የዱባዩ የምርጫ ሰነዶች እና ቁሳቁሶች ህትመት ምን ይለየዋል?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ለሚያካሄደው ምርጫ የሚያገለግሉ ሰነዶች እና ቁሳቁሶች ከሀገር ውጪ ማሳተም ጀምሯል። የምርጫ ሰነዶችን ህትመት የሚያካሂደው  “አል-ጉህሬር” የተባለ በዱባይ የሚገኝ ማተሚያ ቤት ነው።

የምርጫ ሰነዶች እና ቁሳቁሶች ህትመት የተጀመረው ባለፈው ታህሳስ ወር ነበር። የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እና ምክትላቸው ውብሸት አየለ ለኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ማላዊ እና ዛምቢያ የምርጫ ቁሳቁሶችን እንዳተመ የተነገረለትን የዱባዩ ማተሚያ ቤትን በወቅቱ ስፍራው ድረስ በመጓዝ ጎብኝተዋል። የማተሚያ ቤቱንም ኃላፊዎችም አግኝተው አነጋግረዋቸዋል።

የምርጫ መዛግብቱ እና ሰነዶቹ በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማሊኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች እንደሚታተሙ ምርጫ ቦርድ ገልጾ ነበር። ለመራጮች ምዝገባ የሚደረገው የሰነድ ዝግጅት መጠባበቂያን ጭምር እንደሚያካትት ቦርዱ ጨምሮ ገልጿል። 

ምርጫ ቦርድ የዱባዩ ህትመት የመራጮች ምዝገባን ዘመናዊ እና ተዓማኒ እንደሚያደርግ ጠቁሟል። ህትመቱ የምርጫው ሂደት አለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ እና አዲሱ የምርጫ ህግ ላይ የተቀመጡትን መስፈርቶች ያሟላ እንዲሆን የሚያስችል ነውም ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪም ሊፈጠሩ የሚችሉ ስህተቶችን ለመቀነስና እና ማጭበርበርን ለማስወገድ እንደሚረዳ ተገልጿል።

ህትመቱ ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ሲከናወን ከነበረው ምን እንደሚለየው ለመረዳት ዝርዝሩን ከስዕላዊ መረጃው ይመልከቱ።