የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ እንደተቸገሩ ገለጹ

የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየዓመቱ የሚሰጠው ገንዘብ መዘግየት እና የነዳጅ እጥረት እንዲሁም የፀጥታ ሁኔታ እና የፖለቲካ ጫና የምርጫ ቅስቀሳቸውን በፈለጉት መጠን እንዳያከናውኑ እንቅፋት መሆኑን ገለጹ።

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሕብር)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ እንዲሁም ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲዎች ለግንቦት 24፣ 2018 ቀን የተቆረጠለት የ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ከሁለት ወር ያነሱ ቀናት ቢቀሩትም፣ በአዲስ አበባ ከመመሪያዎች፣ ከፋይናንስ እና ነዳጅ እጥረት ጋር በተያያዘ፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ከፀጥታ እና ዕጩዎች ላይ የሚደርሱ ማዋከቦችን ጨምሮ በበርካታ ፈተናዎች ሳቢያ ይህ ነው የሚባል የገጽ ለገጽ የምርጫ ቅስቀሳ አለማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የምርጫ ቅስቀሳውን የጀመረው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቅስቀሳው በሚፈልገው መንገድ እየሄደለት አለመሆኑንና የነዳጅ እጥረት ተግዳሮት እንደሆነበት አስታውቋል። ከተሸከርካሪ በተጨማሪ፣ የድምፅ ማጉያ “ስፒከሮችን” ለመከራየት ያደረገው ጥረት “ገዢው ፓርቲ ቀድሞ ይዞታል” የሚል ምላሽ እየተሰጣቸው እንደሚገኝ የትብብሩ የሕዝብ ግንኙነት ምክትል አስተባባሪ አቶ ታጠቅ አሠፋ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ በአደባባይ ሊያደርጉት ያሰቡት ቅስቀሳ በዚህ ምክንያት አደጋ ላይ መውደቁን ያብራሩት አቶ ታጠቅ፣ በመዲናዋ ቅስቀሳውን በጀመሩበት ዕለት ከተከራዩት 14 መኪና ውስጥ የተገኘላቸው 2 መኪና ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱም “የተሽከርካሪ ባለቤቶቹ ታርጋችን ይያዛል” የሚል ፍርሐት ስላለባቸው እና “በነዳጅ እጥረት” ምክንያት በሚፈለገው ልክ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ነው ብለዋል።

የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አበራ በቀለም በበኩላቸው፣ ፓርቲው ያለበትን የፋይናንስ ችግር መሠረት ያደረገ ቅስቀሳ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸው፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች “በየመንደሩ ከኅብረተሰቡ ጋር በመገናኘት” ስለ ፓርቲው መረጃ የመስጠት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል። ከሁለት ሳምንት በኋላ ደግሞ በአዲስ አበባ ይፋዊ የአደባባይ ቅስቀሳ እንደሚጀምሩ ተስፋቸውን አጋርተዋል።

ምሥረታውን የአዲስ አበባ ፓርቲ አድርጎ የተመሠረተውና በቅርቡ ሀገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ የተቋቋመው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲም በተመሳሳይ ቅስቀሳ ለማድረግ “የፋይናንስ ችግር ተግዳሮት እንደሆነበት” የገለጹት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኘው ናቸው። ምርጫ ቦርድ ከመንግስት “17 ቢሊዮን ብር” የተመደበለት ቢሆንም፣ “የዛሬ ሦስት ሳምንት ገደማ 8 ሺሕ ብር ብቻ” ተረክበናል የሚሉት አቶ አምሃ፣ “ያለ ፋይናንስ የምርጫ ቅስቀሳ የሚታሰብ አይደለም” ብለዋል።

ፓርቲው ገንዘብ የማያገኝ ከሆነ በአዲስ አበባ ቅስቀሳ ለማድረግ እንደሚቸገር የገለጹት የባልደራስ ፕሬዚዳንት፣ “ማኒፌስቶውን ጭምር ለደጋፊዎቹ ለማስተዋወቅ የፋይናንስ ችግር ተግዳሮት ሆኖበታል። ማኒፌስቶ ለማስተዋወቅ የአዳራሽ ኪራይ ክፍያን ጨምሮ፣ የሕትመትና ተያያዥ ወጪዎችን ፓርቲው መሸፈን አይችልም” ሲሉ አክለዋል።

መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ለመወሰን የወጣው መመሪያ ቁጥር 16/2013 በሚወስነው መሠረት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ዕውቅና ላላቸው ፓርቲዎች ሁሉ የሚከፋፈል፣ እንዲሁም ተወዳዳሪ ፓርቲዎቹ ባቀረቡት ዕጩ ጠቅላላ ብዛት፣ በሴት እና አካል ጉዳተኛ ዕጩዎች ብዛት እንዲሁም ፓርቲዎቹ ባሏቸው የሴት ሥራ አስፈፃሚዎች ብዛት ተጨማሪ የሚከፋፈል የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚሰጥ በመመሪያው ላይ ተገልጿል። ይሁን እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህ ገንዘብ “አነስተኛ ነው” የሚል እና “አልደረሰንም” የሚሉ ቅሬታዎችንም ሲያሰሙ ይደመጣል።

የብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሔር ፓርቲያቸው ምርጫ ቦርድ ከመንግሥት የሚገኘውን ገንዘብ በወቅቱ ሊያደርስላቸው ባለመቻሉ “ቅስቀሳ ማድረግ አልቻልንም” ብለዋል። ፓርቲያቸው የዕጩዎችም ሆነ በሴቶች ተሳትፎ ልክ ከመንግሥት ማግኘት ያለበትን በጀት ማግኘት ባለመቻሉ የአደባባይ ቅስቀሳ ሳያካሄድ ሊቀር እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።

በምርጫ ዝግጅት ወቅት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መለያ ምልክቶች፣ መፈክሮችን የያዙ ፖስተሮች በየመንገዱ እና በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ መለጠፍ፣ በተጨማሪም የዕጩዎች ፎቶግራፎች መለጠፍ ተጠቃሽ ናቸው። ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በመዲናዋ የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስታንዳርድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። አስተዳደሩ የወረቀት ማስታወቂያዎችን በመከልከል የዲጂታል ማስታወቂያዎችን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ይህንን ክልከላ ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም አካል ላይ ከ10 ሺህ ብር እስከ 15 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት እንደሚጥል አስታውቆ ነበር። ይህም ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ አዲስ ፈተና እንደሆነባቸው የሕብር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አበራ በቀለ ተናግረዋል።

አቶ አበራ ጉዳዩን “ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታ አቅርበናል” በማለት፣ እንዲህ ያሉ ክልከላዎች መነሳት አለባቸው ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል። “ከተማ ያቆሽሻል ከሆነ ሌላ አማራጭ መጠቀም ይቻላል፤ መንግሥት ካለን የፋይናንስ አቅም አንፃር የዲጂታል ማስታወቂያዎችን መጠቀም እንደማንችል በማሰብ ሆነ ተብሎ የተደረገ ነው ወደሚል ድምዳሚያ እንድንደርስ የሚያደርግ ገፊ ምክንያት ነው” ሲሉ አክለዋል።

የወረቀት ማስታወቂያዎችን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንለጥፍ የሚል ጥያቄ እያቀረብን ነው ያሉት አቶ አበራ “መለጠፋችን ግን አይቀሬ ነው” ሲሉ አበክረው ተናግረዋል። ቅሬታውን ተመልክቶ ምላሽ እንዲሰጥበት ከቦርዱ በተጨማሪ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረባቸውንና ምላሽ እየጠበቁ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ከማል ሰዒድ በበኩላቸው፣ ባነሮችን እና ማስታወቂያዎችን መለጠፍ መከልከሉን ተከትሎ ለምርጫ ቦርድ በተመሳሳይ መልኩ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸው፣ የከተማ አስተዳደሩም በመንገድ ላይ የሚገኙ ስክሪኖችን በነፃ መጠቀም የሚያስችል አቅጣጫ ቢያስቀምጥም፣ አፈፃፀሙን በተመለከተ ግን የተገለጸ ነገር አለመኖሩን አብራርተዋል። ሲቀጥሉም የምርጫ ቅስቀሳ የአጭር ጊዜ ሥራ በመሆኑ በነፃ ሊደረግ ይገባል የሚል ፅኑ አቋም አንፀባርቀዋል።

