የፓርላማ መቀመጫዎች ስብጥር

አሁን በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ550 እንዳይበልጥ ይደነግጋል ። በየአምስት ዓመት በሚካሄድ ምርጫ የሚመረጡት የምክር ቤቱ አባላት ዘጠኝ ክልሎች እና ሁለት የከተማ መስተዳድሮችን የሚወክሉ ናቸው። 

ከፓርላማ መቀመጫዎች አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት የኦሮሚያ ክልል ተመራጮች ናቸው። ኦሮሚያ 178 የተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ያስመርጣል። በመቀመጫ ብዛት ሁለተኝነትን የያዘው የአማራ ክልል በበኩሉ በፌደራል ፓርላማ በ138 ተመራጮች ይወከላል። 

ሃምሳ ስድስት ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦችን በውስጡ ያቀፈው የደቡብ ክልል የፓርላማውን ሶስተኛ ከፍተኛ ቁጥር ይዟል። ክልሉ በተወካዮች ምክር ቤት 123 አባላት አሉት። የትግራይ ክልል በፌደራሉ ፓርላማ 38 መቀመጫዎች በመያዝ በተወካዮች ብዛት በአራተኛነት ደረጃ ተቀምጧል። 

ሶማሌ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፓርላማ ያላቸው መቀመጫ ብዛት እኩል ነው። ሁለቱም በተመሳሳይ 23 ተወካዮች በፌደራሉ የእንደራሴዎች ምክር ቤት አሏቸው። የታዳጊ ክልል የሚባሉት ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር እና ጋምቤላ ክልሎች በድምሩ ያላቸው የፓርላማ ተወካዮች ብዛት ከሶማሌ ክልልም ሆነ ከአዲስ አበባ ያንሳል። ሶስቱ ክልሎች በድምሩ በፓርላማ የሚወከሉት በ20 ተመራጮች ነው። 

እንደ አዲስ አበባ ሁሉ የከተማ አስተዳደርነት እውቅና ያለው የድሬዳዋ ከተማ ሁለት ተመራጮች ብቻ ለፓርላማ ይልካል። የድሬዳዋ አጎራባች የሆነው የሀረሪ ክልልም በፓርላማ ያሉት የተወካዮች ቁጥር ብዛት ሁለት ብቻ ነው። (ኢትዮኢሌክሽን)