ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ጠቅላላ ውጤት አሳወቀ፤ ብልፅግና ፓርቲ የፌዴራል መንግሥት እና የሁሉንም ክልሎችና ፌዴራል ከተሞች ማሸነፉ በይፋ ታውጇል

​የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል ባዘጋጀው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብር ላይ አጠቃላይ የምርጫውን ፍፃሜ ይፋ አድርጓል።

ቦርዱ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ መሠረት፣ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ምርጫ በተካሄደባቸው የሁሉም ክልል እና የፌዴራል ከተማ ምክር ቤቶች እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ወንበሮችን በማግኘት አጠቃላይ አሸናፊነቱን በይፋ አረጋግጧል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ምርጫ ከተካሄደባቸው 501 ወንበሮች መካከል ብልፅግና ፓርቲ 438 መቀመጫዎችን ጠቅልሎ የወሰደ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 48 ወንበሮች በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በግል ዕጩዎች መካከል መከፋፈላቸው ታውቋል። በተወሰኑት ላይ የድጋሚ ማጣራት ወይም ድጋሚ ምርጫ ይካኼድባቸዋል።

ቦርዱ ይፋ ባደረገው የክልል ምክር ቤቶች የመጨረሻ የውጤት ስርጭት መረጃ መሠረት፣ ብልፅግና ፓርቲ በሁሉም አካባቢዎች እጅግ ሰፊ የአብላጫ ወንበር ድምፅ አግኝቷል።

በዚህም መሠረት በኦሮሚያ ክልል ከነበሩት 528 መቀመጫዎች ውስጥ 523ቱን፣ በአማራ ክልል ከ277 መቀመጫዎች 257ቱን፣ በአፋር ክልል ከ135 መቀመጫዎች 124ቱን፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ከተመዘገቡት 252 መቀመጫዎች መካከል 214ቱን ብልፅግና ፓርቲ ማሸነፍ ችሏል። በተጨማሪም በጋምቤላ ክልል ከ205 መቀመጫዎች 176ቱን፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከ165 መቀመጫዎች 145ቱን፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከ171 መቀመጫዎች 144ቱን፣ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከ224 መቀመጫዎች ውስጥ 182ቱን ወንበሮች ገዢው ፓርቲ ወስዷል። ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት 35 የምርጫ ክልሎች መካከል የ34ቱ ውጤት የታወቀ ሲሆን፣ ብልፅግና ከተመዘገቡት 170 መቀመጫዎች 143ቱን አሸንፏል። በሲዳማ ክልል ከ190 መቀመጫዎች 175ቱን፣ በሐረሪ ክልል ከ36 መቀመጫዎች 32ቱን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ158 መቀመጫዎች 134ቱን፣ እንዲሁም በድሬዳዋ ምክር ቤት ከተዘጋጁት 189 መቀመጫዎች መካከል 161ዱን ወንበሮች ብልፅግና ፓርቲ በበላይነት አግኝቷል።

በዕለቱ ይፋ የተደረጉት እነዚህ መዋቅራዊ መቀመጫዎች ውጤታቸው የጸደቀ ሲሆን፣ መፍትሔ የሚሹ የሕግና የአሠራር ክርክሮች የሚስተናገዱባቸውን ወይም ምርጫ የሚደገምባቸውን ልዩ ቦታዎች አይጨምርም።

ቦርዱ እንዳስታወቀው፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ10 የምርጫ ክልሎች፣ እንዲሁም ለክልል ምክር ቤት በ3 የምርጫ ክልሎች ውጤት ላይ ድጋሚ የድምፅ ቆጠራ ይካሄዳል።

ከዚህም በላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ6 የምርጫ ክልሎች፣ እንዲሁም ለክልል ምክር ቤት በ7 የምርጫ ክልሎች ላይ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ የሚደገም ሲሆን፣ ለክልል ምክር ቤት ድጋሚ ምርጫ ከሚደረግባቸው 7 ቦታዎች መካከል 6ቱ በሶማሌ ክልል የሚገኙ ናቸው። ቦርዱ በጥቅሉ በ1,139 የምርጫ ክልሎች እና ከ52 ሺሕ በላይ በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫውን ክንውን አከናውኗል።

​በምርጫው ሂደት ላይ የታዩ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ቦርዱ ባቀረበው ግምገማ፣ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተዋወቀው የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የክኅሎት ክፍተት በመፈጠሩ የመረጃ ፍሰት መስተጓጎል ማጋጠሙን ጠቅሷል። ከዚህም በተጨማሪ በአንዳንድ የታችኛው የመንግሥት መዋቅሮች በኩል በቦርዱ ሥራ ላይ ጣልቃ የመግባት እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ቅስቀሳ የማስተጓጎል ድርጊቶች መታየታቸውን፣ በድምፅ መስጫ ዕለት ረዣዥም ሰልፎች መፈጠራቸውን፣ እንዲሁም አንዳንድ የምርጫ አስፈፃሚዎች የገለልተኝነትና የብቃት ማነስ ችግር እንደነበረባቸው ይፋ አድርጓል።

​ይሁን እንጂ በጠንካራ ጎንነቱ በተጠቀሰው አጠቃላይ መረጃ መሠረት፣ በዚህ አገር አቀፍ ምርጫ ላይ በጥቅሉ 54.5 ሚሊዮን መራጮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከተመዘገበው ጠቅላላ ሕዝብ ውስጥ 96.2 በመቶ የሚሆኑት መራጮች በዕለቱ ጣቢያዎች ተገኝተው ድምፅ መስጠታቸው ተገልጿል።

በዚህም መሠረት ገዢው ፓርቲ ለቀጣዩ አምስት ዓመታት የሀገሪቱን መንግሥት የመምራት ሥልጣኑን በድጋሚ ማረጋገጡን የቦርዱ ውጤት አመላክቷል።

በዚህ የውጤት እወጃ መርሐ ግብር ላይ የኢፌድሪ ፕሬዝደንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ እንዲሁም ከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች በክብር እንግድነት ተገኝተዋል። (ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)