የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የግል ዕጩዎች ብልፅግና ፓርቲ ካልተወዳደረባቸው የምክር ቤት ወንበሮች ውጪ ምን ያህሉን አገኙ?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትናንት ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው አጠቃላይ የምርጫ ውጤት መሠረት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች በድምሩ 48 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (የፓርላማ) እና 271 የክልል ምክር ቤቶች ወንበሮችን ማሸነፋቸው ታውቋል።

ምንም እንኳ አጠቃላይ የምርጫው ውጤት በብዙዎች እንደተጠበቀው በገዢው ብልፅግና ፓርቲ ሰፊ የበላይነት የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ ተቃዋሚዎች እና የግል ዕጩዎች በጠንካራ ፉክክር ለፓርላማ 4 ወንበሮችን፣ ለክልሎች ምክር ቤቶች ደግሞ 6 ወንበሮችን በቀጥታ ከብልፅግና ፓርቲ መንጠቅ ችለዋል።

በምርጫው ሂደት ተቃዋሚዎች ወይም የግል ዕጩዎች ካሸነፏቸው ወንበሮች መካከል አብዛኛዎቹ ብልፅግና ፓርቲ ዕጩ ያላቀረበባቸው (ያልተወዳደረባቸው) ቦታዎች ናቸው። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብልፅግና ያላቀረበው በ48 የምርጫ ክልሎች ላይ የነበረ ቢሆንም፣ በአማራ ክልል በሚገኙ ስምንት የምርጫ ክልሎች ላይ በተፈጠሩ ሁኔታዎች ምርጫው ባለመካሄዱ ምክንያት 3ቱ ብልፅግና የለቀቃቸው ወንበሮች ታጥፈው፤ በአጠቃላይ ብልፅግና ዕጩ ያላቀረበባቸው የፓርላማ ወንበሮች ቁጥር ወደ 45 ዝቅ ብሏል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ለክልል ምክር ቤቶች በድምሩ ለ284 ወንበሮች ዕጩዎችን ያላቀረበ ሲሆን፣ ይህም ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች ሲቀነሱ ተስተካክሎ ወደ 267 ወንበሮች ወርዷል።

ነባራዊው የውጤት ስርጭት እንደሚያሳየው፣ ውጤት ካልተገለጸባቸው የምርጫ ክልሎች ውጪ ባሉት ቦታዎች ሁሉ ተቃዋሚዎች እና የግል ዕጩዎች ብልፅግና ባልተወዳደረባቸው የምርጫ ክልሎች መመረጥ ችለዋል። ሆኖም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ልዩ ሁኔታ የታየ ሲሆን፣ ብልፅግና በ6 የፓርላማ ወንበሮች ላይ ብቻ ሳይወዳደር ቢቀርም ተቃዋሚዎች ግን በአጠቃላይ 10 ወንበሮችን ማሸነፍ ችለዋል።

ከእነዚህ የፓርላማ ወንበሮች መካከል አንዱን በቀጥታ ውድድር ያሸነፈው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ ፓርቲው በተጨማሪም በክልል ምክር ቤቶች ለ6 የክልሎች ምክር ቤቶች ወንበሮች በተደረጉ የቀጥታ ውድድሮች ብልፅግናን ማሸነፍ መቻሉ ተረጋግጧል።

በትናንቱ የውጤት መግለጫ መሠረት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተቃዋሚዎች መካከል ኢዜማ 13 ወንበሮችን በማግኘት ከፍተኛውን ድርሻ ሲወስድ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) 6 ወንበሮችን አግኝቷል። እነርሱን በመከተል፣ የፓርላማ መቀመጫዎች ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ መድረክ (መድረክ) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (ኢዴኃን) እያንዳንዳቸው 3 ወንበሮችን በመውሰድ ተከፋፍለዋል።

