ብልፅግና ፓርቲ ለተቃዋሚዎች 15 በመቶ የምርጫ ክልሎችን ትቶ ለመወዳደር ከ6 ወራት በፊት ወስኖ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ

ገዢው ብልፅግና ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ከ85 በመቶ በላይ በሆኑ የምርጫ ወንበሮች ላይ ሙሉ በሙሉ ላለመወዳደር እና ቀሪዎቹን 15 በመቶ መቀመጫዎች ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ ለመተው ከስድስት ወራት በፊት ውሳኔ አሳልፎ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያረጋገጡት በ6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምርጫው ዙሪያ ባደረጉት ማብራሪያ፣ “በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የምርጫ ታሪክ፣ ምናልባትም ዴሞክራሲ ከእኛ ወዲያ ለሚሉ ሀገራትም ቢሆኑ አድርገው በማያውቁት ልክ፣ የብልፅግና ፓርቲ ከስድስት ወራት በፊት ይህንን ምርጫ በሚመለከት በነበረን ውይይት፣ ብልፅግና ከ85 ፐርሰንት ባለፈው ወንበር አይወዳደርም” ብለዋል።

ውሳኔው በተግባር የተፈጸመው “15 ፐርሰንቱን ሙሉ በሙሉ የሚፎካከሩ ፓርቲዎች በነፃነት፣ incumbent [ተቀማጩ] መንግሥት በሌለበት፣ ተጭበረበረ ወይም ደግሞ መንግሥት በኃይል ወሰደው በማይሉበት ሁኔታ ብቻቸውን ይወዳደሩ” በሚል መነሻ እንደነበር አስረድተዋል።

ይህንን ያልተለመደ ውሳኔ ለማሳለፍ በፓርቲው ውስጥ ጥብቅ ክርክር እንደነበር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ለዲሞክራሲ ቀናይነት ሲባል የብልፅግና ፓርቲ አባላት ያኔ የጎረበጣቸው ቢመስላቸውም አብረን ወስነናል፤ ይኼ ዓይነቱ አካሄድና ውሳኔ በደፈናው አፍሪካ መኖሩን እጠራጠራለሁ፣ በእኛ ሁኔታ ታይቶ አይታወቅም” ሲሉ አክለዋል። በጥቅሉ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የሕዝብ ይሁንታ በግልጽ የታየበት ምርጫ ተከናውኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ምን አልባት ማለፍ ሲገባቸው የቀሩ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ብልፅግና ፓርቲ 15 በመቶ የሚሆኑ ወንበሮችን ለተቃዋሚዎች መልቀቁን ይናገሩ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወደ ድምፅ መስጫ ወረቀቶች ሕትመት የተላኩ የዕጩዎች ዝርዝር እንደሚያሳየው፣ ከ509 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮች ውስጥ በ48ቱ (9 በመቶ) እና ከ2,764 የክልል ምክር ቤቶች ወንበሮች ውስጥ በ284ቱ (10 በመቶ) ላይ ዕጩ ሳያቀርብ ቀርቷል። ፓርቲው ለኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት 1 በመቶ (5 ወንበሮችን) ብቻ ክፍት ሲያደርግ፤ በአንጻሩ ለአዲስ አበባ፣ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ለድሬዳዋ እና ለሶማሌ ምክር ቤቶች እስከ 15 በመቶ የሚሆኑ መቀመጫዎችን ለተቃዋሚዎች ትቶ አልተወዳደረባቸውም።

የዘንድሮው ምርጫ በርካታ ድምፆች እንዲሰሙ ዕድል የፈጠረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በሂደቱ ላይ የነበሩትን ከባድ የጸጥታ ፈተናዎችም አልሸሸጉም። “ምርጫ የማይወዱ ኃይሎች የእኛን ባንዳዎች ልከው ምርጫው እንዳይከናወን እንደ አንድ ታርጌት ወስደው ሰርተውበታል” ብለዋል። የሀገሪቱ ዜጎች ግን ጥይት እየተተኮሰባቸው ሳይደነግጡ ሌሊት ወጥተው መርጠዋል ብለዋል።

የዘንድሮው ምርጫ የኢትዮጵያን ሕዝብ ውስብስብ የረጅም ዘመናት ድልብ ሀብትና በቀላሉ ሊታወቅ የማይችል ጥልቅ ማንነት ያሳየ ነው ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሕዝቡ “አትመዝገቡ፣ አትደግፉ፣ አትምረጡ” ተብሎ የተጋረጡበትን እገዳዎችና ማስፈራሪያዎች ሁሉ ወደ ጎን በመተው፣ አረጋውያን፣ በሽተኞች፣ እናቶች ልጆቻቸውን አዝለው እንዲሁም ኃዘንተኞች ከማዕዳቸው ተነስተው ከ50 ሺሕ በላይ በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያሳዩትን ታላቅ አገራዊ ተጋድሎ መንግሥት እንደ ታላቅ አደራና “በታላቅ ሸክም” የሚመለከተው ነው ብለዋል።

ሕዝቡ ለገዢው ፓርቲ የሰጠው አደራ ቀላል አይደለም የሚለውን ሲገልጹ፣ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ባዶ ቼክ ነው የሰጠን፤ በዚህ ቼክ ላይ መልካም ስም፣ መልካም ሥራ መዝራት የሁላችንም ኃላፊነት ይሆናል። ይህንን ቼክ በአግባቡ ሳንጠቀም ካበላሸነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥይት ሳይፈራ እንደመረጠው፣ ጥይት ሳይፈራ የተቃውሞ እርምጃ መውሰድ ይችላል” ሲሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት አምስት ዓመታት በምክር ቤቱ ውስጥ የሕዝብን ድምፅ ሲያሰሙ ለነበሩት “እንደ ክቡር አቶ ባርጤማ ፈቃዱ እና የኢዜማ አባላት፣ ክቡር አቶ ደሳለኝ ጫኔ እና የአብን አባላት፣ እንዲሁም ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ እና ለሌሎችም የግል ተወዳዳሪዎች” በሙሉ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

በአዲሱ ምክር ቤት የማይቀጥሉ የፓርላማ አባላትንም በተመለከተም፣ “ከምክር ቤት ውጭ እነዚህ አባላት ከመንግሥታችን ጋር በጋራ ሆነን ኢትዮጵያን እንድናገለግል በተከበረው ምክር ቤት ፊት ጥሪ ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ፤ መንግሥታችን እናንተን አካቶ ኢትዮጵያን ማልማት ይፈልጋል” ሲሉ ተቃዋሚዎችን ያካተተ የአብሮነት የሥራ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የሁለት የስልጣን ዘመን (Term Limit) አጀንዳ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ ብልፅግና ፓርቲ በቀጣዩ የሀገራዊ ምክክር መድረክ (Inclusive National Dialogue) ላይ ይዞት የሚቀርበውን ትልቅ መዋቅራዊ አጀንዳ ይፋ አድርገዋል። “በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት ማክሲመም ሁለት ተርም (term) ብቻ መቆየት አለበት የሚል አጀንዳ ብልፅግና ይዞ ይቀርባል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአፍሪካ ደረጃ ሕገ-መንግሥት አሻሽለው ዕድሜ ሲያራዝሙ እንጂ፣ ያልተገደበ ዕድሜ እያላቸው የሥልጣን ዘመንን ለመገደብ የወሰነ ገዢ ፓርቲ ሰምተው እንደማያውቁና ይህም ለሀገር የሚጣል ትልቅ መሠረት በመሆኑ የፓርቲው አባላት ሊኮሩበት እንደሚገባ ገልጸዋል። (ምርጫ 2018  – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)