ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምን አያሸንፉም?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ ብዙዎች እንደጠበቁት በአንድ ፓርቲ ፍፁም የበላይነት መጠናቀቁ ተረጋግጧል። ገዢው ብልፅግና ፓርቲ በፓርላማ 90 በመቶ ወንበሮችን እንዲሁም በክልሎች ምክር ቤቶች ደግሞ 89 በመቶ የሚሆኑትን መቀመጫዎች ጠቅልሎ ሲወስድ፣ ተቃዋሚዎችና የግል ዕጩዎች ያገኟቸው ጥቂት ወንበሮች አብዛኞቹ ገዢው ፓርቲ ዕጩ ባልቀረበባቸው አካባቢዎች የተመዘገቡ ናቸው።

ይህ ኹነት በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ ላይ ትልቅ ጥያቄ ያስነሳል፦ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምን ማሸነፍ አይችሉም?

ምርጫ 97 እንደ መታጠፊያ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተወሰኑ የምክር ቤቶች መንበሮችን ማግኘት ይችሉ የነበረው ከ1997ቱ ምርጫ በፊት በነበሩት የመጀመሪያዎቹ የምርጫ ዓመታት ነበር። ይሁን እንጂ የሀገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ሙሉ በሙሉ ያናጋውና የተቃዋሚዎችን እውነተኛ እምቅ አቅም ያሳየው ታሪካዊው የምርጫ 97 ኹነት ነበር። በወቅቱ ተቃዋሚዎች በፓርላማ ሰፊ ወንበሮችን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ የዋና ከተማዋን የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ሙሉ በሙሉ በበላይነት ማሸነፍ ችለው ነበር።

ነገር ግን ያ የእውነተኛ የፉክክር ወቅት ያጫረው ተስፋ ብዙ አልዘለቀም። መንግሥትና ተቃዋሚዎች በምርጫው ውጤት ላይ ሳይማመኑ መቅረታቸው አገሪቱን ወደ ከባድ ቀውስ ከመክተቱም በላይ፣ ከምርጫ 97 ማግስት ጀምሮ የነበሩት ምርጫዎች ሁሉ የምኅዳሩን መጥበብ አስከትለው መጡ።

ገዢው ፓርቲ የሽንፈት ጫፉን አይቶ ከተመለሰበት ከምርጫ 97 በኋላ በተካሄዱት ተከታታይ ምርጫዎች (በተለይም የ2002 እና የ2007 ምርጫዎች) ተቃዋሚዎች ወንበር ማግኘት ጭራሽ እየተሳናቸው መጥቶ ገዢው ፓርቲ 99.6 እና 99.8 በመቶ የፓርላማ ወንበሮችን እስከመቆጣጠር ደርሶ ነበር።

ምንም እንኳን የቀድሞው ገዢ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በተወሰነ መልኩ ተቀይሮ በብልፅግና ፓርቲ ቢተካም፣ በምርጫ 2013ም ይሁን በምርጫ 2018 የተገኘው ውጤት ተመሳሳይ ፍፁም የገዢው ፓርቲ የበላይነት የታየበት ነበር።

የተቋማት ገለልተኛ አለመሆን

ለዚህ ተደጋጋሚ የአንድ ፓርቲ የበላይነት እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሰው የነፃ ተቋማት አለመኖር እና በመንግሥትና በገዢው ፓርቲ መካከል ያለው መስመር መደብዘዝ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የሰጡት ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ገዢዎች ለዲሞክራሲ ቁርጠኛ አለመሆናቸውን ጠቅሰው፣ ነፃ ፍርድ ቤት፣ ነፃ ሚዲያ እና ነፃ ምርጫ ቦርድ አለመኖር ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ ትልቅ እንቅፋት መሆናቸውን ይገልጻሉ።

