የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28፣ 2018 ዓ.ም እስከ መጋቢት 28 ድረስ እንደሚካሄድ አቅዶት የነበረውን የጊዜ ሰሌዳ ለ14 ቀናት በማራዘሙ እስከ 1.6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ እንዳስወጣው ገልጿል።
የቦርዱ አባል አቶ ተኽሊት ይመሰል ሚያዚያ 17 ቀን 2018 ዓ.ም የፌዴራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት “የምርጫ ፍትሕ በኢትዮጵያ የዳኝነት፣ የፍትሕና የአስተዳደር አካላት ሚና” በሚል በአዲስ ዓለም ዐቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ባዘጋጅው ውይይት ላይ ባደረጉት ንግግር “ለምርጫ አስፈፃሚዎች ክፍያ 14 ቀን ጨምረን ከ1.5 እስከ 1.6 ቢሊዮን ጠይቆናል” ብለዋል።
በተጨማሪም ቦርዱ ሚያዚያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው ነበር። መንግሥት ለምርጫ ቦርድ 10 ቢሊዮን ብር መመደቡን የገለጹት ሜላትወርቅ፣ “አሁን ባለን አካሄድ ከዛ በላይ የሚያስፈልግ እንደሆነ ነው የምናምነው፤ ተጨማሪ በጀት አዘጋጅተን ጥያቄ አቅርበናል” ብለዋል።
ቦርዱ በማቋቋሚያ አዋጅ 1133/2011 መሠረት የበጀት ጥያቄውን በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ሲፀድቅለት፣ ገንዘብ ሚኒስቴር በአንድ ወር ግዜ ውስጥ በቦርዱ የሒሳብ ገቢ ማድረግ እንዳለበት ይገልጻል።
ቦርዱ የመራጮች ምዝገባን ሲያከናውኑ ከቆዩ 195 ሺሕ 316 ምርጫ አስፈፃሚዎች ውስጥ 70 ሺሕ ለሚሆኑት ክፍያ መፈፀሙን ገልጿል። የምርጫ አስፈፃሚዎች “በገባነው ውል መሠረት፣ የመጀመሪያው ክፍያ 40 ፐርሰንት የሚከፈለው የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀ በ15 ቀናት ውስጥ የሚል ነው። ነገር ግን ያለውን ሁኔታ ቦርዱ በመመልከት፣ 1 ቢሊዮን ብር ለ70 ሺሕ አስፈፃሚዎች” ከፍለናል ብለዋል።
ሰብሳቢዋ ክፍያው በባንክ ሥርዓት እየተጣራ መግባት ስለሚገባው የዳታ ማጥራቱ ሥራ አሁንም እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ሆኖም የምርጫ አስፈፃሚዎች የክፍያው መዘግየት ላይ ቅሬታ እያሰሙ መሆኑን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከምርጫ አስፈፃሚዎች የሐሳብ መለዋወጫ የቴሌግራም ገጽ ላይ ለመመልከት ችላለች።
በተጨማሪም ለምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች የተከፈላቸው ገንዘብ መጠን ከክልል ክልል ተለያይቷል በማለት ቅሬታቸውን ሲያሰሙም ሚዲያችን ተመልክታለች። “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ቦርዱ ከምርጫ አስፈፃሚዎች ጋር የገባው የቅጥር ውል አንቀፅ 4፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች ክፍያ “በቀን አበል የሚታሰብ 548 ብር” መሆኑን ገልጾ፣ የቀን ቆጠራው ውሉ ከሚፈረምበት የካቲት 20፣ 2018 ቀን ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ ተጠናቆ የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ክልል እስከሚመልሱበት እስከ ሚያዝያ 10 እንደሆነ ይገልጻል። በተጨማሪም፣ ለድምፅ መስጫ ከግንቦት 20 እስከ 26 ያሉት ሰባት ቀናት ተጨምረው በጠቅላላው የ54 ቀናት የቅጥር ውል እንደገቡ ውሉ ያሳያል።
በዚህም መሠረት፣ አጠቃላይ ክፍያው 29 ሺሕ 592 ብር ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ክፍያ 40 ፐርሰንት 11 ሺሕ 836 ብር የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀ በ15 ቀናት ውስጥ የሚከፈል ይሆናል በሚል በውሉ ላይ ተቀምጧል።
ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ለ14 ቀናት መራዘሙን ተከትሎም ለሁሉም ምርጫ አስፈፃሚዎች በሚል መጋቢት 3 ቀን 2018 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች የውል ግዜ መራዘሙን ጠቅሶ፣ በዚህ መሠረትም ለተጨመሩት 14 ቀናት ክፍያ እንደሚፈፅም ለምርጫ አስፈፃሚዎቹ ገልጾላቸው ነበር።

በተጨማሪም ቦርዱ ሚያዚያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫው፣ ከምርጫ አስፈፃሚዎች በተጨማሪ ለፖለቲካ ፓርቲዎችም የፋይናንስ ድጋፍ ማድረጉን አሳውቋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ለማድረግ የነዳጅ እና የፋይናንስ ችግር ገጥሞናል ሲሉ ቢቆዩም፣ ቦርዱ እንዲህ ያለ ጥያቄ ቀርቦልኝ አያውቅም የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ዋና ሰብሳቢዋ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመደበኛ ግዜ የሚሰጣቸው ገንዘብ እና በምርጫ ወቅት የሚሰጣቸው በጀት የተለያየ መሆኑን ገልጸው፣ “የመጀመሪያ ዙር 30 በመቶውን ከፍለናል። የሚቀረውን በተለያየ ክፍፍል የሚሰጠውን ለመስጠት የመረጃ ክፍተት ገጥሞናል” ብለዋል።
ሜላትወርቅ ኃይሉ የገጠማቸውን የመረጃ ክፍተት ሲያብራሩ፣ የአካል ጉዳተኛ ዕጩዎች ቁጥር መረጃ በደንብ አጥርተው ያቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለመኖራቸው በጀቱን ማከፋፈል እንዳልተቻለ የገለጹ ሲሆን፣ የፋይናንስ ድጋፍ መስጠት መጀመራቸውን በመግለፅ፣ “36 ለሚሆኑት ፓርቲዎች ከፍለናል፤ ለቀሪዎቹም የምንከፍል ይሆናል” ብለዋል።
ሰብሳቢዋ ለ32 የፖለቲካ ፓርቲዎች በንግድ ባንክ በኩል 81 ሚሊዮን ብር ገደማ የፋይናንስ ድጋፍ መሰራጨቱን ገልጸው፣ ለቀሪዎቹ “በሌላ ባንክ የሚከፈል በመሆኑ እየተከታተልን መክፈላችንን እንቀጥላለን” ብለዋል። ሆኖም ፓርቲዎቹ የሴት ዕጩዎቻቸውን ቁጥር በትክክል ያሳወቁ ቢሆንም፣ የአካል ጉዳተኛ ዕጩዎቻቸውን “ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸው እና ይህንን ከፓርቲዎች በሰነድ ማረጋገጥ ባለመቻሉ ክፍያው ዘግይቷል” ብለዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




