የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ከፊል አሃዛዊ ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ መረጃዎቹ በተለያዩ የምርጫ ክልሎች አሸናፊ የሆኑ ተመራጮች ባገኟቸው ድምፆች መካከል እጅግ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ ያሳያሉ። በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የመራጮችን ድምፅ ያገኙ ተመራጮች ቢመዘገቡም፣ በሌላ በኩል ከአንድ ሺሕ እስከ አሥር ሺሕ በሚያንስ ድምፅ ያሸነፉ ዕጩዎች ግማሽ ሚሊዮን ድምፅ ካገኙት ጋር እኩል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) የመግባት ዕድል ማግኘታቸው ተስተውሏል።
በዚህ ረገድ በአማራ ክልል “አዲስ ቅዳም” የምርጫ ክልል የተወዳደሩት ፈተና ባዩ ሽባባው ያገኙት አጠቃላይ ድምፅ 840 ብቻ በመሆኑ፣ በምርጫው እጅግ በጣም ዝቅተኛ ድምፅ ያገኙ ተመራጭ ሆነዋል። ፈተና ባዩ በተወዳደሩበት በዚህ የምርጫ ክልል በአጠቃላይ ድምፅ የሰጡት ሰዎች ብዛት 1,916 ብቻ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ እርሳቸው ያገኙት ውጤትም የአጠቃላይ መራጮቹን 44 በመቶ ይሸፍናል። እንደ ምርጫ ቦርድ አሠራር አንድ የድምፅ መስጫ ሳጥን (ኮሮጆ) ከ1,200 እስከ 1,500 የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ማስተናገድ የሚችል በመሆኑ፣ ፈተና ባዩ የተወዳደሩበት የምርጫ ክልል ውስጥ በትክክል የተሰጠው አጠቃላይ ድምፅ ሁለት ኮሮጆ እንኳ የማይሞላ መሆኑን መረዳት ይቻላል።
| ተ.ቁ. | ክልል | የምርጫ ክልል | የተመራጭ ሥም | ያገኙት ድምፅ | አጠቃላይ የመረጡ ሰዎች ቁጥር | ተመራጭ ያገኙት ድምፅ ከአጠቃላይ መራጮች በመቶኛ |
| 1 | አማራ | አዲስ ቅዳም | ፈተና ባዩ ሽባባው | 840 | 1,916 | 44% |
| 2 | ቤኒሻንጉል ጉሙዝ | ሺናሻ ልዩ | ፍሬህይወት አበበ ጎበና | 1,881 | 2,830 | 66% |
| 3 | ደቡብ ኢትዮጵያ | ላስካ/ባስኬቶ መደበኛ | ካሳሁን ደለነ ደያላ | 3,869 | 5,275 | 73% |
| 4 | አዲስ አበባ | የምርጫ ክልል 2 እና 14 | ዳንኤል ክብረት ብርሃኔ | 4,157 | 6,367 | 65% |
| 5 | ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ | ሱርማ ልዩ | ሜሪ ገርሲ ፈጠነ | 4,775 | 5,199 | 92% |
| 6 | ደቡብ ኢትዮጵያ | አይዳ ልዩ | እንድሪስ ወርቁ ጉሳ | 4,806 | 8,305 | 58% |
| 7 | አዲስ አበባ | የምርጫ ክልል 15 | ደበሌ ቃቢታ ሁርሳ | 5,280 | 7,892 | 67% |
| 8 | አማራ | አርጎባ ልዩ | ማህሙድ መሀመድ አወል | 6,506 | 8,895 | 73% |
| 9 | አማራ | አማኑኤል | ዮሃንስ ጥላሁን ጌቴ | 6,613 | 6,613 | 100% |
| 10 | ደቡብ ኢትዮጵያ | ጊዶሌ መደበኛ | ዘነበ ሳጎያ አርካይዶ | 6,644 | 12,979 | 51% |
ሰንጠረዥ 1፤ እጅግ ዝቅተኛ ድምፅ ያገኙ 10 የፓርላማ ተመራጮች
በተመሳሳይ ሁኔታ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “ሸንጎ ልዩ” የምርጫ ክልል ፍሬሕይወት አበበ ጎርፉ በ1,881 ድምፅ (66%) እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ “ሳስካ/ሳስካቶ መደበኛ” የምርጫ ክልል ካሳሁን ደለነ ደያላ በ3,869 ድምፅ (73% በትክክል የመረጡ ሰዎችን ዝቅተኛ ድምፅ በማግኘት) አሸናፊ መሆን ችለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የምርጫ ክልል 2 እና 14” የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት አቶ ዳንኤል ክብረት ብርሃኔ በ4,157 ድምፅ (65% መራጮችን ድምፅ በማግኘት) አሸናፊነታቸውን አረጋግጠዋል። አቶ ዳንኤል ክብረት በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በግል ዕጩነት በ“ምርጫ ክልል 28” ተወዳድረው ያሸነፉ ሲሆን፣ በወቅቱ 51,760 ድምፅ ማግኘት ችለው እንደነበር ይታወሳል።
በተቃራኒው በአፋር፣ በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ የምርጫ ክልሎች እጅግ ግዙፍ የሆነ የመራጮች ቁጥር እና የአሸናፊዎች ድምፅ የተመዘገበባቸው ሆነዋል። በዚህ ረገድ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ድምፅ በማግኘት ቀዳሚ የሆኑት በአፋር ክልል “አብዓላ” የምርጫ ክልል የተወዳደሩት የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ ሙሳ ናቸው። በምርጫ ክልሉ በትክክል ድምፃቸውን ከሰጡት 560,005 መራጮች መካከል ወይዘሮ አይሻ 553,458 ድምፅ (99 በመቶ) በማግኘት ተመርጠዋል።