አቶ አንዱዓለም እንደሚከራከሩት፣ ከኢሕአዴግ ጊዜ ጀምሮ ተንሰራፍቶ የቆየው በሚሊዮን የሚቆጠር የካድሬ መዋቅር ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሲል በምርጫ ወቅት በፓርቲ ተወዳዳሪነትና በአስመራጭነት ይመጣል። ለዚህም በማሳያነት በ1997 ዓ.ም. በደሴና ወልዲያ የማጣሪያ ምርጫ ወቅት “የምርጫ ቦርድ ወኪል ሆኖ የመጣ ሰው በአርባምንጭ የኢሕአዴግ የወጣቶች ተወካይ” የነበረ መሆኑንና እርሱው ራሱ ከእነሱ ጋር ይከራከር እንደነበር ያስታውሳሉ።

የኦሮሞ ፌደራል ኮንፈረንስ (ኦፌኮ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሱልጣን ቃሲም በበኩላቸው፣ “በቀበሌም ይሁን በወረዳ በተለያየ የአስተዳደር ደረጃ ያሉ ተቋማት የመንግሥት ተቋማት ናቸው… ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የስነ መንግሥት ልምምድ መንግሥትና ፓርቲን የሚለይ አይደለም” ይላሉ። ገዢው ፓርቲ ምኅዳሩን ዘግቶ፣ ቢሮዎችን ከርችሞ እና ተፎካካሪዎችን ካዳከመ በኋላ “ለተፎካካሪዎች ወንበር ለቀናል” የሚለው አካሄድ የማስመሰል ተግባር እንደሆነ ይኮንኑታል።

የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ዎሕነን) ፕሬዝዳንት ዶ/ር ወልደማርያም ልሳኑም ተቋማዊ ድክመቱን ሲያብራሩ፣ በሕገ-መንግሥቱ ጭምር የምርጫ ቦርድን የሚያደራጀው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር (የአንድ ገዢ ፓርቲ መሪ) መሆኑ ተቋሙ የፓርቲው ነጸብራቅ እንዲሆን በር የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል።

በምርጫዎች መካከለ ያለው አፈና

ብዙዎች ገዢው ፓርቲ ምርጫውን የሚያሸንፈው ገና ምርጫው ከመካሄዱ በፊት፣ በምርጫዎች መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ተቃዋሚዎችን በማዳከም እንደሆነ ይገልጻሉ። ተቃዋሚዎች አባላትን ለመመልመል፣ ከሕዝብ ጋር ለመወያየትና ሕዝባዊ መሠረት ለመገንባት የሚያስችሉ የአደባባይ ስብሰባዎችን እንዳያደርጉ በመንግሥት መዋቅሮች በኩል ክልከላ ይደረግባቸዋል።

ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣም ይሄው የአፈና ጫና እንደሚጠናከር ማሳያዎች አሉ። በ2017 ዓ.ም. የደኅንነት ስጋትን ሽፋን በማድረግ የተወሰኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ በጊዜያዊነት መሠረዙ፣ የዋዜማ ሬዲዮ እና የአዲስ ስታንዳርድ ፈቃድ መሰረዝ፣ እንዲሁም የሮይተርስ እና ዶቸ ቨለ ዘጋቢዎች ፈቃድ መታገድ የዚሁ ምኅዳሩን የማጥበብ ሂደት አካል መሆኑ ይነገራል። እንደ ቢቢሲ አማርኛ ያሉ ሚዲያዎችም ዘጋቢዎቻቸው የምርጫ ዘገባ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ባጆች ከምርጫ ቦርድ ማግኘት አልቻሉም።

በቅርቡ በተጠናቀቀው የ2018 ዓ.ም. የቅድመ-ምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም፣ የመንግሥት የታችኛው መዋቅር አባላት እና ካድሬዎች ገዢው ፓርቲ ጠንካራ ፉክክር ባለባቸው ወረዳዎች የተቃዋሚዎችን የቅስቀሳ መርሃ-ግብሮች በተደራጀ ሁኔታ በማስተጓጎል፣ ስታዲየሞችን እና አዳራሾችን በጸጥታ ሰበብ እንዳይጠቀሙ የማደናቀፍ መዋቅራዊ ጫናዎችን በይፋ ፈጽመዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም፣ በተለይም በገጠር ቀበሌዎች የሚገኙ የአካባቢ ሚሊሻዎችና አመራሮች ገና ምርጫው ሳይደርስ በቅስቀሳው ወቅት “ከገዢው ፓርቲ ውጪ ሌላ አማራጭ መምረጥ መዘዙ ከባድ ነው” የሚሉ የማስፈራሪያ መልዕክቶችን በማሰራጨት፣ በመራጩ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ የስነ-ልቦና ወከባ እና የደኅንነት ስጋት አስቀድመው በመዝራት የቅድመ-ምርጫ ምኅዳሩን አጥበውታል።

