‘የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ’ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ኃይለማርያም ለ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ 3 ሺሕ ተቀማጭ እና 2 ሺሕ ተንቀሳቃሽ፣ በድምሩ 5 ሺሕ ታዛቢዎችን ለማሰማራት ዝግጅት ማድረጋቸውን ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 5 ሺሕዎቹ ታዛቢዎች ጊዜያዊ ማለትም ለምርጫው ቀን ብቻ በታዛቢነት የሚሰማሩ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም 522 የረጅም ጊዜ ታዛቢዎች ማሰማራታቸውን የገለጹት አቶ አበራ፤ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ 547 የምርጫ ክልሎች በያንዳንዳቸው አንድ ታዛቢ ለመመደብ የተዘጋጁ ቢሆንም፣ ትግራይ ክልልን ጨምሮ የመራጮች ምዝገባ ያልተካሔደባቸው አካባቢዎች በመኖራቸው ቁጥሩ ዝቅ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል።
ይህ የረጅም ጊዜ ታዛቢዎች ቡድን የመራጮችን ምዝገባ ሂደት፣ የሲቪል ምኅዳሩ ምን እንደሚመስል፣ የመራጮች ትምህርት አሰጣጥ ደረጃ፣ እንዲሁም የፓርቲዎች ክርክርና ዘመቻ ምን ይመስላል የሚሉትን ጉዳዮች እንደሚዳስስ ያስረዱት አቶ አበራ፤ ታዛቢዎቹ አጠቃላይ የምርጫ ዝግጅቱን በተመለከተ በሳምንት ሁለት ጊዜ መረጃዎችን ወደ ዋናው የመረጃ ቋት ይልካሉ ብለዋል።
የአጭር ጊዜ ወይም በምርጫው ዕለት የሚሰማሩትን 5 ሺሕ ታዛቢዎች ክፍፍል በተመለከተም፣ በምርጫ ጣቢያዎች ብዛት ላይ ተመሥርቶ እንደሚተገበር ኅብረቱ ገልጿል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ተቀማጭ ታዛቢዎቹ አራት ጊዜ የምርጫውን ሂደት ተከታትለው ሪፖርት ያደርጋሉ። እነርሱም በመጀመሪያ የምርጫውን አከፋፈት በተመለከተ ዝግጅቱን ጨምሮ የተከፈተበት ሰዓት፣ የድምፅ አሰጣጡን ሂደት፣ ከዚያም የተዘጋበትን ሰዓት፣ ቆጠራ እና የምርጫ ውጤትን የሚታዘቡ ናቸው።
አቶ አበራ “ይህንንም በተገቢው መንገድ ለመተግበር ለታዛቢዎች አስፈላጊው ሥልጠና በsimulation exercise (በቪዲዮ የታገዘ ማስረጃ) ጭምር እየሰጠን ነው፤ ታዛቢዎቹ አፖሎ ፕላትፎርም የተሰኘ አዲስ ሲስተም ይጠቀማሉ” ብለዋል።
ታዛቢዎችን ለመመልመል “Digital election observation workspace” (ዲጂታል የምርጫ ታዛቢዎች የሥራ ማቀላጠፊያ) የተሰኘ አዲስ ፖርታል ወይም ቴክኖሎጂ እንደተጠቀሙ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ፖርታሉ ታዛቢዎችን ለመመልመል፣ ለማሰልጠን እና ፈቃድ ለመስጠት፣ እንዲሁም ለማሰማራት እና ለመቆጣጠር እንደሚረዳ አክለው ገልጸዋል።
“ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር በጥራት፣ በፍጥነት እና መረጃዎችን በሚገባ ለመያዝ የሚረዳ መሣሪያ ነው፤ ይህንን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ላይ በማዋል ነው ታዛቢዎችን የመለመልናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።
በዚህ የምልመላ ሂደት ውስጥ 70 የሚጠጉ አባል ድርጅቶች መሳተፋቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የታዛቢዎቹ የትምህርት ደረጃ፣ ገለልተኝነት እና ሥነ ምግባር መረጋገጡንም አክለው ገልጸዋል።
‘የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ’ አጠቃላይ የቅድመ ምርጫ ዝግጅቱን በተመለከተ ከምርጫው በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ዳይሬክተሩ አሳውቀዋል። አክለውም፣ ምርጫው በተካሄደ እስከ 72 ሰዓታት ባለው ጊዜ ውስጥ መግለጫ እንደሚሰጡ ጠቁመዋል። እንዲሁም በመቀጠል አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን ወይም የቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ወቅት እና ከድኅረ ምርጫ በኋላ ያለውን ሁኔታ በዝርዝር እንደሚገልጹ አስታውቀዋል።

በዚህ መግለጫ ውስጥ በምርጫው ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች እና በጎ ተሞክሮዎች ተፈትሸው ምክረ ሐሳቦች ጭምር በዝርዝር እንደሚተነተኑ አቶ አበራ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም “ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የትዝብት ሥራዎች፣ የሚዲያ ክትትል እና የትምህርት ሥራዎች ከአንድ ዓመት በፊት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተን እየሠራን ነው” ብለዋል።
