የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት የምርጫ እና ፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አላምረው ይርዳው፣ “ተጠናክሮ የቀጠለው ዛቻ እና ማስፈራሪያ” በስምንት ቀን ውስጥ የማይቆም ከሆነ “ከምርጫው እንወጣለን” ሲሉ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ኃላፊው ይህንን ያሉት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ ሚያዝያ 14 ቀን ነው።
አቶ አላምረው በጋሞ ዞን፣ ዲታ የምርጫ ክልል፣ የፀጥታ አካላት “የጦር መሳሪያ ደግነው የሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ምልክት ያለበት ልብስ እያስወለቁ፣ እንዲሁም የምርጫ ቅስቀሳዎችን እያስተጓጎሉ ይገኛሉ” ብለዋል። ኃላፊው አክለውም የጥምረቱ ዕጩ የሆኑ ግለሰብ ከሥራ መባረርን ጨምሮ በደረሰባቸው “ዛቻ እና ማስፈራሪያ” ሳቢያ የዕጩዎች ከተወዳዳሪነት መውጣት የመሳሰሉት ፈተናዎች እንደገጠሟቸው ተናግረዋል።
ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት እያካሄደ ባለው የ7ኛው ጠቅላላ ሃገራዊ የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ላይ ገዢው ፓርቲ እና የመንግሥት የፀጥታ አካላት ከፍተኛ ጫና እና ወከባ እያሳደሩበት መሆኑን ሚያዚያ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫም አሳውቆ ነበር። በዚሁ መግለጫው፣ ፓርቲው “ሕገ-ወጥና አፈናዊ አሠራር ድርጊቶች ፈፃሚ አካላት ጉዳያቸው በአስቸኳይ ተጣርቶ ለምርጫው ሂደት ካለን የጊዜ እጥረት አንፃር በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ” ጠይቆ እንደነበር ይታወሳል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋሞ ዞን፣ ዲታ የምርጫ ክልል የጥምረቱ ዕጩ የሆኑት አቶ አብርሃም አዳሙ እና ሁለት ጓደኞቹ በዲታ ወረዳ ኮዶ ቀበሌ መታሰራቸውን እና ሌሎች በተለያዩ አካባቢዎች ዕጩ ያደረጋቸው አባላቱ፣ ከሥራ መባረርና መታገድ፣ ደመወዝ መከልከል፣ ማስፈራራት፣ የምርጫ ቅስቀሳ ቁሳቁስ መነጠቅ እና ሌሎችም ጫናዎች እየደረሱበት መሆኑን ጥምረቱ በመግለጫው አንስቷል።
በተመሳሳይ የጥምረቱ አንዱ አባል የሆነው እና በአቶ አላምረው በሚመራው በአገው ብሔራዊ ሸንጎ ዕጩዎች ላይ በሚደርሰው “ዛቻ እና ማሰፈራሪያ” ሳቢያ አራት ዕጩዎች ከምርጫው መውጣታቸውንም ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
አቶ አላምረው “ማስፈራሪያ እና ዛቻው በታጠቁ ኃይሎች የሚደረግ ሳይሆን፣ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች እያደረሱት ያለው ማስፈራሪያ ነው። ብልፅግና በታጣቂ ሥም የሚያደርገው ማስፈራሪያ በታችኛው መዋቅር ብቻ የሚደረግ ሳይሆን፣ ከበላይ የመንግሥት አካላት ጀምሮ የሚደረግ የተደራጀ ሴራ ነው” በማለት ወቀሳቸውን ገዢው ፓርቲ ላይ ሰንዝረዋል።

አቶ አላምረው፣ ምርጫው “ሰላማዊ እንዳይሆን” ብልፅግና እየሠራ ነው በማለት “የፓርቲው ዕጩዎች በተለያዩ አካባቢዎች እየታሰሩ ይገኛሉ፤ አባላቶቻችንም እስሩን ለምን አላሳቆማችሁም በሚል ቅሬታ እያቀረቡብን ይገኛል” ሲሉ አክለዋል።
“በዋግኽምራ አከባቢ ብልፅግናን ካልመረጣችሁ እርዳታ አታገኙም” በሚል ዜጎች በሚደርስባቸው ጫና ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ ያሉት ኃላፊው፣ “ይህ አካሄድ የምርጫ ሂደቱን ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ሂደቱ ላይ ጥያቄ ፈጥሯል” ብለዋል።
በተጨማሪም አንድ በዋግኽምራ አካባቢ የነበሩ የጥምረቱ ዕጩ እና የዋግህምራ ልማት ማኅበር ፕሬዝዳንት ከሥራቸው እንዲባረሩ መደረጉን ፓርቲው ገልጿል። በመሆኑም መንግሥት የሚያደርሰውን ጫና በሳምንት ገደማ ጊዜ ውስጥ የማያስተካክል ከሆነ ከ7ኛው ጠቅላላ ሃገራዊ ምርጫ “ራሱን እንደሚያገል” ጥምረቱ በግልጽ አስታውቋል።
ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት በይፋ የተመሠረተው እና ዕውቅና ያገኘው በሕዳር ወር 2018 ዓ.ም ሲሆን፣ ስምንት ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማቀፍ ለዘንድሮው ምርጫ እየተዘጋጀ ነው።
