ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲ በዘንድሮው 7ኛው ጠቅላላ ሀገር አቀፍ ምርጫ “በውስጥ በነበሩ መከፋፈሎች” ውስጥ ሆኖም ለምርጫ እየተዘጋጀ መሆኑን የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አምሃ ዳኜ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ፕሬዚዳንቱ በውስጣዊ መከፋፈሉ ሳቢያ በበቂ ሁኔታ ዝግጅት ማድረግ ባይችሉም፣ ፓርቲው 300 የሚሆኑ ዕጩዎችን ለምርጫ ውድድር አስመዝግቧል ብለዋል።
“ከዓመት በላይ ስንካሰስ የቆየን በመሆኑ፣ ቢሯችን በላያችን ላይ በመፍረሱ፣ እንዲሁም የባንክ አካውንታችን በመዘጋቱ፣ በዚሁ ሁሉ ችግር ውስጥ [የምርጫ] ዝግጅት እያደረግን ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ባልደራስ በውስጥ ክፍፍሉ ምክንያት፣ ከውጪ ገንዘብ ይልኩለት የነበሩት እና በቀድሞው የፓርቲው ፕሬዚዳንት የተቋቋመው የባልደራስ የሰሜን አሜሪካ ደጋፊ የሚባለው ቡድን አባላት ድጋፋቸውን ካቋረጡ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆናቸውም ጨምረው ገልጸዋል። አቶ አምሃ ዳኜ፣ በክፍፍሉ ሳቢያ ወደ “ሦስት ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ” በፍርድ ቤት እንደታገደባቸውም ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ፣ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ፣ የክፍፍሉ መንስዔ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት እና አፈ ጉባዔ፣ ምልዓተ ጉባኤው ያልተሟላበት የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ በማድረግ የአመራር ለውጥ በማድረጋቸው መሆኑን በመግለጽ ተችተዋል።
አቶ አምሃ ግን ልዩነቱ የተፈጠረው “በውጭ ያሉት ደጋፊዎቹ እና በሀገር ውስጥ ያሉት የተወሰኑ አባላት አንድ ላይ ሆነው ባልደራስን በማፍረስ እነሱ ወደሚፈልጉት ዓላማ ለመውሰድ ያደረጉትን ጥረት አንቀበልም፤ ውጪ ሆናችሁ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ልትዘውሩ አትችሉም” በማለታችን ነው ብለው ይከራከራሉ።
የክፍፍሉ መነሻ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ታህሳስ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ያደረገው የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ እና በዚያ ስብሰባ ላይ ያደረገው የአመራር ለውጥ መሆኑን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የፍርድ ቤት ሰነድ ያመለክታል። ይህንን የፓርቲውን ውሳኔ በመቃወም 15 የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ‘የተደረገው ስብሰባ ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ውጪ በመሆኑ ቦርዱ ጉዳዩን እንዲመረምርልን’ በማለት አቤቱታ አቅርበዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የዚህን ስብሰባ ውጤት መርምሮ “ፓርቲው በድጋሚ ሕጋዊ ስብሰባ እንዲያደርግ” በመወሰኑ፣ ባልደራስ በቦርዱ ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱ ታውቋል።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው በባልደራስ እና በምርጫ ቦርድ መካከል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ልደታ ምድብ፣ የምርጫ ችሎት የተደረገው ክርክር እንደሚያመለክተው፣ ይግባኝ ባዩ ባልደራስ መልስ ሰጪው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ስብሰባ እና አዲስ የተመረጡ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሹመት ሳያፀድቅ ቀርቶ፣ በድጋሚ ጉባኤው እንዲካሄድ መወሰኑን ተቃውሞ ተከራክሯል።