የቅድመ ምርጫ ሥራዎችን በተመለከተም፣ ለመራጮች “እኔ እመርጣለሁ” በሚል መሪ ቃል የመራጮች ትምህርትና ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀው፤ ይህንንም ትምህርት በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በበይነመረብ፣ በሕትመቶችና በማኅበራዊ ሚዲያዎች እያስተላለፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በዚህም 1,700 መልዕክቶች በቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚተላለፉ ሲሆን፣ በሬዲዮ ጣቢያዎች ደግሞ 1,650 መልዕክቶችን በ10 ቋንቋዎች እያስተላለፉ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በየተያያዘም “የእሷ ድምፅ በተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ሴቶችን ማዕከል ያደረገ የምርጫ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራን ነው” ብለዋል።
‘የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ’፣ 9 አባላት ያሉት የሚዲያ ክትትል ቡድን አዋቅሮ ሚዲያው ለምርጫ ዘገባዎች የሚሰጠውን ሽፋን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚዲያ አጠቃቀም፣ መረጃዎች በአግባቡ ለመራጩ መድረሳቸውን፣ እንዲሁም ሐሰተኛ ወይም አደናጋሪ መረጃዎች መሰራጨታቸውን ይከታተላል። “በተጨማሪም የግል እና የመንግሥት ሚዲያዎች የሚያደርጉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር እንዲሁም የአየር ሰዓት ድልድልን በተመለከተ ፓርቲዎቹ የተሰጣቸውን ሰዓት በአግባቡ መጠቀማቸውን እና አለመጠቀማቸውን እንከታተላለን” ሲሉ አቶ አበራ አክለዋል።
“አከራካሪ” ቦታዎች ጭምር ታዛቢዎችን ለማሰማራት መዘጋጀታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ይሁን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ ታዛቢዎችን ማሰማራት የማይቻልባቸው የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች የታዛቢዎችን እንቅስቃሴ ይገድባሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
አቶ አበራ የኢንተርኔት መሠረተ ልማት አለመሟላት እና መቆራረጥ በምርጫ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል በፓርቲዎች ቅሬታ ቢነሳም፣ “የምርጫ ምዝገባው በከፊል በዲጂታል መሆኑ ግልጸኝነትን ከማረጋገጥ እና የድምፅ መስጠት ድግግሞሽን ወይም ማጭበርበርን ይቀንሳል፤ የመራጮችን ማንነት በግልጽ ለማወቅ ይረዳል” በማለት አዎንታዊ ጎኑ እንደሚበዛ አስረድተዋል።
ዳይሬክተሩ የዘንድሮው ምርጫ ከ6ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ምን እንደሚለየው ሲናገሩ “ምዝገባው በዲጂታል መሆኑ፣ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ከስድስተኛው ምርጫ በቁጥር አንሶ መዋቀሩ፣ እንዲሁም የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ ከባለፈው ምርጫ የተሻለ ያደርገዋል” ብለዋል።
የምርጫ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴን በተመለከተ በዝርዝር ያስረዱት አቶ አበራ “በስድስተኛው ምርጫ ወቅት በየምርጫ ጣቢያው የምርጫ አስፈፃሚውን ጨምሮ ሦስት አባላት ያሉት ሰሚ ኮሚቴ ነበር የተቋቋመው፤ ይህም ማለት 50 ሺሕ የምርጫ ጣቢያ ቢኖር 150 ሺሕ የሰው ኃይል ያስፈልጋል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከበጀት አኳያ የሚያዋጣ አይደለም። በዘንድሮው ምርጫ ግን በምርጫ ክልል ብቻ አንድ ሰው እንዲኖር ተደርጓል” በማለት ውሳኔውን ደግፈው ተናግረዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ትምህርት እንዲሰጡ እና ምርጫ እንዲታዘቡ ዕውቅና የሰጣቸው አገር በቀል ድርጅቶች ብዛት 212 ሲሆኑ፣ ለዘንድሮው 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ደግሞ 224 ድርጅቶች ዕውቅና እንደተሰጣቸው መገለጹ ይታወሳል። ኅብረቱ በ2012 የተመሠረተ ሲሆን፣ ከ190 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጀቶችን በአባልነት እንዳቀፈ እና ባለፉት ሰባት ዓመታት ስድስት ምርጫዎችን እና ሕዝበ ውሳኔዎችን እንደታዘበ የኅብረቱ ድረገጽ ይገልጻል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




