በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ብልጽግና ፓርቲን በመወከል በአዲስ አበባ ከተማ ለፓርላማ አባልነት ዕጩ ሆነው ቀርበው የነበሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተተኩ። ዶ/ር ሳሙኤል ከምርጫው ራሳቸውን ያገለሉት “በግል ምክንያት” እንደሆነ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል ገዢው ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ለፓርላማ እንዲወዳደሩ ካቀረባቸው 20 ዕጩዎች መካከል አንዱ ነበሩ። ዕጩው በስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲን በመወከል ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ተመርጠው እንደነበር ይታወሳል።

ብልጽግና ፓርቲ ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ይፋ ባደረገው የዕጩዎች ዝርዝር፤ ዶ/ር ሳሙኤል ፓርቲውን በመወከል በአራዳ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ምርጫ ክልል 2 እና 14 ለፓርላማ እንደሚወዳደሩ አስታውቆ ነበር። ዶ/ር ሳሙኤል ገዢው ፓርቲ ባዘጋጃቸው የዕጩዎች ማስተዋወቂያ ይፋዊ መድረኮች ላይ በመገኘት ተወዳዳሪነታቸውን አረጋግጠዋል።
ሆኖም የእርሳቸው ዕጩነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነታቸው ጋር የሚቃረን መሆኑን በህግ በማስደገፍ የገለጹ ወገኖች ተወዳዳሪነታቸውን ጥያቄ ውስጥ ከተውታል። እነዚህ ወገኖች የሚጠቅሱት ድንጋጌ፤ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎችን ለመደንገግ በ2016 ዓ.ም በወጣ አዋጅ ላይ የተካተተ ነው።
የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሹመትን የሚመለከተው የአዋጁ ክፍል በመስፈርትነት ካስቀመጣቸው ጉዳዮች አንዱ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ጋር የተያያዘ ነው። ይኸው መስፈርት ክፍል ለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትነት የሚሾም ግለሰብ “በውድድር ካሸነፈ እና የፖለቲካ ፓርቲ አባል ከሆነ…ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ለመልቀቅ” መስማማት እንዳለበት ይደነግጋል።

ዶ/ር ሳሙኤል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ይህ አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ስራ ላይ ከመዋሉ ሁለት ወራት አስቀድሞ ነበር። ዶ/ር ሳሙኤል ይህን ኃላፊነታቸውን ከመረከባቸው አንድ ወር አስቀድሞ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሐምሌ 2015 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ዶ/ር ሳሙኤል በአዋጁ መሰረት “ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነታቸው መልቀቅ” የሚገባቸው ቢሆንም፤ በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በድጋሚ በዕጩነት ከመቅረብ ወደ ኋላ አላሉም። የዶ/ር ሳሙኤል ፎቶዎች የታተሙባቸው ፖስተሮች በዚህ ሳምንት ጭምር ለምርጫ ቅስቀሳ ሲውሉ ተስተውለዋል።
ሆኖም ዶ/ር ሳሙኤል ራሳቸውን ከምርጫ ያገለሉት ከያዝነው ሚያዝያ ወር መጀመሪያ አንስቶ እንደሆነ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፓርላማ ተወዳዳሪው ራሳቸውን ከምርጫ ያገለሉት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ስለማይፈቅድላቸው እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ “በግል ምክንያት ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በአጭር የጹሁፍ መልዕክት በሰጡት ምላሽ፤ ይህንን የ“ግል ጥያቄያቸውን” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበጎ መልኩ መቀበሉን” ገልጸዋል። በ2013 ዓ.ም በምርጫ ቦርድ የወጣው የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ፣ የድጋፍ ፊርማ አሰባሰብ እና መለያ ምልክት አመራረጥ መመሪያ፤ “አንድ የፖለቲካ ድርጅት ያቀረበው ዕጩ ራሱን ያገለለበት እንደሆነ የዕጩ ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ እስከሚያልቅ ድረስ ሌላ ዕጩ ሊተካ ይችላል” ይላል።
ይኸው መመሪያ “ዕጩው ራሱን ያገለለው የዕጩዎች ምዝገባ ጊዜ ካለቀ በኋላ ከሆነ፤ የፖለቲካ ድርጅቱ ተተኪ ዕጩውን ማቅረብ የሚችለው ለጽምጽ መስጫ ቀን የቀረው ጊዜ አንድ ወር ከሆነ ብቻ ነው” ሲል ያስቀምጣል። ምርጫ ቦርድ የዕጩዎችን ምዝገባ ያጠናቀቀው ከአንድ ወር በፊት የካቲት 16፤ 2018 ዓ.ም እንደነበር ይታወሳል።
ዶ/ር ሳሙኤል በእርሳቸው ምትክ የተተካውን ዕጩ ማንነት እንደማያውቁ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከብልጽግና ፓርቲ የአራዳ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ግን እርሳቸውን የተኳቸው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መሆናቸው አረጋግጧል። በዛሬው ዕለት በጽህፈት ቤቱ ተገኝቶ የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ የዲያቆን ዳንኤል ፎቶ የታተመበት የምርጫ ቅስቀሳ አዲስ ባነር ተመልክቷል።