የጥምረቱ አባላት የጋምቤላ ነፃነት ንቅናቄ፣ አገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ ከፋ አረንጓዴ ፓርቲ፣ ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ከፋ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት፣ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አገው ለፍትሕ እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ናቸው።
ጥምረቱን ለመመሥረት ለአራት እና አምስት ዓመታት ሰነዶች ቀርበው ውይይት በማድረግ ያስማማናል ብለው የፈረሙ 32 ፓርቲዎች የነበሩ መሆኑን ኃላፊው የገለጹ ሲሆን፣ የፓርቲዎች የውስጥ ችግር እንዲሁም በቦርዱ ፍቃድ ሳይሰጣቸው በርካታ ፓርቲዎች በመቅረታቸው ለጥምረቱ የበቁት ፓርቲዎች ስምንት ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጥምረቱ ግጭት ባለበቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በዋግኽምራ፣ በላስታ ላሊበላ፣ በጎንደር ጃናሞራ፣ በቋራ፣ አዊ ዞን እና በመተከልም ዕጩዎችን ማቅረቡን ገልጿል። በተጨማሪም በሐዋሳ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ በሁሉም ምርጫ ክልሎች ዕጩ ያቀረበ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከ23 የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ክልሎች ውስጥ ለ18ቱ ዕጩዎችን አቅርቧል።
በአጠቃላይ 404 ዕጩዎችን ለ7ኛው ጠቅላላ ሃገራዊ ምርጫ ይዞ በመቅረብ 71 ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ 333 የሚሆኑትን ደግሞ ለክልል ምክር ቤት ዕጩ አድርጓል።
አቶ አላምረው፣ ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት የሚከተለውን ርዕዮት ዓለም “አዳጊ ማኅበራዊ ዴሞክራሲ” ሲሉ የጠሩት ሲሆን፣ “ከምዕራቡ ዓለም ቀጥታ የሚቀዳ ማኅበራዊ ዴሞክራሲን” በመተግበር ፈንታ፣ “በቅድሚያ አዳጊ የሆነ ማኅበራዊ ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ ቢያንስ ለ30 እና 40 ዓመታት በመተግበር በልምምድ ወደ የተሟላ ማኅበራዊ ዲሞክራሲ መሸጋገር” እንደሚያልም ተናግረዋል።
ጥምረቱ “አዲስ የአስተዳደር መዋቅር” እንደሚያዘጋጅ የገለጹት ኃላፊው፣ ከፌደራል አስተዳደር ቀጥሎ ክፍለ ሃገር፣ ወረዳ፣ ቀበሌ እንዲሁም የከተማ አገልግሎት እያለ እንደሚቀጥል በመግለጽ፣ “የዞን አስተዳደርን እንደሚያስቀር” አስታውቀዋል።
ጥምረቱ መንግሥት የሚሆንበት ዕድል ሲፈጠር፣ “የፌዴሬሽን ምክር ቤትን በማፍረስ፣ የባለሙያዎች ተቋም በማቋቋም፣ ከሕግ ባለሙያዎች፣ የድንበር ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለሙያዎች በማሰባሰብ፣ የክፍለ ሃገር ይገባኛል የሚል ጥያቄን ሕገ መንግሥቱን ብቻ መሠረት አድርገው የሚዳኙ የባለሙያዎች ተቋም ይቋቋማል” ብለዋል። በሌላ በኩል የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል የሆነ አንድ ሚኒስቴር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ባለማድረግ በአስፈፃሚው አካል እና በሕግ አውጪው መካከል የተወካዮች መደራረብ (overlap) እንዳይፈጠር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ጥምረቱ “የብሔር ፖለቲካ ወይም የዜግነት ፖለቲካ በሚል አንድ ጥግ ላይ ቆሞ የከረረ የፖለቲካ አካሄድ የመከተል ፍላጎት” እንደሌለው ኃላፊው ገለጸው፣ ኅብረብሔራዊ የሆነ ሃገር የመመሥረት ዓላማ ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል።
“አንድ ክልል በአንድ ብሔር ሥም መጠራት የለበትም” የሚሉ አቶ አላምረው፣ “ለምሳሌ አማራ ክልል ውስጥ የተለያዩ ማንነት ያላቸው ዜጎች ባሉበት” ሁኔታ ክልሉን፣ አማራ ብሎ መሰየም አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥምረቱ በ7ኛውጠቅላላ ምርጫ ምን ለማሳካት እንዳቀደ ላቀረበችው ጥያቄ፣ “ካቀረብናቸው ዕጩዎች 80 በመቶውን ዱላ እና ጠመንጃ ካላስቸገረን እናሸንፋለን” ሲሉ፣ አብዛኛዎቹን ዕጩዎቻቸውን ወደ ምክር ቤቶች ማስገባት ዓላማቸው መሆኑን አቶ አላምረው አመላክተዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




