የደንጣ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ለፍትህ ፓርቲ (ደሕዴፍፓ) ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ በክልላዊ ፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ መሟላት ያለበትን ቅድመ ሁኔታ ቢያሟላም የእውቅና ሰርተፍኬት ባለማግኘቱ ምክንያት በምርጫው መሳተፍ እንዳልቻለ አስታወቀ። ሆኖም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በሰጠው ምላሽ ፓርቲው የምዝገባ ጥያቄውን ያቀረበው ከመራጮች ምዝገባ 90 ቀናት በፊት ስላልሆነ እና በሕግ የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ያሟላ ባለመሆኑ ዘንድሮ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሊሳተፍ እንደማይችል ገልጿል።
የደሕዴፍፓ ሊቀመንበር ኢ/ር ዳዊት ኃይሉ “ለምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት ፓርቲው የደንጣ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ለፍትህ ፓርቲ በሚል ስያሜ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባ ጥያቄ አቅርቧል።
“ልናሟላ የሚገባውን ቅድመ ዝግጅት ጨርሰን ብናቀርብም” ምርጫ ቦርድ “የእውቅና ሰርተፍኬት ያለምንም ምክንያት ሳይሰጠን በመቅረቱ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ እንዳንሳተፍ ተደርገናል” ሲሉ የፓርቲው ሊቀመንበር አክለዋል።
ፓርቲው “ሕዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ለቦርዱ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የተፈቀደው እና ታኅሣሥ 18 ቀን 2018 በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው የምስረታ ጉባኤ፤ የሕዝቡን ተሳትፎ እና የድጋፍ መጠኑን የሚያሳይ” እንደነበር ዳዊት አስታውሰዋል።
ዳዊት በማከልም “ታኅሣሥ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ለቦርዱ የቀረበው የምስረታ ሪፖርት፣ ጥር 01 ቀን 2018 በቦርዱ የጸደቀበት ሂደት” እንዳለ ገልጸው በ14 ቀናት የግዜ ገደብ “በአርማና በስያሜ ዙሪያ የሕዝብ አስተያየት ቦርዱ ተቀብሎ ምላሽ እንድንሰጥበት አቅጣጫ አስቀምጦ ነበር” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 03 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በማህበራዊ ድህረ ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት “እነ አቶ ዳዊት ኃይሉ የደንጣ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ለፍትህ ፓርቲ (ደህዴፍፓ) በሚል ስያሜ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባ ጥያቄ ያቀረቡ” መሆኑን ገልጾ “በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 68 ንዑስ አንቀጽ 2 እና 3 መሰረት በፓርቲው ስም፣ አርማ ወይም ሌሎች ጉዳዮች ተቃውሞ ያለው ሰው ከጥር 03 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በ14 ቀናት ውስጥ ተቃውሞውን ለቦርዱ ጽሕፈት ቤት እንዲያቀርብ” አሳስቦ ነበር፡፡
ዳዊት እንደሚሉት “አስፈላጊውን ምላሽ ፓርቲያችን ሰጥቶ ሕጋዊ እውቅና ማግኘታችን ቢታወቅም” ቦርዱ “እስካሁን የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ባለመስጠቱ፣ ምንም ምላሽ ሳይሰጠን የዕጩዎች ምዝገባ ተጠናቆ የምርጫ ሂደቱ ቀጥሏል” ሲሉ አብራርው ፓርቲያቸው የካቲት 10 ቀን 2018 ቀን ጀምሮ ሰርተፍኬቱን ባለማግኘቱ የካቲት 16 ቀን 2018 የተጠናቀቀውን የእጩዎች ምዝገባ ላይ ሳይሳተፍ መቅረቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቅሬታው በሰጠው ማስተባበያ በምርጫ፣ በፖለቲካ ፖርቲዎች ምዝገባ እና በምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 65(8) መሠረት በማናቸውም ደረጃ ምርጫ በሚካሄድበት ዘመን የሚካሄድ የምዝገባ ጥያቄ የመራጮች ምዝገባ ከመጀመሩ 90 ቀናት በፊት የቀረበ ከሆነ የዕጩዎች ምዝገባ ከመጀመሩና የምርጫ ዘመቻ የጊዜ ሠሌዳ ከመውጣት በፊት መጠናቀቅ እንዳለበት ጠቅሷል።

በተጨማሪም ቦርዱ እንደገለጸው የመራጮች ምዝገባ የጀመረው የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. ሲሆን፤ ፖርቲው የምዝገባ ጥያቄውን ያቀረበው ደግሞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ነው። ስለሆነም ፖርቲው የምዝገባ ጥያቄውን ያቀረበው ከመራጮች ምዝገባ 90 ቀናት በፊት ስላልሆነ በህግ የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ያሟላ ባለመሆኑ ዘንድሮ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሊሣተፍ አይችልም ብሏል።
ዳዊት ደሕዴፍፓ በማንነት ጥያቄ ውስጥ “ከ35 ዓመት በላይ የቆየውን” የደንጣ ማህበረሰብ ጥያቄ “ፍትህ ለማሰጠትና እና አስተዳደራዊ በደሎችን ለማሻሻል” እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በማከልም ዳዊት ፓርቲያቸው “አሁን ባለው ምርጫ መሳተፍ ባይችልም እንኳን ለወደፊት የትግል ምዕራፋችንን በማደራጀት ለቀጣዩ አምስት ዓመት [8ኛው ዙር ምርጫ] ሙሉ በሙሉ በቁርጠኝነት በመዘጋጀት ላይ ነን” ያሉ ሲሆን “ሕጋዊ የሰውነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ቦርዱ እንዲሰጠን አበክረን እንጠይቃለን” ሲሉም አክለዋል። [ምርጫ 2018 – በኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