ዲያቆን ዳንኤል ለፓርላማ ወንበር ሲወዳደሩ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜያቸው ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ በግላቸው የተወዳደሩት በየካ ክፍለ ከተማ ነበር። እርሳቸው የተወዳደሩበት ቦታ፤ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ተወካይ ያላቀረበበት ብቸኛው የአዲስ አበባ ምርጫ ክልል እንደነበር አይዘነጋም።
በዚሁ ምርጫ ዲያቆን ዳንኤል አብረዋቸው ለምርጫ ከቀረቡት የዘጠኝ ፓርቲ ተወካዮች በላይ የሆነ ድምጽ በማግኘት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ተቀላቅለዋል። በወቅቱ ከዲያቆን ዳንኤል ጋር ለምርጫ ቀርበው ከነበሩት ፓርቲዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እናት ፓርቲዎች ይጠቀሳሉ።
በውስጡ 151 የምርጫ ጣቢያዎችን በያዘው ምርጫ ክልል 28፤ በወቅቱ ድምጽ ለመስጠት ተመዘግበው የነበሩት መራጮች ብዛት 176,741 ነበር። በምርጫው ዕለት ድምጽ ከሰጡ መራጮች መካከል 29.3 በመቶ የሚሆኑት ዲያቆን ዳንኤልን መምረጣቸውን ተከትሎ የግል ተወዳዳሪው ፓርላማ መግባት ችለዋል። እርሳቸው ተከትለው ከፍተኛ ድምጽ ያገኙት የባልደራስ የፓርላማ ዕጩ የነበሩት አቶ አምሃ ዳኘው ነበሩ።
የመራጮችን 15.1 በመቶ ድምጽ አግኘተው የነበሩት አቶ አምሃ፤ በወቅቱ የባልደራስ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የኢኮኖሚ ጉዳይ ኃላፊ ነበሩ። አቶ አምሃ ከዚህ ምርጫ አምስት ወራት በኋላ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾመዋል። ባልደራስ በግንቦት 2015 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያደርግ ደግሞ ፓርቲውን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠዋል።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዲያቆን ዳንኤል በሰባተኛው ዙር ምርጫ ይወዳደሩ እንደው ባለፈው መጋቢት ወር ጥያቄ አቅርቦላቸው፤ “ዘንድሮ አልወዳደርም” የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። “አዲስ ማለዳ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን “ዲያቆን ዳንኤል በዘንድሮው ምርጫ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው እንደሚወዳደሩ” በትላንትናው ዕለት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በድጋሚ ጥያቄ የቀረበላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ፤ ዜናው እውነት እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

“ለሌሎች ዕድል ለመስጠት ብዬ የመተው ፍላጎት ነበረኝ። አሁን ሌሎች ዕድል ማግኘታቸውን ስላረጋገጥኩ የብልጽግና ዕጩ ሆኜ ልወዳደር ነው” ሲሉ ዲያቆን ዳንኤል ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በላኩት አጭር የጹሁፍ መልዕክት አስታውቀዋል። ሆኖም ዕጩው ለፓርላማ ወክለው የሚወዳደሩትን የብልጽግና ፓርቲን ከመቼ ጀምሮ እንደተቀላቀሉ ከመግለጽ ተቆጥበዋል። [ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




