በማዕከላዊ ጎንደር ዞንና በጎንደር ከተማ በአዘዞ ክፍለ ከተማ የምርጫ ምዝገባ ሲያስተባብሩ የነበሩ የአካባቢ ሚሊሺያዎች መገደላቸው ተሰማ

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ትላንት መጋቢት 15፣ 2018 ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ባወጣው መግለጫ ላይ በመመሥረት ባደረገችው ማጣራት በማዕከላዊ ጎንደር ዞንና በጎንደር ከተማ በአዘዞ ክፍለ ከተማ መጋቢት 12 ቀን 2018 ዓ.ም የምርጫ ምዝገባ ሲያስተባብሩ የነበሩ ሚሊሺያዎች መገደላቸውን ከተለያዩ ምንጮች ማረጋገጥ ችላለች። ይሁንና ጥቃቱን ማን እንደፈፀመውና ምን ያህል ሚሊሻዎች እንደተገደሉ በግልጽ ማረጋገጥ አልቻለችም።

ትበብር ለኢትዮጵያ አንድነት መጋቢት 15/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “ድርጊቱ ፍርኃት ፈጥሮብኛል” ሲል አስታውቋል።

ትብብር ለኢትዮጵያ በመግለጫው “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዕጩዎችና ምርጫን ለማስተባበር የሚወጡ የመንግሥት አካላት ጭምር በተለያዩ [የአማራ ክልል] አካባቢዎች ለከፍተኛ ሰቆቃና ሕልፈት” እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጽ፣ “በማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና በጎንደር ከተማ በአዘዞ ፀዳ ክ/ከተማ ባለፈው እሑድ መጋቢት 12 ቀን የኾነውና በመራጩ፣ በዕጩዎችና በአስተባባሪዎች ላይ ያደረሰው ፍርሐት፣ ሥነልቡናዊ ጫናና ተስፋ መቁረጥ” እንደ በቂ ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጿል።

“ዕጩዎችና አባላትን አደጋ ላይ የጣሉ፣ ምርጫውን አስቻይ የማያደርጉ ኹነቶች በአስቸኳይ እንዲፈቱ” ሲልም ትብብር ለኢትዮጵያ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።

የፀጥታ ችግር ያለባቸው አማራ ክልል ሙሉ በሙሉ፣ በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ፣ ከፊል ኦሮሚያ (ከዋና ዋና ከተሞች ወጣ ባሉ አካባቢዎች) እና በቤኒሻንጉል ክልል – መተከል ዞን ባሉ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ የደኅንነትና ለምርጫ አስቻይነት እጅግ አዳጋች መሆኑን ትበብሩ  ተረድቻለሁ ብሏል፡፡ ይኽንንም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ማሳወቁን ገልጿል፡፡

የሁኔታውን አደገኝነት ሲያስረዳ፣ ትብብሩ በመግለጫው “የዕጩ ምዝገባ በተጠናቀቀበትና የምርጫ ቅስቀሳ በተጀመረበት በአኹኑ ወቅት የእያንዳንዱ የትብብሩ ዕጩ እንቅስቃሴ ከየትኛውም ወገን ሊቃጣበት ከሚችል የሕይወት አደጋ ላይ ነው፤ ያ እንዳይኾን መጠበቅ እንደሚገባ ደግሞ  ትብብራችን በጽኑ ያምናል” ብሏል።

ስለኾነም አማራ ክልልን ጨምሮ በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚደረጉ ጦርነቶችና አጠቃላይ ለሕይወት አስጊ የፀጥታ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅላቸውና ጦርነቱ በጠረጴዛ ዙሪያ በድርድር እንዲቋጭ ለዚኽም መንግሥት ትልቁን ድርሻ እንዲወጣ  በመግለጫው ጠይቋል። በማከልም፣ “ኹኔታዎቹ በአስቸኳይ ፖለቲካዊ መፍትሔ ተሰጥቷቸው የዕጩዎቻችን ደህንነት ዋስትና እስካላገኘ ድረስ በተጠቀሱ አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ ስለሚከብደን ይፋዊና የአደባባይ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከማድረግ እንቆጠባለን፤ ቀጣይ እርምጃችንንም ለሕዝባችን በይፋ እንገልጻለን” ብሏል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]