መጋቢት 4፣ 2018 — “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) ከጥር 16 እስከ የካቲት 15 ቀን 2018 ዓ.ም ባለው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በምሽት ሁለት ሰዓት ዜናዎቹ ያቀረባቸውን ዘገባዎች መርምሯል። ዳሰሳው ትኩረት ያደረገው በቅድመ ምርጫ 2018 አዘጋገብ ፍትሓዊነት ላይ ሲሆን፣ በመንግሥት በጀት የሚተዳደረው ይህ መገናኛ ብዙኃን ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመጣጣኝ እና ፍትሓዊ የዘገባ ሽፋን እንዳልሰጠ ማረጋገጥ ችሏል።
የምርመራው መነሻ (መግፍዔ)
ኢትዮጵያ በግንቦት 2018 ዓ.ም የሚካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ለማከናወን በሂደት ላይ ባለችበት ወቅት፣ የመገናኛ ብዙኃን በተለይም የመንግሥት ሚዲያዎች ለተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ፍትሓዊ የአየር ሽፋን መስጠታቸው ለምርጫው ተዓማኒነት ወሳኝ ነው።
በዚህ መሠረት “የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ ሥነ-ምግባር እና አሠራር መመሪያ ቁጥር 02/2013” በአንቀጽ 16(1) ላይ የመንግሥት ሚዲያዎች “ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች አቋማቸውን ለመራጭ ሕዝቡ ለማቅረብ ፍትሓዊ ዕድል እንዲያገኙ” የማድረግ ግዴታ ጥሎባቸዋል። እንዲሁም በአንቀጽ 16(6) መሠረት በምርጫ ወቅት ለሚዘጋጁ የውይይት፣ የክርክር እና የቃለ-መጠይቅ ፕሮግራሞች ተገቢ የዜና ሽፋን መስጠት እንዳለባቸው ይደነግጋል።
ሐምሌ 3፣ 2013 ዓም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ኛውን አገር ዐቀፍ ምርጫ ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ የቀድሞዋ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ባደረጉት ንግግር “ዛሬ እዚህ የምትቀርፁን የመንግሥት ሚዲያዎች… የመንግሥት ባለሥልጣናት ኮታቸው ላይ የተሰካው ማይክራፎን የማይወልቅ ይመስል ሌት ተቀን የእነሱን ካምፔን እና ቅስቀሳ ስታስተላልፉ ቆይታችሁ የተቃዋሚዎችን 10 እና 15 ደቂቃ ማድረጋችሁ ፍትሐዊነታችንን አጉድሎብናል” ማለታቸው ይታወሳል።
ከፍተኛ ተደራሽነት ያላቸው የመንግሥት ሚዲያዎች የምርጫ አዘጋገብ የምርጫው ፍትሐዊነት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በመረዳት፣ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ይህንን ዳሰሳ አዘጋጅታለች።
የዳሰሳው ግኝት
ይህንን መሠረት በማድረግ በ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተደረገው የሚዲያ ዳሰሳ መሠረት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ETV) ከጥር 16/2018 ዓ/ም እስከ የካቲት 15/2018 ዓ/ም ባሉት ቀናት ውስጥ የቀረቡ የምሽት 2፡00 ሰዓት ምርጫ ነክ ዜናዎች እና ማስታወቂያዎች የተሰጣቸውን አጠቃላይ ሽፋን፣ የዜናዎቹን ይዘት፣ ከምርጫ ነክ ዜናዎች ውጪ ያሉ ዘገባዎች በምርጫው ተሳታፊ የሆኑ ፓርቲዎች ላይ የሚያሳድረው አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖዎችን በመመርመር በተገኘው መረጃ መሠረት ብልፅግና ፓርቲ ከሌሎቹ ፓርቲዎች በተለይ ሰፊ የዜና ዘገባ ሽፋን እንደተሰጠው ለማረጋገጥ ተችሏል።

ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ የአየር ሰዓት ከተሰጣቸው አምስት ዘገባዎች ውስጥ ሁለቱን አግኝቷል። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በብልፅግና ፓርቲ ስብሰባ ላይ ምርጫን በተመለከተ ያቀረቡት ንግግር ላይ ያተኮረ ዜና ብቻውን 10 ደቂቃ በመውሰድ ከፍተኛ የአየር ሰዓት ሽፋን ሲያገኝ፣ ለፓርቲው ማኒፌስቶ እና አርማ ማስተዋወቂያ የተዘጋጀው ፕሮግራም ደግሞ 4 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ በመውሰድ አራተኛ ከፍተኛ የአየር ሰዓት ሽፋን አግኝቷል።
በአንፃሩ ሕብር ኢትዮጵያ የምርጫ ማኒፌስቶ ማዘጋጀቱን የሚገልጸው ዜና 3 ደቂቃ ከ46 ሰከንድ የወሰደ የአየር ሰዓት ያገኘ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኗል። 2ኛ ከፍተኛ የአየር ሰዓት የወሰደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ ነክ ትንታኔ ቢሆንም በፓርላማ መንግሥትን በመወከል ያደረጉት ንግግር መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለብልፅግና ፓርቲ የተሰጠ የአየር ሰዐት ተደርጎ በዳሰሳው አልተወሰደም።
ሆኖም በጥቅሉ ብልፅግና ፓርቲ በተናጠል ወይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ የሚጠቀስባቸው ዘገባዎች 17 ደቂቃ የአየር ሰዓት ሽፋን ያገኙ 5 ዜናዎች ሲሆኑ፣ በአንፃሩ ሌሎች 9 የተወዳዳሪ ፓርቲዎች በተናጠል ወይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የተጠቀሱባቸው ዘገባዎች 16 ደቂቃ የወሰዱ አጫጭር ዜናዎቹ ናቸው። በዚህም በድምሩ 25 ደቂቃ ከሰላሳ ሰከንድ ብቻ የአየር ሰዓት ሽፋን እንዳገኙ ዳሰሳው ያሳያል።

በዜናዎቹ ውስጥ የተጠቀሱ ፓርቲዎችን በተናጠል ወይም በቡድን በተጠቀሱበት ድግግሞሽ መሠረት ሲታዩ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) 6 ዘገባዎች ላይ ሥሙ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ቀዳሚው ፓርቲ ሆኖ ተገኝቷል። ከኢዜማ በመቀጠል ብልፅግና ፓርቲ 5 ጊዜ፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) 3 ጊዜ ቢጠቀሱም፣ ሌሎቹ ሰባት ፓርቲዎች ከአንድ ጊዜ በላይ አልተጠቀሱም።
ተቃዋሚዎቹ ፓርቲዎች ምንም እንኳን ሥማቸው እና እነርሱን የሚመለከቱ ጉዳዮች በዜና ዘገባዎች ከሌሎች ፓርቲዎች አንድ ላይ በጋራ ቢጠቀሱም፣ “ሕብር ኢትዮጵያ” የተባለ የፓርቲዎች ቅንጅት የምርጫ ማኒፌስቶ እያዘጋጀ መሆኑን የሚገልጽ የዜና ትንታኔ ከማግኘቱ በቀር የተናጠል ሽፋን ዘገባ ያገኘ ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ በዳሰሳው በተቃኙ ዘገባዎች ውስጥ አልታየም። ሆኖም፣ በዜና እወጃዎች ሰዓት መካከል በተደጋጋሚ ይለቀቁ በነበሩ ማስታወቂያዎች ብልፅግና ፓርቲ፣ ኢዜማ፣ እና ነእፓ የፓርቲዎቻቸውን ዝግጅት የሚመለከቱ ቃለ መጠይቆች እንደተደረጉላቸው መገንዘብ ይቻላል።

ከዚህ በተጨማሪ በዳሰሳው ውስጥ እንደተስተዋለው፣ “ምርጫ ነክ ዜና” ተብለው ያልተመደቡ ነገር ብልፅግና ፓርቲ በመንግሥት ኃላፊነቱ ያከናወናቸውን የልማት ሥራዎች አፈፃፀም የሚያመለክቱና በተዘዋዋሪ የፓርቲውን ገጽታ የሚገነቡ የልማት ዘገባዎች እጅግ ሰፊ የአየር ሰዓት ይሰጣቸዋል።
ዳሰሳው በተመለከታቸው የአንድ ወር የምሽት ሁለት ሰዓት ዜናዎች ውስጥ ተደጋጋሚ እና ሰፊ የአየር ሽፋን የሚሰጣቸው ዘገባዎች፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ሥራዎች ክትትል፣ የ“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶች ምረቃ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች እድገት፣ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም እና የከተማ ገጽታ ለውጥ የሚያሳዩ ዜናዎች ናቸው። እንዲሁም የስንዴ ኤክስፖርት እና የግብርና ምርታማነትን የሚያወድሱ ዘገባዎች በብዛት መቅረባቸው ገዥው ፓርቲ በተዘዋዋሪ እንደ ምርጫ መቀስቀሻ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ዘገባዎች ናቸው።