ፓርቲው ስብሰባውን የጠራው ለሁለት ጊዜያት ምልዓተ ጉባኤ ሳይሟላ በመቅረቱ፣ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ለ3ኛ ጊዜ በተገኙ አባላት ስብሰባ ለማካሄድ በሚፈቅደው ድንጋጌ መሠረት እንደሆነ ገልጾ ተከራክሯል። በተጨማሪም፣ ቅሬታ ያቀረቡት 15 አባላት ፊርማቸው “ትክክል አይደለም” በሚል በፎረንሲክ እንዲመረመር ጠይቆ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ቦርዱ በሰጠው መልስ ፓርቲው ለስብሰባው ያልተገኙ አባላት በአግባቡ ስለመጠራታቸውና መጥሪያው ስለመድረሱ የሚያሳይ በፊርማ የተረጋገጠ ማስረጃ ማቅረብ አለመቻሉን፤ ፊርማቸው እውነተኝነቱ የተጠረጠሩት አባላት በቦርዱ በአካል ቀርበው ፊርማው የራሳቸው መሆኑን ስላረጋገጡ፣ የፎረንሲክ ምርመራ የማያስፈልግ ስለመሆኑ፤ እንዲሁም፣ የፓርቲው ሥልጣን ያላቸው አካላት (ፕሬዚዳንቱ እና አፈ ጉባኤው) የፈጸሙት ተግባር ከመተዳደሪያ ደንቡ ውጭ መሆኑን ጠቅሶ ተከራክሯል።
ፍርድ ቤቱም በታህሳስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት፣ ቦርዱ ፓርቲው ያደረገውን ጉባኤ ውድቅ በማድረግ ያሳለፈውን ውሳኔ ፍርድ ቤቱም አፅንቶታል።
አቶ አምሃ ግን “በደንቡ መሠረት ማንኛውም የፓርቲ ኮሚቴ መገኘት ካልቻለ በተገኙት ይወሰናል” በማለት አሁንም በቦርዱ እና ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ያላቸውን ቅሬታ አልሸሸጉም። “ይህንን አፅድቆ የሰጠን ምርጫ ቦርድ ነው” ነገር ግን “በሦስተኛ ጊዜ ምክር ቤቱ ካለው 30 አባላት ውስጥ 6 ሰው በመገኘቱ በደንቡ መሠረት ባለው ቁጥር የተጓደለው ኃላፊ ቦታ ላይ ሰው ተክተናል” ይሁን እንጂ በዚህ ውሳኔያችን ላይ 15 የሚሆኑ አባላት ቅሬታቸውን አንስተዋል ብለዋል።
ይልቁንም አቶ አምሃ “ፓርቲው በተማረ ሰው ይመራ፣ እንዲሁም ሁልጊዜ ከፖሊስ ጋር እየተጋጩ መታሰር መገለጫችን አይሁን የሚል ሐሳብ በማንሳታችን ጉዳዩን ወደ ቦርዱ በመውሰድ ሊከሱን ችለዋል” በማለት የክፍፍሉ መንስዔ የፍርድ ቤት ክርክር ከተደረገበት የምልዓተ ጉባኤ ጉዳይ የተለየ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በፓርቲው ክፍፍል ውስጥ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅሬታቸውን ካቀረቡት 15 አባላት መካከል የፓርቲውን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር በቃሉ አጥናፉን አነጋግራለች። ዶ/ር በቃሉ፣ የክፍፍሉ መነሻ “የአመራር ክፍተት ነው” ያሉ ሲሆን፣ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊው መመረጥ “የፓርቲው ምክር ቤት ሳያፀድቀው የተደረገበት አካሄድ ስህተት ነው” ብለዋል። ምርጫ ቦርድ በፕሬዚዳንቱ የተደረገውን ምርጫ ያላፀደቀው “የምርጫ ሂደቱ ከመሠረቱም ስህተት የነበረ በመሆኑ ነው” ይላሉ።
አብዛኛዎቹ የምክር ቤት አባላቱ ወጣቶች መሆናቸውን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ከወጣት የምክር ቤት አባላት ጋር የፓርቲው ፕሬዚዳንት “እልህ” በመጋባታቸው የተነሳ ችግሩ ሊፈጠር ችሏል ይላሉ። ወጣቶቹም በተፈጠረው ችግር ምክንያት ወደ ቦርዱ በመሄድ ውሳኔው እንዳይፀድቅ ማድረግ ችለዋልም ሲሉ ያስረዳሉ።
7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ባልደራስ የሚያቀርባቸውን ዕጩዎች በቅድሚያ ሥራ አስፈጻሚው፣ በመቀጠልም ምክር ቤቱ አፅድቆት መሆን ሲገባው ከአንድ ዓመት በላይ ያልተሰበሰበው ምክር ቤት ሳያፀድቀው ዕጩ ቀርቧል መባሉን እንደማይቀበሉትና ጉዳዩን ለግልግል ወደ ምርጫ ቦርድ መውሰዳቸውን ዶ/ር በቃሉ ተናግረዋል።
የፍርድ ቤት ሂደቱን ማስፈጸምም ሆነ ዕጩዎችን በተመለከተ ቅሬታ አቅራቢ የፓርቲው አባላት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እየጠበቁ መሆኑንና ባልደራስ የተጋረጠበትን አደጋ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው እየሠሩ መሆኑን ዶ/ር በቃሉ አክለው ገልጸዋል።
“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ በይፋ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ተመዝግቦ መንቀሳቀስ የጀመረው በጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ነው። ባልደራስ ሲመሰረት ክልላዊ ፓርቲ ሆኖ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ብቻ አባላትን መልምሎ ይንቀሳቀስ ነበር። የፓርቲው ዋና መስራችና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ናቸው።
