የአብን የፓርላማ አባሉ ዶ/ር አበባው ደሳለው በመጪው ምርጫ ኢሕአፓን ወክለው ሊወዳደሩ ነው

በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ወክለው የፓርላማ አባል የሆኑት ዶ/ር አበባው ደሳለው፤ በመጪው ምርጫ ኢሕአፓን ወክለው ሊወዳደሩ ነው። የአብን የአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ይህዓለም ታምሩም በተመሳሳይ መልኩ የፓርቲ ለውጥ አድርገው በመጪው ምርጫ እንደሚቀርቡ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 3፤ 2018 ማምሻውን በበይነ መረብ በሰጠው መግለጫ ሁለቱ ቀድሞ የአብን አባላት ፓርቲውን መቀላቀላቸውን ይፋ አድርጓል። በበይነ መረብ የተካሄደውን መግለጫ ከሁለቱ የምርጫ ተወዳዳሪዎች ጋር በመሆን የሰጡት፤ የኢሕአፓ ዋና ጸሐፊ ሚስጥረስላሴ ታምራት ናቸው።

ሁለቱ የቀድሞ የአብን አባላት ለዘንድሮው ምርጫ በእጩነት የተመዘገቡት፤ ኢሕአፓ አባል በሆነበት “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” በተሰኘው የፓርቲዎች ቅንጅት በኩል መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ባለፈው መስከረም ወር የተመሰረተው ይህ የፓርቲዎች ቅንጅት፤ ከኢሕአፓ በተጨማሪ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ አባል የሆኑበት ነው።

በቅንጅቱ ተካትቶ የነበረው እናት ፓርቲ፤ በዚህ የፓርቲዎች ስብስብ ውስጥ አባል መሆኑን በተመለከተ በፓርቲው ጉባኤው ከማስጸደቅ አንጻር ያላሟላው ሂደት በመኖሩ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እግድ ተጥሎበታል። እናት ፓርቲ ሂደቱን ሲያሟላ የስብስቡ አምስተኛ አባል መሆን እንደሚችል ምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል።

ዶ/ር አበባው እና ዶ/ር ይህዓለም “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” በተሰኘው የፓርቲዎች ቅንጅት ስር ለምርጫ የሚወዳደሩት በአዲስ አበባ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች መሆኑን ገልጸዋል። ሆኖም ዕጩዎቹ የትኛው የምርጫ ጣቢያ ላይ እንደሚወዳደሩ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በአማራ ክልል በሚገኘው ጅጋ የምርጫ ክልል አብንን በመወከል ለፓርላማ ተወዳድረው ያሸነፉት ዶ/ር አበባው፤ በዘንድሮው ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ በአዲስ አበባ ለመወዳደር የወሰኑት አስቀድሞ በተወዳደሩበት አካባቢ ደግመው ለመወዳደር “አስቻይ ሁኔታ ባለመኖሩ” እንደሆነ አስረድተዋል። ባለፈው ምርጫ በአማራ ክልል የፍኖተ ሰላም ምርጫ ክልል ተወዳዳሪ የነበሩት ዶ/ር ይህዓለም ታምሩም እንዲሁ በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ በአዲስ አበባ ለመወዳደራቸው ተመሳሳይ ምክንያት አቅርበዋል።

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፤ 42 ፓርቲዎች በተናጠል፣ 15 በቅንጅት እንዲሁም አንድ ግንባር ለመጪው ምርጫ መመዝገባቸውን አስታውቆ ነበር። ባለፈው ህዳር ወር በወጣው ይፋዊ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እሁድ የካቲት 1 ይጠናቀቅ የነበረውን የዕጩዎች ምዝገባ፤ ቦርዱ እስከ የካቲት 16 ማራዘሙም ይታወሳል።    

ሁለቱ የ“ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” ዕጩዎች ከአብን መውጣታቸውን ቢገልጹም፤ ለፓርቲው በይፋ መልቀቂያ እንዳላስገቡ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዛሬው የበይነ-መረብ መግለጫ ላይ ዶ/ር አበባው “ባለፉት አራት አመታት ከአብን አመራሮች ጋር በፍጹም ተገናኝቼ አላውቅም” ሲሉ ተደምጠዋል። 

“ፓርላማ ስንገባ ጀምሮ የአብን አመራሮች አግኝተው ተልዕኮ ሰጥተውን አያውቁም። ተወያይተን አናውቅም። ስንንቀሳቀስ የነበረው በግል እንደህዝብ ተወካይነት እንጂ እንደፓርቲ አልነበረም” ሲሉም የጅጋ ምርጫ ክልል ተመራጩ አክለዋል። በፓርቲ መንቀሳቀስ “በጣም አስፈላጊ” እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር አበባው፤ ኢሕአፓን ለመቀላቀል የወሰኑት በአሁኑ ወቅት “የተሻለ ትግል በማድረግ ላይ ያለ ፓርቲ እንደሆነ” ስላመኑበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ዶ/ር ይህዓለም ከአብን የወጡበት ምክንያት፤ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ካተካሄደ በኋላ ፓርቲው ለሚታገልለት ማህበረሰብ መታገል በሚገባው ልክ “መታገል ስላልቻለ” እንደሆነ አስረድተዋል። “ፓርቲው ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም ብዬ ስላመንኩ በግሌ በራሴ [ከአባልነት ለቅቄያለሁ]” ሲሉ የቀድሞው የአብን የአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አስታውቀዋል።

ባለፈው ምርጫ ለፓርላማ እና ለአማራ ክልል ምክር ቤት በርከት ያሉ ተወካዮቹን ካስመረጠው አብን ራሳቸውን ያገለሉት ዶ/ር ይህዓለም እና ዶ/ር አበባው ብቻ አይደሉም። አብንን በመወከል በባህር ዳር ከተማ ምርጫ ክልል ተመርጠው ላለፈው አራት ዓመት ተኩል በፓርላማ የቆዩት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ በመጪው ምርጫ እንደማይወዳደሩ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

ዶ/ር ደሳለኝ ራሳቸውን ለምርጫ በዕጩነት ላለማቅረብ የወሰኑት ነጻ፣ ሰላማዊ እና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል “ምቹ መደላድል ባለመኖሩ” ምክንያት እንደሆነ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰራጩት መግለጫው አመልክተዋል። ዶ/ር ደሳለኝ በዚሁ መግለጫቸው፤ በመጪው ምርጫ ለመወዳደር በባህር ዳር አሊያም በአዲስ አበባ በዕጩነት እንዲቀርቡ ከ“አንዳንድ ፓርቲዎች” ዕድሉ ተሰጥቷቸው እንደነበር እና ይህንኑ አለመቀበላቸውን በዚሁ መግለጫቸው ላይ ጠቅሰው ነበር። ( ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)