የዲጂታል ስክሪኖችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ እንዲጠቀሙ ምርጫ ቦርድ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ የሚናገሩት ደግሞ አቶ ታጠቅ አሠፋ ናቸው። ስክሪኖቹ በክፍያ ዋጋቸው ውድ በመሆኑ መንግሥት “በነፃ እንድንጠቀም” ሊያደርግ ይገባል የሚል ሐሳብ ሰንዝረው፣ ዓላማውም የከተማን ውበት ለመጠበቅ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው ግን “የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምስል” ብቻ የሚያሳዩ ሆነዋል ሲሉ ድርጊቱን ኮንነውታል።

ከአዲስ አበባ ውጭ፣ በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የፀጥታ ችግር ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፈተና መሆኑ ተጠቅሷል። በተጨማሪም ፓርቲዎቹ “በተደራጀ መንገድ” ወከባ ደርሶብናል ሲሉ ይደመጣል። ትላንት ሚያዝያ 9፣ 2018 በዚህ ጉዳይ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ያወጣው ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት፣ ለምርጫ ያስመዘገበው ዕጩ ለእስር መዳረጉን ጨምሮ፣ ሌሎችም የፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ላይ ከፍተኛ ወከባና እንግልት በመንግሥት ኃላፊዎች እና በገዢው ፓርቲ እየተፈፀመበት እንደሆነ ገልጿል።

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ፣ ፓርቲው ቅስቀሳ በጀመረባቸው አንዳንድ የደቡብ ክልል ከተሞች ላይ “የአባላት መታሰር” እንዳጋጠማቸውና የማወከብ ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር እንዲፈቱ መደረጉን ጠቅሰዋል። ፓርቲው የአዲስ አበባ ቅስቀሳውን በቅርቡ እንደሚጀምርም አስታውቀዋል።

ባልደራስም በዘንድሮው ምርጫ በርካታ ዕጩዎች ባቀረበበት የደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቅስቀሳ ለማድረግ እየተቸገረ መሆኑን የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅሰዋል። “ፖስተሮችን ለመለጠፍ በወላይታ እንዲሁም በያቤሎ ተግዳሮት ገጥሞናል፤ ይህንንም የፓርቲው አባላቶች መረጃ እንዲልኩ በማድረግ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቀናል” ብለዋል።

በተመሳሳይ ሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ “እስካሁን እየተደረጉ ባሉት ቅስቀሳዎች በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር እንዲሁም ሐዋሳ የተወሰኑ መዋከቦች ደርሶብናል” የሚል ወቀሳ ሰንዝሯል። የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አበራ በቀለ በደቡብ ክልሎች በጎፋ አካባቢ በፓርቲው አባላቶች ላይ እስር ማጋጠሙን ገልጸዋል። የመንግሥት የታችኛው መዋቅር ከፍተኛ የሆነ “ማዋከብ” እና “ማመናጨቅ” እያደረሰብን ነው ሲሉም የገጠማቸውን ጫና አውግዘዋል።

እንደ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ፣ እስካሁን ደምቆ መታየት ያልቻለው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፓርቲዎች የቅስቀሳ ጊዜ በይፋ የጀመረው ታኅሣሥ 30 ሲሆን፣ የሚጠናቀቀውም በግንቦት 19 እንደሚሆን ይጠበቃል። የድምፅ መስጫው ቀን ከመድረሱ 4 ቀናት አስቀድሞ ማንኛውንም ዓይነት የቅስቀሳ ተግባር በአካል፣ በቤት፣ በስብሰባ ወይም በኢንተርኔት እና በማኅበራዊ ሚዲያ ማካሔድ በጥብቅ የተከለከለ ይሆናል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]