተወከሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ከፍርድ ቤት ተወካዩ አቶ ምትኩ ማዳ በስተቀር፣ አብዛኞቹ ተቋማት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች አለማንሳታቸው በተሳታፊዎች ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል። ተሳታፊዎች በተለይም በታችኛው የፖሊስ መዋቅር ላይ ያለውን የገለልተኝነት ችግር እና የወገንተኝነት አሠራር በተመለከተ ለምክትል ኮሚሽነር ሙሊሳ ቅሬታዎቻቸውን ሰንዝረዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