በተመሳሳይ፣ በሶማሌ ክልል “ፊልቱ” የምርጫ ክልል የተወዳደሩት ኢክራም መሐመድ አደን 539,524 መራጮች ባሉበት ጣቢያ ሙሉውን 539,524 ድምፅ (100 በመቶ) ያገኙ ሲሆን፤ በዚሁ ክልል “ቀብሪ በያህ” ምርጫ ክልል የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ተመራጭ የሆኑት አቶ አብዲቃድር አብዱላሂ በያህ 505,275 ድምፅ (93%) አግኝተዋል።
| ተ.ቁ. | ክልል | የምርጫ ክልል | የተመራጭ ሥም | ያገኙት ድምፅ | አጠቃላይ የመረጡ ሰዎች ቁጥር | ተመራጭ ያገኙት ድምፅ ከአጠቃላይ መራጮች በመቶኛ |
| 1 | አፋር | አብአላ | አይሻ መሀምድ ሙሣ | 553,458 | 560,005 | 99% |
| 2 | ሶማሌ | ፊልቱ | ኢክራም መሀድ አደን | 539,524 | 539,524 | 100% |
| 3 | ሶማሌ | ቀብሪ በያህ | አብዲዋስ አብድላህ በዴ | 505,275 | 542,112 | 93% |
| 4 | ኦሮሚያ | ሚቻታ | ወዚራ አህመድ ሃሚድ | 441,053 | 441,053 | 100% |
| 5 | ኦሮሚያ | ፉኛን ቢራ | ሲራጅ አብዱላሂ ሁሴን | 438,557 | 438,557 | 100% |
| 6 | አፋር | ዱብቲ | ሐሰን አብዱልቃድር በርከት | 437,860 | 487,842 | 90% |
| 7 | ኦሮሚያ | ሀራዋጫ | አብዱረማን ኑሬ አሊሾ | 369,567 | 369,567 | 100% |
| 8 | አፋር | አይሳይታ | ፋጡማ አወል ዊቲካ | 368,735 | 370,142 | 100% |
| 9 | አፋር | ዳሊፋጌ | በርኦ ሀሰን በርኦ | 360,781 | 378,785 | 95% |
| 10 | ሶማሌ | ፊቅ | ፈርዶሳ አህመድ መሐሙድ | 358,396 | 358,396 | 100% |
ሰንጠረዥ 2፤ እጅግ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙ 10 የፓርላማ ተመራጮች
ተመራጮች በአማካይ ያገኟቸው ድምፆች በክልሎች መካከልም የጎላ ልዩነት የታየበት ሲሆን፣ አፋር ክልል ተመራጮች በአማካይ 300 ሺሕ ገደማ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙበት ክልል ሆኗል። በተቃራኒው፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተመራጮች በአማካይ 21,866 ድምፆችን በማግኘት በምርጫ ክልሎች ዝቅተኛ ድምፆች የተገኙበት ሆኖ ተመዝግቧል።
| ተ.ቁ. | ክልል | ተመራጮች ያገኙት አማካይ ድምፅ |
| 1 | አፋር | 302,975 |
| 2 | ሶማሌ | 204,744 |
| 3 | ኦሮሚያ | 128,991 |
| 4 | ድሬዳዋ | 123,313 |
| 5 | ጋምቤላ | 90,015 |
| 6 | ሲዳማ | 88,445 |
| 7 | ሃረሪ | 78,044 |
| 8 | አማራ | 72,469 |
| 9 | ማዕከላዊ ኢትዮጵያ | 55,268 |
| 10 | ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ | 44,082 |
| 11 | ደቡብ ኢትዮጵያ | 37,895 |
| 12 | አዲስ አበባ | 35,408 |
| 13 | ቤኒሻንጉል ጉሙዝ | 21,866 |
ሰንጠረዥ 3፤ በክልሎች ተመራጮች ያገኟቸው አማካይ ድምፆች
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 54(3) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የሕዝብ ብዛትንና በልዩ ትኩረት ውክልና የሚሰጣቸው አናሳ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቁጥር መሠረት በማድረግ 550 የማይበልጥ ሆኖ ከዚህ ውስጥ አናሳ ብሔረሰቦች 20 የማያንስ መቀመጫ ይኖራቸዋል” ሲል ይደነግጋል።
በዚህ መሠረት ፓርላማው 547 መቀመጫዎች ቢኖሩትም የምርጫ ክልሎች ለመጀመሪያው ምርጫ ከተካለሉ ወዲህ የሕዝቦችን አሰፋፈር ለውጥ እና የሕዝብ ዕድገትን ከግምት ውስጥ ያስገባ ማስተካከያ አልተደረገም።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮው የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በ501 የምርጫ ክልሎች ያካሄደ ሲሆን፣ የ486ቱ ውጤት በይፋ ፀድቆ፣ ቀሪዎቹ ድጋሚ ምርጫ ወይም ድጋሚ ቆጠራ እንደሚያካሂዱ መነገሩ ይታወሳል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