በአጠቃላይ ከጥር 16/2018 እስከ የካቲት 15/2018 የተላለፉ የምሽት 2፡00 ሰዓት የምርጫ ዘገባ ሽፋን መረጃዎች የሚያመለክቱት በምርጫ ሂደት ውስጥ የመንግሥት ቴሌቪዥን ለተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠው የአየር ሰዓት ሽፋን ተመጣጣኝ እንዳልሆነ የሚያሳይ ሲሆን ይህም በመገናኛ ብዙኃን የምርጫ አዘጋገብ መመሪያ የተጠቀሱትን የፍትሐዊ ሽፋን መርሆች እንደሚጥስና የአየር ሰዓት ሽፋን ድልድል ኢፍትሕዊ እንደሚያደርገው ያመለክታል።
ምርጫ እና የሚዲያ አዘጋገብ
መገናኛ ብዙኃን የኤዲቶሪያል ነፃነታቸው የተጠበቀ ቢሆንም፣ ይህ ነፃነት የሕዝብን እምነት ለመጠበቅ ታስበው በተዘጋጁ ሙያዊ ደንቦች አማካኝነት ሚዛን እንዲጠብቁ ይደረጋል። በዘርፉ በተደረጉ ጥናቶች እንደተመላከተው ተጨባጭነት (objectivity) እውነታዎችን እና ማስረጃዎችን ነጥሎ በመለየት እንዲሁም በገለልተኝነት ወይም ከአድልዎ በመጠበቅ (impartiality) የሕዝብን አመኔታ ለማግኘት ይረዳል። ይህንን ሕዝባዊ አመኔታ የማግኘት ኃላፊነቱ ደግሞ በሕዝብ (መንግሥት) በጀት በሚተዳደሩ የሚዲያ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ነው።
በኢትዮጵያ ምርጫዎች ወቅት በመንግሥት ሚዲያዎች ገዢው ፓርቲ የተለየ ሽፋን ያገኛል የሚሉ ቅሬታዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ። ይህንን ለመቅረፍ በምርጫ 2013 ዋዜማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ለተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች የሚውለውን የነፃ አየር ሰዓት ድልድል በ57 የመንግሥት እና የንግድ መገናኛ ብዙኃን ላይ ተፈፃሚ ሆኗል። ሆኖም፣ የመገናኛ ብዙኃን ሚና በነዚህ የነፃ አየር ሰዓቶች ብቻ የተገደበ ባለመሆኑ የቀድሞዋ የቦርዱ ሰብሳቢ እንደጠቀሱት የመንግሥት ሚዲያዎች ለብልፅግና ፓርቲ የተለየ የአየር ሽፋን ሰጥተዋል።
የሚዲያ የአየር ሰዓት ሽፋንና ፍትሐዊነትን በተመለከተ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ በባህር ዳር የኒቭርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ የሚዲያና ሥነ ተግባቦት ተማሪ እንደገለጹት “በምርጫ ወቅት የመንግሥት ሚዲያዎች በተወዳዳሪ ፓርቲዎች መካከል የአየር ሰዓት ሚዛን መጠበቅ የዲሞክራሲ ሂደቱን ተዓማኒነት ለማጠናከር ወሳኝ ነው።” አስተያየት ሰጪው አክለውም “በምርጫ ወቅት የመገናኛ ብዙኃን ሚና በተለይም የመንግሥት ሚዲያዎች ሚና በዲሞክራሲ ሂደት ውስጥ ወሳኝ በመሆኑ የምርጫውን ተዓማኒነትና ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ተመጣጣኝ የአየር ሰዓት ሽፋን መስጠት መራጩ ሕዝብ በተለያዩ ፖለቲካ አማራጮች ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲወስን ያግዛል” ብለዋል።
“ይሁን እንጅ” ይላሉ አስተያየት ሰጪው “የመንግሥት ሚዲያ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የሚሰጠው የሽፋን ሚዛን ካልተጠበቀ የምርጫ ፍትሃዊነት በሕዝብ ዘንድ ጥያቄ ሊያስነሳ ስለሚችል ሚዲያዎች የምርጫ ዘገባ ሽፋንን እና የምርጫ ክርክር የአየር ሰዓት ሽፋን ድልድልን በፍትሐዊነት መምራት አለባቸው።”
[ምርጫ 2018 – በኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




