ከምርጫ ካርድ ነጠቃ እስከ ታዛቢዎች ድብደባ፤ፓርቲዎች በአንዳንድ ምርጫ ክልሎች ድጋሚ ምርጫ የጠየቁባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. አጠቃላይ የምርጫ ውጤት ይፋ ባደረገበት ዕለት፣ በበርካታ የምርጫ ክልሎች ላይ ድጋሚ የድምፅ ቆጠራ እና ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑን ማስታወቁ ይታወሳል። የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ንዋይ ይፋ ያደረጉትን ይህንን ውሳኔ ተከትሎ፣ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)፣ የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሕብር) እና የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ዎሕነን) አመራሮች በምርጫ አስፈጻሚዎችና በአካባቢው የመንግሥት መዋቅሮች የተፈጸሙ መሠረታዊ የሕግና የሥነ ምግባር ጥሰቶች ለውሳኔው ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በ10 የምርጫ ክልሎች ማለትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል (ብርብራ፣ ገረሴ እና ዳሞት ወይዴ 2)፣ በሲዳማ ክልል (ሀገረ ሰላም እና ጩኮ)፣ በኦሮሚያ ክልል (ወልመራ፣ ክብረ መንግሥት እና አሊቦ)፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልል (ቀላፎ) የምርጫ ክልሎች ላይ ድጋሚ የድምፅ ቆጠራ ይደረጋል።

ለክልል ምክር ቤት ደግሞ በኦሮሚያ (ክብረ መንግሥት)፣ በሶማሌ (ሐርሺም)፣ በአፋር (አሚባራ) እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ (ሃላባ 1) የምርጫ ክልሎች ድጋሚ ቆጠራ ይካሄዳል።

በሌላ በኩል ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ተሰርዞ ድጋሚ ምርጫ የሚካሄድባቸው የፓርላማ ወንበሮች በሲዳማ (አራሬሳ)፣ በኦሮሚያ (ቤጉ እና ባቱ ዝዋይ)፣ እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ (ሶሮ 1 እና ጠንባሮ) ይገኛሉ። ለክልል ምክር ቤት ድጋሚ ምርጫ ከሚደረግባቸው 7 ቦታዎች መካከል 6ቱ በሶማሌ ክልል (ሐርገሌ፣ ዳሮር፣ ሐዲጋላ፣ አዋሬ እና ዳራቶሌ) ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ በደቡብ ኢትዮጵያ (ጨንቻ) እና በኦሮሚያ (ቤጉ እና ባቱ ዝዋይ) መሆናቸው ታውቋል።

በሲዳማ ክልል ጩኮ እና ሀገረ ሰላም የምርጫ ክልሎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው ምርጫ ላይ አቤቱታ ያቀረበው የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) የሲዳማ ክልል አስተባባሪ አቶ ታደለ ታኔ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፣ በምርጫው ዕለት በክልል ምክር ቤት የመምረጫ ወረቀት ላይ የፓርቲያቸው የ9 ዕጩዎች ስም ዝርዝርና ምልክት አለመኖሩን አረጋግጠዋል።

ጉዳዩን ወዲያውኑ ለቦርዱ ቢያሳውቁም፣ የቦርዱ ተወካይ ችግሩ ከ4 ሰዓታት በኋላ መስተካከሉን ቢገልጽላቸውም፣ በወቅቱ ግማሹ መራጭ ድምፅ ሰጥቶ ከሄደ በኋላ በመሆኑና ከነእፓ ውጪ የሌሎች ፓርቲዎች ምልክቶች በሙሉ በሰነዱ ላይ የነበሩ በመሆኑ ሂደቱ ፍትሐዊ እንዳልነበር ጠቅሰዋል።

አስተባባሪው አክለውም፣ በዕለቱ ምሽት ቆጠራ ሲጀመር “ወንዶ በር ጩኮ” ምርጫ ጣቢያ ላይ የነበሩ የፓርቲያቸው ሁለት ታዛቢዎች “ይመሽባችኋል፣ በጊዜ ሂዱ” በሚል በአስፈጻሚዎች ተገፍተው እንዲባረሩ መደረጉንና ቆጠራው ታዛቢ በሌለበት መከናወኑን ከሰዋል።

አቶ ታደለ አሁን ላይ ማዕከል መጥቶ እየተደረገ ስላለው ድጋሚ ቆጠራ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸውና ወደ አዲስ አበባም ታዛቢ እንዳልላኩ ገልጸዋል። በዚህ የምርጫ ክልል ላይ የሕዳሴ ፓርቲም አቤቱታ ማቅረቡ የተረጋገጠ ሲሆን፣ የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በበኩሉ አቤቱታው በማን እንደቀረበ ባያውቅም ቦርዱ ውሳኔውን በፍጥነት እንዲያሳውቀው እየጠየቀ ይገኛል።