የፋይናንስ ምንጭ ድርቀት

ሌላው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የምርጫ ቅስቀሳ የማድረግ አቅማቸውን በከፍተኛ ደረጃ የገደበው መዋቅራዊ ፈተና የፋይናንስ እጥረት ነው። በፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ ምክንያት አቅሙ ያላቸው የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ለተቃዋሚዎች የገንዘብ ድጋፍ የመስጠት ልምድ የሌላቸው ሲሆን፣ አቶ አንዱዓለም አራጌ እንደሚሉት ፖለቲካው ለቀቅ ቢደረግና ሰው ባይፈራ ሕዝቡ ድጋፍ ከመስጠት ወደኋላ እንደማይል የምርጫ 97 የታየውን የቅንጅት ያሳያል።

በአሁኑ ወቅት ግን ተቃዋሚዎች የራሳቸውን ወጪ መሸፈን ባለመቻላቸው ከምርጫ ቦርድ በሚሰጠው ውስን በጀት እና በውጭ ሀገር በሚኖረው የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ስጦታዎች ላይ ጥገኛ ሆነዋል። ይሁን እንጂ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያደርገው የዳያስፖራ ኮሚኒቲ በተለይ በአሁኑ ወቅት የገንዘብና የሞራል ድጋፉን በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ የሀገር ውስጥ ፓርቲዎች ይልቅ የትጥቅ ትግልን ወደ መደገፍ ማዞሩ፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲያገልሉ በጽኑ መፈለጉ የተቃዋሚዎችን የፋይናንስ ምንጭ ይበልጥ አድርቆታል።

ዶ/ር ወልደማርያም ልሳኑ የገንዘብ አጠቃቀሙን ፍፁም ኢፍትሐዊነት ሲያስረዱ፣ ገዢው ፓርቲ በአንድ ወረዳ ላይ ኢንቨስት የሚያደርገው ገንዘብ ተቃዋሚዎች ለ180 ምርጫ ክልል ውድድር ከሚያገኙት ጋር እንደሚመጣጠን ገልጸዋል። “እነሱ በሁሉም ጣቢያ ላይ በሬ አርደው የራሳቸውን መራጭ፣ ታዛቢና አስፈጻሚ ይመግባሉ… ታዛቢው በገንዘብ ሃይጃክድ (Hijacked) ሆኗል፣ ምርጫው ሄዷል” በማለት የሕዝብ ሀብት (Public Resource) ለፓርቲ ቅስቀሳ መዋሉን ይተቻሉ።

የተቃዋሚዎች ውስጣዊ ድክመት

የተቃዋሚዎች ማሸነፍ አለመቻል ከመንግሥት ጫና ባሻገር ከራሳቸው የውስጥ አንድነትና የስትራቴጂ ክፍተት ጋር የተያያዘ መሆኑን የዘንድሮው የ”ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” ፍጥጫ ትልቅ ማሳያ ነው። ጥምረቱ በምርጫው ማግስት “አንገባም” የሚል ውሳኔ ቢያስተላልፍም፣ በውስጡ ያሉ አሸናፊ ዕጩዎች እና የፓርቲው ፕሬዚዳንት ሳይቀሩ ውሳኔውን አጣጥለውታል። ይህ የሚያሳየው ተቃዋሚዎች የጋራ የፖለቲካ ግብና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ እንደሌላቸው ነው።

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሶሻሊስት ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በውስጥ ክፍፍል ሳቢያ ዕጩዎቹ የተሰረዙበት ሲሆን፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲም ከነውስጣዊ ክፍፍሉ ነበር ወደ ምርጫ የገባው።

