ለ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫለፓርላማ እና ለክልል ምክር ቤቶች ከሚወዳደሩ 80 የግል ዕጩዎች መካከል፣ 43ቱ (54%) ከሱማሊ ክልል እንደሆኑ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው ሰርተፊኬት የተሰጣቸው ዕጩዎች ዝርዝር አመላከተ። ከ43ቱ የግል ተወዳዳ ዕጩዎች 39ኙ ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ ሲሆን፣ 4ቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ይወዳደራሉ።
ግንቦት 24፣ 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 80 ፖለቲከኞች የግል ዕጩ ሆነው መቅረባቸውን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከምርጫ ቦርድ መረጃ ለመመልከት ችላለች።
ከነዚህም ውስጥ 25ቱ ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሚወዳደሩ ሲሆን 55ቱ ደግሞ ለክልል ምክር ቤቶች እንደሚወዳደሩ ታውቋል።
ዕጩዎቹ በ7 ክልልሎች እና በ2 የከተማ አስተዳደሮች የሚወዳደሩ ሲሆን፣ ምርጫ በሚካሄድባቸው ቀሪዎቹ 4 ክልሎች ውስጥ አንድም የግል ዕጩ አልተመዘገበም። የግል ዕጩዎች የተመዘገቡባቸው ክልሎች አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሐረሪ፣ ሶማሌ እና ደቡብ ኢትዮጵያ እንዲሁም አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ናቸው። የግል ዕጩ ያልቀረበቡባቸው ክልሎች ደግሞ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ እና ሲዳማ ክልሎች ናቸው።

ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል በኦሮሚያ 11፣ በአዲስ አበባ 10፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ 5፣ በደቡብ ኢትዮጵያ 4፣ እንዲሁም በአማራ፣ በድሬዳዋ እና በሐረሪ ክልሎች በእያንዳቸው ሁለት፣ ሁለት የግል ዕጩዎች የሚወዳደሩ ሲሆን፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ደግሞ አንድ ዕጩ በግል የሚወዳደሩ ይሆናል።
በግል ዕጩነት ከቀረቡት መካከልም የቀድሞዎቹ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራሮች አቶ ቀጀላ መርዳሳ እና አቶ አራርሳ ቢቂላ በሚወዳደሩባቸው መንዲ እና ደደር 2 የምርጫ ክልሎች ያለማንም ተቀናቃኝ ብቻቸውን እንደሚወዳደሩ ታውቋል።
የመጀመሪያ በሆነው የ1987 ምርጫ 960 የሚሆኑ የግል ዕጩዎች ተወዳዳሪ የነበሩ ሲሆን፣ 10 ያህሉ የፓርላማ ወንበር ለማሸነፍ ችለዋል።
በ1992 ዓ.ም. በተካሄደዉ ሁለተኛው ምርጫ በግል ከተወዳደሩ 490 ዕጩዎች 13 ዕጩዎች አሸንፈው ፓርላማ ገብተዋል።
በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ልዩ ቦታ በሚሰጠው በምርጫ 97 የግል ተወዳዳሪ ዕጩዎች ቁጥር ቀንሶ ወደ 353 ወርዶ ነበር። ከዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በስተቀር ለምክር ቤት አባልነት ያሸነፈ ዕጩ አልነበረም።
በ2002 ዓ.ም. በተካሄደው አራተኛው ምርጫ የግል ዕጩዎች ብዛት ደግሞ 34 ብቻ እንደነበሩ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን፣ በውጤቱም ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ብቸኛው የግል ተመራጭ መሆናቸው የሚታወስ ነው።
በ2007 ዓ.ም የፓርላማ መቀመጫ ለማግኘት ራሳቸውን ዕጩ ያደረጉ የግል ተወዳዳሪዎች ብዛት እያሽቆለቆለ መጥቶ 5 ብቻ ቢቀርቡም፣ አንዳቸውም ተመራጭ ሆነው ወደ ፓርላማ መግባት አልቻሉም።
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ 125 የግል ዕጩዎች የተወዳደሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የሚገኙ ሲሆን፣ በዘንድሮው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ብልፅግናን ተቀላቅለው እንደ ሚወዳደሩ ለ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መዘገቧ አይዘነጋም።
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተመዘገቡት የግል ዕጩዎች ቁጥር ከምርጫ 2002 እና 2007 ቀጥሎ ዝቅተኛው ነው።
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በግል ዕጩ ሆነው ከቀረቡ በቀድሞው ተሳትፏቸው በሰፊው ከሚታወቁ ግለሰቦች መካከል ዶክተር ዲማ ኖጎ፣ ኡስታዝ ከሚል ሸምሱ፣ ቀጀላ መርዳሳ፣ አራርሶ ቢቂላ እና ዳንኤል ጌታቸው ይገኙበታል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]



