የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ እንደተቸገሩ ገለጹ
የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየዓመቱ የሚሰጠው ገንዘብ መዘግየት እና የነዳጅ እጥረት እንዲሁም የፀጥታ ሁኔታ እና የፖለቲካ ጫና የምርጫ ቅስቀሳቸውን በፈለጉት መጠን እንዳያከናውኑ እንቅፋት መሆኑን ገለጹ።
“ምርጫ 2018 - ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሕብር)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ እንዲሁም ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲዎች ለግንቦት 24፣ 2018 ቀን የተቆረጠለት የ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ከሁለት ወር ያነሱ ቀናት ቢቀሩትም፣ በአዲስ አበባ ከመመሪያዎች፣ ከፋይናንስ እና ነዳጅ እጥረት ጋር በተያያዘ፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ከፀጥታ እና ዕጩዎች ላይ የሚደርሱ ማዋከቦችን ጨምሮ በበርካታ ፈተናዎች ሳቢያ ይህ ነው የሚባል የገጽ ለገጽ የምርጫ ቅስቀሳ አለማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የምርጫ ቅስቀሳውን የጀመረው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቅስቀሳው በሚፈልገው መንገድ እየሄደለት አለመሆኑንና የነዳጅ እጥረት ተግዳሮት እንደሆነበት አስታውቋል። ከተሸከርካሪ በተጨማሪ፣ የድምፅ ማጉያ “ስፒከሮችን” ለመከራየት ያደረገው ጥረት “ገዢው ፓርቲ ቀድሞ ይዞታል” የሚል ምላሽ እየተሰጣቸው እንደሚገኝ የትብብሩ የሕዝብ ግንኙነት ምክትል አስተባባሪ አቶ ታጠቅ አሠፋ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ በአደባባይ ሊያደርጉት ያሰቡት ቅስቀሳ በዚህ ምክንያት አደጋ ላይ መውደቁን ያብራሩት...