የዎላይታ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ዎሕነን) ፕሬዝዳንት ዶ/ር ወልደማርያም ልሳኑ፣ ቦርዱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዳሞት ወይዴ 2 ምርጫ ክልል ላይ ድጋሚ ቆጠራ ብቻ እንዲደረግ ማዘዙን አጥብቀው ተቃውመዋል። ዶ/ር ወልደማርያም “እኛ ድጋሚ ድምፅ ቆጠራ አልጠየቅንም፤ የፓርቲያችን ጥያቄ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት የተፈጸመባቸው 5 የምርጫ ክልሎች ምርጫው ሙሉ በሙሉ ውድቅ ሆኖ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ የሚል ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ እንደሚያስረዱት፣ በዳሞት ጋሌ 1፣ በዳሞት ወይዴ 2፣ በሶዶ ዙሪያ 1፣ በኩንዶ ኮይሻ 1 እና በሁንዶ ጠበላ ምርጫ ክልሎች ከገጠር የሚመጡ መራጮች “በራሳችሁ መምረጥ አትችሉም” በሚል የምርጫ ካርዳቸው በአስፈጻሚዎች ተነጥቆ ለብልፅግና ፓርቲ ካድሬዎች ተሰጥቷል፤ እንዲሁም በዕለቱ ታዛቢዎቻቸው ከጣቢያ ተባረው ድምፅ ተቀይሯል።

በመሆኑም ቦርዱ ሌሎቹን አካባቢዎች ትቶ በዳሞት ወይዴ 2 ላይ ድጋሚ ቆጠራ ብቻ ለመሥራት የወሰነው ውሳኔ ተገቢ ባለመሆኑና ስላሳዘናቸው፣ ጉዳዩን በድጋሚ በመቃወም ለቦርዱ አቤቱታ አስገብተው ምላሽ እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዳሞት ወይዴ 2 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በጨንቻ የክልል ምክር ቤት ውድድር ላይ አቤቱታ ያቀረበው የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አበራ በቀለ፣ በዳሞት ወይዴ 2 ዎሕነን፣ ብልፅግና፣ ነእፓ እና ሕብር ኢትዮጵያ መወዳደራቸውን ጠቅሰው፣ ክስ የቀረበው ምርጫ አስፈጻሚዎች በድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ ስርዝ ድልዝ በማብዛት ውጤቱን የማቀያየር ሥራ በመሥራታቸው ነው ብለዋል። አቶ አበራ አሁን ላይ ቆጠራው በማዕከል እየተደረገ ቢሆንም፣ የምርጫ ኮሮጆዎቹ ከክልል ወደ ማዕከል ሲመጡ በተደረገው አያያዝና ርክክብ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ፓርቲው በጨንቻ ምርጫ ክልል ምርጫው በድጋሚ እንዲደረግ የተገደደበትን ምክንያት ሲያስረዱም፣ በዕለቱ የፓርቲው ታዛቢዎች መደብደባቸውን፣ እንዲሁም ያልታወቁ ሰዎችን በከባድ መኪና ጭኖ በማምጣት በተደጋጋሚ እንዲመርጡ የማድረግ መዋቅራዊ ጥሰት እንደነበር አክለዋል።

አቶ አበራ ፓርቲያቸው በጎፋ ምርጫ ክልልም ተመሳሳይ አቤቱታ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ቦርዱ ውድቅ ማድረጉን ጠቅሰው፣ “አስፈጻሚዎች መራጮች የት ላይ መምረጥ እንዳለባቸው ድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ እየጠቆሙ የማሳየት ሕገወጥ አሠራር በጎፋም የነበረ ቢሆንም፣ ቦርዱ ሊቀበለው አልቻለም” ብለዋል።

ካድሬዎች በጣቢያዎች ቆመው ለብልፅግና እና ገዢው ፓርቲ ለሚደግፋቸው ሌሎች ፓርቲዎች ድምፅ እንዲሰጥ ሲያስገድዱ እንደነበርና ሕብር ኢትዮጵያ እንዲያሸንፍ ባለመፈለጋቸው በመሆኑ ከፍተኛ ወከባ እንደደረሰባቸው አቶ አበራ በጥሬው ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል ባቱ ዝዋይ፣ ክብረ መንግሥት፣ አሊቦ እና ወልመራ ምርጫ ክልሎች ውስጥ አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ኦነግ እና ሕዳሴ ፓርቲ የተወዳደሩ ሲሆን፤ በወልመራ ምርጫ ክልል ከተወዳደሩት መካከል የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል አስተባባሪ አቶ ኡመር ጎበና ሂደቱን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ኡመር በወቅቱ የደረሰውን ጥሰት በቃል ለጣቢያ ኃላፊዎች ማሳወቃቸውንና ሌሎች ሁለት ፓርቲዎች ደግሞ በጽሑፍ ለቦርዱ አቤቱታ ማቅረባቸውን ገልጸው፣ “የአካባቢው ሚሊሻ እና የታችኛው የመንግሥት መዋቅር አባላት በኃይል ተጠቅመው መራጮች አንድን ፓርቲ ብቻ እንዲመርጡ ከፍተኛ ጫና አሳድረዋል” ብለዋል።

ምርጫውን በከፍተኛ የስነ-ልቦና እና የአካል ጫና ውስጥ ሆነው ማከናወናቸውን የገለጹት አቶ ኡመር፣ ቦርዱ ድጋሚ ምርጫው መቼ እንደሚካሄድ እስካሁን የሰጣቸው ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለ አረጋግጠዋል። “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተነሱት በእነዚህ መዋቅራዊ የሕግ ጥሰት ቅሬታዎች ላይ ከምርጫ ቦርድ በኩል ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም እስካሁን አልተሳካላትም። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)