አቶ አንዱዓለም እንደሚሉት፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ሥልጣን ወዳድ ከመሆናቸው ባሻገር ሌላ የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው ለጥቅማ ጥቅሞች መሯሯጣቸው የውስጥ ልዩነት ይፈጥራል። በተጨማሪም በገዢው ፓርቲ በኩል በገንዘብ የመደለልና “የውስጥ አርበኛ” የማድረግ፣ ወይም በደኅንነቶች በኩል የመግደልና የማሰር ማስፈራሪያዎች መኖራቸው ተቃዋሚዎችን ከውስጥ ይበታትናል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ስትራቴጂ ሁልጊዜም “ምርጫውን ማሸነፍ” ሳይሆን “የሂደቱን ጉድለት ማሳየት” ላይ ብቻ ያተኮረ ነው የሚለውን ወቀሳ በተመለከተ አቶ አንዱዓለም ሲመልሱ፣ “በተወሰነ ደረጃ እውነትነት አለው፣ ሁልጊዜ ግን አይደለም” ይላሉ። ፍርድ ቤት እና ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ባልሆኑበት፣ እንዲሁም በአገዛዙ ፈርጣማ እጅ ተወጥሮ በተያዘ ሥርዓት ውስጥ “እንዴት ነው አሸንፋለሁ ብለህ የምትነሳው?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

ከምርጫ 97 በኋላ “ፓርላማ አንገባም/ውጤት አንቀበልም” የሚለውን አዙሪት በተመለከተም፣ በ1997 ዓ.ም. ቅንጅት ለኢትዮጵያ አንድነት ፓርላማ ላለመግባት ያሳለፈው ውሳኔ ትክክል እንደነበረና “ትክክለኛ እና ፍትሐዊ ምርጫ የማይደረግ ከሆነ ማቋረጥ እምቢ ማለት አለብን… ትክክል ካልሆነ ለምን ትቀበላለህ? ለምንድን ነው የሕዝብ ድምፅ ተዘርፎ ከሌባ ጋር የምትተባበረው?” ሲሉ ምርጫው ድራማ እስከሆነ ድረስ አለመቀበል ትክክለኛ የፖለቲካ መከራከሪያ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ሌላው በኢትዮጵያ የሥልጣን ሽግግርን አስቸጋሪ የሚያደርገው መዋቅራዊ ጉዳይ የሀብት እጥረት መሆኑን ዶ/ር ወልደማርያም ያነሳሉ። “በጣም scarce [ውሱን] የሆነ resource [ሀብት] ባለበት ሀገር ላይ ሥልጣን መያዝ ማለት ያቺን ሪሶርስ የበላይነት ይዞ ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት ስለሆነ… ወደ ሥልጣን የመጣ አካል ያንን ሥልጣን ፈቅዶ ማስተላለፍ አልተለመደም” ይላሉ።

ዶ/ር ወልደማርያም የፖለቲካ ምኅዳሩን መሻሻል በተመለከተ ተስፋ አስቆራጭ ማሳያ ነው ያሉትን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የ25 ዓመት ዕቅድ ይጠቅሳሉ። “አሜሪካ ላይ ሪፐብሊካን እና ዲሞክራቶች በሚያደርጉት ውድድር ውስጥ ቢበዛ ዕቅድ የሚያወጡት የአምስት ዓመት ነው። ኢትዮጵያ ላይ አሁን ገዢ ፓርቲ ዛሬ ዲስክሎዝ ያደረገው ዕቅድ የ25 ዓመት ዕቅድ ነው። ይህ ማለት by default (በተዘዋዋሪ) ሥልጣን በቀላሉ ለየትኛውም አካል ማስረከብ የማይቻል ነው ተብሎ የሚታሰብ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው” ሲሉ ትንታኔያቸውን ይቋጫሉ።

ለወደፊቱ ፍትሐዊ ምርጫ እንዲደረግ ግን የፍትህ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው መዋቀር እንዳለባቸው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በታዛቢነት መገኘት እንዳለበት፣ ፓርቲ እና አገር መለየት እንዳለባቸውና በጋራ ቁጭ ተብሎ የጋራ ቃልኪዳን መፈረም እንዳለበት ፖለቲከኞቹ ይመክራሉ። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)