በግል የቀረቡ ዕጩዎች ደግሞ 8 የፓርላማ ወንበሮችን ማሸነፍ ችለዋል። በሌላ በኩል “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቅንጅት” አባላቱ ቢያሸንፉም እንኳ ወደ ምክር ቤት እንዳይገቡ የከለከለ ቢሆንም፣ በምርጫው ሂደት 2 አባላቱ ለፓርላማ፣ 6 አባላቱ ደግሞ ለክልል ምክር ቤቶች ወንበር ማግኘታቸው ታውቋል።

ለክልል ምክር ቤቶች በተመዘገበው ውጤት መሠረት፣ ኢዜማ 73 ወንበሮችን በማግኘት በክልል ደረጃ ከፍተኛው የተወካዮች ቁጥር ያለው ተቃዋሚ ፓርቲ መሆን ችሏል። ነእፓ በ35 ወንበሮች እንዲሁም ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት በ34 ወንበሮች በጥንካሬ ተከትለዋል።

የግል ዕጩዎች በበኩላቸው 9 የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን ወስደዋል። በተለይ በሶማሌ ክልል ተቃዋሚዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወንበር (በድምሩ 38 ወንበሮች) ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) 20 ወንበሮችን፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ደግሞ 13 ወንበሮችን በበላይነት ወስደዋል።

  • ከትግራይ ክልል ውጪ ያሉ የክልል ምክር ቤቶች ወንበሮች ብዛት፤ 2,764
  • ውጤታቸው የተገለጸላቸው የክልል ምክር ቤቶች ወንበሮች ብዛት፤ 2,700
  • በአማራ ክልል ምርጫ ያልተካሄደባቸው ወንበሮች ብዛት፤ 17
  • ድጋሚ ቆጠራ ወይም ድጋሚ ምርጫ የሚካሄደባቸው ወንበሮች ብዛት፤ 47
  • ምንም ዕጩ ያልቀረበባቸው (vacant) ወንበሮች ብዛት፤ 19
  • ብልፅግና ወንበሮች ያሸነፋቸው ወንበሮች ብዛት (19ኙ ውጤታቸው ያልተገለጹትን ጨምሮ)፤ 2,410 (89%)
  • ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች ያገኟቸው ወንበሮች ብዛት (19ኙ ውጤታቸው ያልተገለጹትን ጨምሮ)፤ 271 (10%)

ይሁን እንጂ ትናንት ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መግለጫ ላይ ውጤታቸው እንደጸደቀ ቢገለጽም፣ ማን እንዳሸነፋቸው በስም ያልተጠቀሰ 19 የክልል ምክር ቤት ወንበሮች አሉ።

ለአብነት ያህል በአማራ ክልል ውጤት የጸደቀላቸው 274 ወንበሮች መሆናቸው ቢነገርም፣ 257ቱን ብልፅግና እና 16ቱን ተቃዋሚዎች አሸነፉ ተብሎ በድምሩ የ273 ወንበሮች ዝርዝር ብቻ የተገለጸ ሲሆን የ4 ወንበሮች ውጤት አልተነገረም። በተመሳሳይ ሁኔታ በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ንዋይ በተነበበው ሪፖርት ላይ በድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤት የ11 ወንበሮች፣ በጋምቤላ ክልል ምክር ቤት የ3 ወንበሮች፣ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የ1 ወንበር ዝርዝር አሸናፊ አልተካተተም።

ጉዳዩን በተመለከተ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከቦርዱ ባገኘችው ይፋዊ ምላሽ፤ እነዚህ በጥቅሉ 19 የሚሆኑት ወንበሮች በምዝገባ ወቅት ምንም ዓይነት ዕጩ ያልቀረበባቸው በመሆናቸው ማንም ተወካይ የማይገባባቸው (Vacant) ሆነው የሚቆዩ መሆናቸው ተረጋግጧል።

በአጠቃላይ እስካሁን ይፋ በሆነውና በእነዚህ 19 ዕጩ አልባ ወንበሮች ስሌት መሠረት፣ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ 2,410 ወንበሮችን (89 በመቶ) በማሸነፍ የአንበሳውን ድርሻ ሲይዝ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች በጋራ 271 ወንበሮችን (10 በመቶ) ማግኘት ችለዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)