እስክንድር ሐምሌ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ለፓርቲያቸው በጻፉት ደብዳቤ “በመንግሥት ጫና በአባልነትም ሆነ በአመራርነት መሥራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ” በሚል ራሳቸውን ከአባልነት ካገለሉ በኋላ፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል የትጥቅ ትግል ከሚመሩ ቡድኖች ጋር በመቀላቀል ከሰላማዊ ፖለቲካ መውጣታቸው ታውቋል። ሆኖም፣ ፓርቲያቸው ከክልላዊ ፓርቲነት ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት በመሸጋገር፣ አቶ አምሃ ዳኜን ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧቸዋል። የባልደራስን ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት መሸጋገር ምርጫ ቦርድ በነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም በሰጣቸው ሰርተፊኬት አረጋግጧል።
ፓርቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ የተሳተፈው በ2013 ዓ.ም በተካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ሀገር አቀፍ ምርጫ ነበር፤ የወቅቱ ፕሬዚዳንት እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎችም ከእስር ቤት ሆነው በተወዳደሩበት በዚህ ምርጫ፣ ባልደራስ ከብልፅግና ቀጥሎ ከፍተኛውን ሁለተኛ የመራጮች ድምፅ በአዲስ አበባ ማግኘቱ ይታወሳል።
“በስድስተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ሁለተኛ የወጣን ቢሆንም በተሠራብን ሸፍጥ የፓርቲው ቢሮ ኪራይ ከነበረበት 80 ሺህ ወደ 400 ሺህ በአንድ ጊዜ እንዲጨምር ተደርጎብናል” የሚሉት አቶ አምሃ፣ “ለብዙ ዓመታት በአራት ኪሎ አካባቢ የነበረውን ቢሮ በመልቀቅ ወደ ቸርቸል ጎዳና የመጣን ቢሆንም፣ ቤቱ እንዲፈርስ ተደርጓል” ሲሉ በሀዘኔታ ይገልጻሉ። ፓርቲው በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በ75 ሺህ ብር ቢሮ ተከራይቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ሆነው ለ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አምሃ፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ 300 የሚሆኑ ዕጩዎችን ለዘንድሮው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ አቅርቧል፤ ከእነዚህ ውስጥ 60 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ እንዲሁም 240 የሚሆኑት ዕጩዎቹን ደግሞ ለክልል ምክር ቤት ማቅረቡን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል። እንደ አቶ አምሃ፣ ፓርቲው በገጠመው ውስጣዊ ክፍፍል ሳቢያ፣ ያቀረባቸው ዕጩዎች ቁጥር ከመቀነሱም ባሻገር፣ እንቅስቃሴውን በደቡብ አካባቢ ማድረጉን ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ ጨምረው እንደገለጹት፣ በአማራ እና በአፋር ክልል ዕጩዎችን የማስመዝገብ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለዕጩዎቻቸው ደኅንነት በመስጋት ለመወዳደር ፈቃደኛ አይደሉም።
ይህ ዜና ታትሞ ከተሰራጨ በኋላ የተጨመረ መረጃ
የባልደራስ ፕሬዚዳንት አቶ አምሃ ዳኘው፣ በዚህ ዜና ላይ የተጠቀሱት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ በገዛ ፈቃዳቸው ፓርቲውን ከለቀቁ ከ11 ወራት በኋላ የፓርቲው ምክትል ፕሬዘዳንት ተብለው መጠቀሳቸውን በመቃወም ለዝግጅት ክፍላችን ቅሬታ አቅርበዋል። በዚህም መሠረት ዜናው እንዲታረምላቸው ጠይቀዋል። “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጉዳዩን የበለጠ ለማጣራት ባደረገችው ሙከራ ዶ/ር በቃሉ መልቀቂያ ማስገባታቸውን አምነው፣ ነገር ግን በሌሎች አባላት ግፊት መልቀቂያቸውን መሰረዛቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለፓርቲው ማስገባታቸውን ገልጸውልናል። አቶ አምሃም ደብዳቤውን መቀበላቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ይህ ዶ/ር በቃሉን ወደ ምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው ሳይሆን ወደ አባልነት ብቻ እንደሚመልሳቸው በመግለጽ አስተባብለዋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]



