ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች በ7ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በየመኖርያ አካባቢያቸው ሄደው በመራጭነት እንዲሳተፉ ያስተላለፈው መመሪያ ለትግበራ አዳጋች እንደሆነ እና የተማሪዎችን የምርጫ ተሳትፎ እንደሚቀንስ የተለያዩ አካላት ገለጹ።
የትምህርት ሚኒስቴር “ተማሪዎች መርጠው ለመመለስ የሚያስፈልጋቸው ቀናት ብቻ ታስቦ እንዲፈቀድላቸው” ሲል ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሰራጨው መመሪያ በተለይ በመዝገብ ወይም በማኑዋል የመራጮች ምዝገባ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ነዋሪ ለሆኑ ተማሪዎች አመቺ አልሆነም። በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች ሁለት ግዜ ተመላልሰው የመራጮች ምዝገባን ለማካሄድ እና በምርጫው ዕለትም ተገኝተው ድምጻቸውን ለመስጠት ከፀጥታ፣ ከሎጅስቲክስ እና ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሳቢያ እጅግ አዳጋች እንደሆነ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስተያየት የሰጡ ተማሪዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ባልደረቦች እና የ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ገልጸዋል።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ልዩ የምርጫ ጣቢያ መቋቋም የሚያስፈልግባቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚገኙባቸውን አካባቢዎች እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ “ቦርዱ ጥናት አድርጎ መረጃ መሰብሰቡን” ገልጸዋል።
በተለይም ጥናቱ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ “ምን ያህል ተማሪዎች አሉ” ከሚለው ጀምሮ “ምዝገባው እንዴት ይካሄዳል እና ድምጽ እንዴት ይሰጣል የሚሉትን” አስመልክቶ ከሚመለከታቸው የተቋማት ኃላፊዎች ጋር ምክክር መደረጉን ሰብሳቢዋ አሳውቀዋል። በቀጣይነትም መረጃዎቹን ተንተርሶ ከሌሎቹም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ቦርዱ ሁኔታዎችን የሚያመቻች እንደሆነም ጠቅሰው ነበር።

በዚህም መሠረት የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በመጪው 7ተኛ ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉበትን ሁኔታ አስመልክቶ ለሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመመሪያ ደብዳቤ አሰራጭቷል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የካቲት 18 ቀን 2018 ይፋ ባደረገው በዚህ ደብዳቤ እንደተገለጸው በሀገራዊው ምርጫ ላይ “ተማሪዎች መምረጥ እንዲችሉ የሚሰጠው ትምህርት ከምርጫው በፊት እንዲጠናቀቅ” እና ተማሪዎች ወደ መኖሪያ አካባቢዎቻቸው እንዲሄዱ ታስቦ የነበረ ቢሆንም “አካሄዱ በትምህርት አሰጣጥና ጥራት እንዲሁም በተማሪዎች የፈተና ዝግጅትና ስኬታማናት ላይ በሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ ምክንያት አስቸጋሪ ሆኖ” መገኘቱን ገልጿል።
በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ወደየአካባቢዎቻቸው “ሄደው መርጠው ለመመለስ የሚያስፈልጋቸው ቀናት ብቻ ታስቦ እንዲፈቀድላቸው እና መርጠው እንደተመለሱ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ” ትምህርት ሚኒስቴር ከምርጫ ቦርድ አመራሮች ጋር መግባባት ላይ እንደደረሰ አሳውቋል። ሚኒስቴሩ “ተማሪዎች በተፈቀደላቸው ቀናት ውስጥ ሄደው መርጠው መመለስ እንዲችሉ ፍቃድ እንዲሰጣቸው” ሲልም አሳስቧል። ሆኖም በተለያዩ ግላዊና ሀገራዊ ችግሮች ምክንያት ወደየመጡበት አካባቢ ሄደው ለመምረጥ እንደሚቸገሩ ተማሪዎች ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የማርኬቲንግና ፋይናንስ ተማሪ የሆነው ብርሀን ክንዳለም ከደብረ ታቦር አካባቢ እንደመጣና እሱም ሆነ ሌሎች በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ የአካባቢው ተወላጆች ካለው የጸጥታ ሁኔታ አንጻር ከዩንቨርሲቲው ፍቃድ ቢያግኙም ወደ አካባቢው ሄደው በምርጫው በመራጭነት ለመሳተፍ አዳጋች እንደሚሆንባቸው ገልጿል።
