ሰባተኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ተከትሎ በትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ስም የምክር ቤት መቀመጫ ያሸነፉ ዕጩዎች ወደ ምክር ቤት አይገቡም መባሉን እና “እርምጃ ይወሰዳል” የሚለውን መግለጫ የትብብሩ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ እና አንድ በውድሩ ያሸነፉ ዕጩ መቃወማቸውን ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ።
የትብብሩ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ “ማንም ሰው ድምፅ አግኝቻለሁ ብሎ ምክር ቤት ቢገባ መከልከል አንችልም፤ ዕጩዎችን እንዳትገቡ ማለትም ሆነ የዲሲፕሊን እርምጃ መውሰድን በትብብሩ ምክር ቤት አልተመከረበትም” ሲሉ የውስጥ መከፋፈል መኖሩን ፍንጭ ሰጥተዋል።
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የዘንድሮው ምርጫ “ዴሞክራሲን አያዋልድ፣ መፍትሔም አይፈይድ” ሲል በጽኑ የኮነነ ሲሆን፣ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ማንኛውም ዕጩ በትብብሩ ስም ወደ ምክር ቤት ቢገባ ፍጹም ተቀባይነት እንደማይኖረው አስታውቆ ነበር።
የትብብሩ ዋና ጸሐፊ ምሥጢረ ሥላሴ ታምራት በቅርቡ ከ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ይህንን የትብብሩን ውሳኔ ሳይቀበሉ ወደ ምክር ቤት የሚገቡ ዕጩዎችን ትብብሩ ዕውቅና እንደማይሰጥ ገልጸው፣ “በዚህ ምርጫ ለተመሠረተ ፓርላማ መግባት በሀገሪቱ ለሚፈጠሩ ምስቅልቅሎች ዕውቅና መስጠት በመሆኑ ይህንን አንቀበለውም። የትብብሩን አቋም ተላልፎ ወደ ምክር ቤት እገባለሁ የሚል ካለ የምንቀበለው አይደለም፤ የዲሲፕሊን ዕርምጃም በትብብሩ ውስጥ የምንወስድ ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የትብብሩ የሥራ አስፈጻሚ አባል በበኩላቸው ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት፣ በትብብሩ ውስጥ የፖለቲካ ውሳኔ መስጠት የሚችሉት የሥራ አስፈጻሚ አባላት በመሆናቸው የምክር ቤት መግባት አለመግባትም ሆነ ሌሎች ውሳኔዎችን አስፈጻሚ ኮሚቴው የምክር ቤቱን ውሳኔ ሳይጠብቅ መወሰን ይችላል።
እኚሁ አመራር ሲያስረዱም፣ ከእያንዳንዱ ፓርቲ ሁለት ሁለት አመራሮች ተውጣጥተው ይህንን ውሳኔ የወሰኑ ሲሆን፣ ውሳኔውም በምርጫው ወቅት 90 በመቶ የሚሆን ታዛቢ በመመደብ በተገኙ ተጨባጭ የምርጫ ጥሰቶች ላይ ተመርኩዞ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ይህንን መዋቅራዊ አቋም በግልጽ የተቃወሙት የትብብሩ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ፣ መጀመሪያ ዕውቅና ባልሰጡት ምርጫ ላይ “ግቡ አትግቡ” የሚል አተካራ ውስጥ መግባት እንደማያስፈልግ ገልጸው፣ የትብብሩ ምክር ቤት ከተሰበሰበ ሁለት ወራት ያለፉት በመሆኑ በዚህ ዙሪያ የወሰነው ምንም ዓይነት ውሳኔ አለመኖሩን አስታውቀዋል።
“ዲሲፕሊን” የሚለውን ዛቻ በተመለከተም ሲያስረዱ፣ ትብብሩ የተመሠረተው ጊዜያዊ ጉዳይን ለማስፈጸም በመሆኑ ከላይ እስከ ታች ያለ የተዋቀረ መዋቅር እንደሌለውና የዲሲፕሊን እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን የጥምረቱ ሳይሆን የስምምነት ጥሰቶችን አይቶ እርምጃ መውሰድ የሚችለው የእያንዳንዱ ፓርቲ መዋቅር ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በትብብሩ ስም በአዲስ አበባ ምክር ቤት የጉለሌ ምርጫ ክልል ወንበር ያሸነፉት የመኢአድ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊና የትብብሩ ምክር ቤት አባል አቶ ሙሉጌታ አበበ በበኩላቸው፣ በትብብሩ ስም “እርምጃ ይወሰዳል” የሚለው ወሬ መሠረተ ቢስና የማኅበራዊ ሚዲያ የግለሰቦች አቋም እንጂ የፓርቲ ውሳኔ አይደለም ሲሉ አጣጥለውታል።
አቶ ሙሉጌታ “የእኔ አቋም እገባለሁ አልገባም የሚል አይደለም፤ በራሴ ላይ የመወሰን ሥልጣን የለኝም። ሕዝብ አምኖብኝ ኃላፊነቱን ሰጥቶኛል፣ ይህንን እኔም እምቢ የማለት ሥልጣን የለኝም” ካሉ በኋላ፣ ምክር ቤት አንገባም የሚለው አካሄድ ከ20 ዓመታት በፊት የነበረ ያረጀ ያፈጀና የማያወጣ አካሄድ ነው ብለዋል።
በትብብሩ ውስጥ መከፋፈል አለ ወይ ለሚለው ጥያቄም “በትብብሩ መካከል መከፋፈል የለም፣ ይልቅስ ችኩልነት አለ” ሲሉ ምላሽ የሰጡት አቶ ሙሉጌታ፣ ትብብሩን በመወከል ቢወዳደሩም ሁሉንም የምክር ቤት መቀመጫዎች ያሸነፉት ግን የመኢአድ አባላት መሆናቸውን በይፋ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ትብብሩ 2 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና 6 የክልሎችም ምክር ቤቶች መቀመጫዎችን አሸንፏል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ትብብሩን በመወከል በጉለሌ ምርጫ ክልል 24 የተወዳደሩት አቶ ሙሉጌታ አበበ 152 ሺህ 315 መራጮች በተመዘገቡበት የምርጫ ክልል 24 ሺህ 476 ድምፅ በማግኘት የአዲስ አበባ ምክር ቤት መቀመጫን አሸንፈዋል።