በተጨማሪም ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ከዳንግላ እና ከሞጣ አካባቢዎች የመጡ ሁለት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት የማርኬቲንግ ተማሪዎች አስገዳጅ ካልሆነ በቀር ለምርጫ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው ሄደው መምረጥ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ውሳኔው የተማሪውን አቅምና ፍላጎት “በፍፁም ያላማከለ” እንደሆነ የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የሆነችው ፌኔት አብዱረህማን ትገልፃለች።
እንደ ፌኔት ገለጻ ከሆነ አንድ ተማሪ በ5 ቀናት ወደ ምርጫ ጣብያ ሄዶ ለመምረጥ የመራጮች ካርዱን ቀድሞ መውሰድ ይጠበቅበታል። በማንዋል የመራጮች ምዝገባ በሚካሂደባቸው አካባቢዎች ተማሪው በአካል ተገኝቶ የመራጮች ካርድ ሳይወስድ፣ የመምረጥ ፍላጎትና አቅም ኖሮት ቢሄድ እንኳን ቀድሞ የመራጭነት ካርዱን ባለመውሰዱ ምክንያት መምረጥ አይችልም ስትልም ፌኔት አክላለች።

ከኑሮ ውድነት አንጻር ለመጓጓዣ የሚያስፈልገው ወጪ፣ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋለው የሰላም ሁኔታ እንዲሁም ተማሪው ትምህርቱን ለመጨረስና ለመመረቅ በሚዳክርበት ወቅት ከመሆኑ እና በተለይ ተመራቂ ተማሪዎች ከሚጠብቃቸው የመውጫ ፈተና ዝግጅት አንጻር ለመምረጥ የተሰጡት ቀናት አነስተኛ መሆናቸው ውሳኔው የተማሪዎችን ሁኔታ ታሳቢ ያላደረገ እንደሆነ ያሳያል ስትል የተማሪ ህብረት ፕሬዝዳንቷ ገልጻለች።
“የፈለገ ይሂድና ይምረጥ ያልፈለገ ይተው” በሚመስል መልኩ የተላለፈ መልዕክት ነው ያለችው ፌኔት አሁን ባለው ሁኔታ ተማሪው በአብዛኛው ሄዶ ምርጫ ላይ ተሳትፎ ለመመለስ ዝግጅት ያለው አይመስልም ስትልም አክላልች።
የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ ሂደቱን ለማገዝ ቦርዱ በሚሰጠው አቅጣጫ መሰረት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ለተማሪዎቻቸው የመራጮች “ምዝገባ እና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን በማመቻቸት” ለቦርዱ የምርጫ እንቅስቃሴ ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስቦ ነበር።
ሆኖም አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ እንደገለጸው ዩኒቨርሲቲው ስለተማሪዎች የመራጭነት ተሳትፎ የአፈጻጸም መመሪያ እስካሁን እንዳልደረሰውና ተማሪዎቹም በቦታ ርቀትና በገንዘብ እጥረት ምክንያት ወደየመጡበት አካባቢ ሄደው ለመምረጥ ፍላጎት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
በ2013 ዓ.ም በተካሄደው 6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ተማሪዎች በሚማሩበት የትምህርት ተቋም ውስጥ በተቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች አማካኝነት ደምጽ መስጠት ችለው እንደነበር የገለጸችው ፌኒት ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔውን በድጋሚ ቢያጤነው በምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎች የተሻለ ነው ብላለች።
በተመሳሳይ የኢትዮጵዯ ዴሞክራቲክ ኅብረት (አዴኅ) ሰብሳቢ ገብሩ በርሔ ውሳኔውን “ሊመርጠን የሚችለውን የወጣቱን ኃይል [ተሳትፎ] የገደበ” ሲሉ ኮንነውታል። ገብሩ በማከልም ሀገር ተረካቢው በትምህርት ላይ ያለው ወጣቱ ኃይል መሆኑን ጠቁመው ይህ የህብረተሰብ ክፍል የራሱ ገቢ ያለው ባለመሆኑ “በራስህ ገንዘብ ሂድና መርጠህ ተመለስ ማለት አዳጋችና የማይታሰብ” እንደሆነ አብራርተዋል። “ይህንንም ጉዳይ ትምህርት ሚኒስቴር በድጋሚ ተመልክቶ እንደሚያስተካከለው እምነቴ ነው” ሲሉም አክለዋል። [ምርጫ 2018 – በኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