በአንጻሩ በዚህ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወዳደሩት ታዋቂው ዕጩ ዶ/ር አበባው ደሳለው 6,087 ድምፅ ብቻ በማስመዝገብ ሳያሸነፉ ቀርተዋል። በተመሳሳይ በልደታ ምርጫ ክልል ከተመዘገቡት መራጮች መካከል ወይዘሮ አታለለች በኃይሉ የተባሉ የመኢአድ አባል 14 ሺህ 271 ድምፅ በማግኘት ሌላኛውን የአዲስ አበባ ምክር ቤት መቀመጫ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን፣ በዚህ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወዳድረው የነበሩት የትብብሩ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ጌጡ ግን ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የትብብሩን መተዳደሪያ ደንብ ተመልክታ እንዳረጋገጠችው፣ ጳጉሜ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. በወጣው በአምስቱ ፓርቲዎች መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 10 ንዑስ አንቀፅ 10.1 ላይ “ምክር ቤቱ የቅንጅቱ የመጨረሻው ወሳኝ አካል ይሆናል” ይላል።
በአንቀፅ 11 የቅንጅቱ ሥራ አስፈፃሚ ተግባርና ኃላፊነት በተመለከተው ንዑስ አንቀፅ 11.6 ላይ ደግሞ የሥራ አስፈጻሚው ተግባር ቅንጅቱን በሚመለከት በማናቸውም ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ “ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ” ብቻ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል።
የዲሲፕሊን ጉዳይን በተመለከተም ደንቡ ላይ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ አባላትን ለየፓርቲዎቻቸው ኃላፊዎችና ለምክር ቤቱ በማሳወቅ “ውሳኔ እንዲሰጥበት ያደርጋል” ከሚል ውጭ፣ ሥራ አስፈጻሚው ራሱ በቀጥታ ውሳኔ የመስጠትም ሆነ አባላትን የመቅጣት ሕጋዊ ሥልጣን እንደሌለው ሰነዱ ያረጋግጣል።
መስከረም 2018 ዓ.ም. የተመሠረተው ይህ ጥምረት፤ አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ የመሠረቱት ቅንጅት ነበር። መስራቾቹም፦ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፤ እናት ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፤ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ (አግን) ነበሩ። ይሁን እንጂ ምክንያቱ በይፋ ባልተገለጸ ሁኔታ ቅንጅቱ “አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን” ከመካከሉ በመቀነስ፣ ጥምረቱ በአራት ፓርቲዎች ብቻ ሆኖ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ተወዳዳሪ ሆኖ ቀርቧል።
የምርጫውን መጠናቀቅ ተከትሎ ከትብብሩ መሥራች ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የአማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ ፕሬዚዳንት የሆኑት እና በትብብሩ ውስጥ “የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ” መሆናቸው የተጠቀሱት አቶ ምርጫው ስንሻው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ “7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ ትልቅነቱን፣ ሰላም ወዳድነቱንና አሸናፊነቱን ያረጋገጠበት ነው” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሰላማዊ ሽግግር እንዲኖር ትብብሩ ጥረት ማድረጉንና “በምርጫው በሰላም የምንታገል ኃይሎች መሆናችንን ለዓለም ማሳየት ችለናል” ሲሉ ምልከታቸውን ሰጥተው ነበር።
ይህንን የአቶ ምርጫው አስተያየት ተከትሎ በትብብሩ ስም በወጣው መግለጫ “ከሰሞኑ የትብብሩ አመራር በመምሰል የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ ነኝ በሚል፣ በተግባርም በአስተዋጽዖም የማናውቀው ግለሰብ እንዲኽና እንዲያ አለ የሚል ውርውር ሲል ታዝበናል፤ እነዚህ የብፌ ፖለቲከኛና የሳይበሩ ሸኔ ትንኮሳ የዝኾን ጆሮ ላይ ያረፈ ዝንብ ናቸው” ሲል በስሙ የተላለፈውን መልዕክት አጣጥሎት ነበር።
አሁን የመኢአድ አባላት ከሆኑት የትብበሩ አካላት የቅንጅቱ የሥራ አስፈፃሚዎች ንግግር ላይ የተነሳው አቤቱታ፣ ትብብሩ ላይቀጥል እንደሚችል አመላካች ሆኗል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




