በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ፣ ለክልል ምክር ቤቶች የሚቀርቡ ዕጩዎችን ዝርዝር “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት አጠናቅራዋለች። በዚህ የዕጩዎች መረጃ መሠረት ሲዳማ ክልል ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ክልላዊ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል የዕጩዎች ብዛት በማቅረብ ከፍተኛ ፉክክር የሚጠበቅበት ክልል ሆኗል።
በአንጻሩ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ (በድምሩ አምስት) ክልሎች እና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤቶች ካሏቸው መቀመጫዎች መካከል ከግማሽ በላይ ዕጩዎችን ያቀረበው ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ብቻ መሆኑን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከምርጫ ቦርድ ሰነድ ተመልክታለች።
የዕጩነት ሰርተፊኬት በተሰጣቸው ዕጩዎች ዝርዝር ለመረዳት እንደሚቻለው፣ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ካሉት 190 መቀመጫዎች መካከል ቢያንስ ግማሹን መሙላት የሚችሉ ዕጩዎችን ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ማቅረብ ችለዋል። በዚህም ክልሉ በከፍተኛ የፓርቲዎች ፉክክር ቀዳሚነቱን ይዟል።
በሲዳማ ክልል መንግሥት ለመመሥረት በሚያስችል የዕጩዎች ብዛት የቀረቡት ፓርቲዎች ሰባት ፓርቲዎች መካከል ብልፅግና ፓርቲ በ175 ዕጩዎች ቀዳሚነቱን ይዟል። በመቀጠልም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በ162 ዕጩዎች፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በ148 ዕጩዎች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በ146 ዕጩዎች ለፉክክር ቀርበዋል። በተጨማሪም የሲዳማ ሕዝብ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ድርጅት 141 ዕጩዎችን ያስመዘገበ ሲሆን፣ ሲዳማ አንድነት ፓርቲ 106 ዕጩዎችን፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ደግሞ 96 ዕጩዎችን በማቅረብ ለክልል ምክር ቤት ውድድር ተዘጋጅተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ብልፅግና ፓርቲ በተወዳዳሪ ዕጩ ብዛት በተቃዋሚዎች የተበለጠበት ብቸኛው ምክር ቤት ሆኗል። ከሲዳማ ክልል በመቀጠል በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤት ካሉት 158 መቀመጫዎች ውስጥ ለ143ቱ ዕጩዎችን በማስመዝገብ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ቀዳሚነቱን ሲይዝ፣ ሕዳሴ ፓርቲ 142 ዕጩዎችን በማቅረብ ተከትሏል።
ብልፅግና ለአዲስ አበባ የከተማ መስተዳድር ምክር ቤት 134 እና ኢዜማ 106 ዕጩዎችን አስመዝግበዋል።
በአፋር ክልል ደግሞ ብልፅግና (129)፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ (96)፣ የአፋር ነፃ አውጪ ግንባር (78) እና አርጎባ አንድነት ጀበርቲ (72) ዕጩዎችን አቅርበዋል። ክልሉ 142 መቀመጫዎች አሉት።
በደቡብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ሦስት ሦስት ፓርቲዎች ለክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ከግማሽ በላይ ዕጩዎችን አቅርበዋል። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብልፅግና እና ኢዜማ እኩል 144 ዕጩዎችን ሲያስመዘግቡ፣ ነእፓ 91 ዕጩዎችን በማቅረብ ይፎካከራቸዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ደግሞ ብልፅግና፣ ኢዜማ እና ትብብር በተከታታይ 201፣ 169 እና 141 ዕጩዎችን በማቅረብ ይፎካከራሉ
በተመሳሳይ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ሶማሊ ክልሎች ውስጥ ሁለት ሁለት ፓርቲዎች ከግማሽ በላይ ዕጩዎችን ያስመዘገቡ ሲሆን፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብልፅግና (148) እና ኢዜማ (104)፣ በሶማሊ ክልል ደግሞ ብልፅግና (232) እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ – 161) ዕጩዎችን አቅርበዋል።
ብልፅግና ምርጫ ከማይካሄድበት ትግራይ ክልል በቀር፣ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች መንግሥት ለመመሥረት በሚያስችል የዕጩ ብዛት ሲወዳደር፣ ኢዜማ በአምስቱ እና ትብብር በሦስት ክልል ምክር ቤቶች መንግሥት በመመሥረት አቅም ይፎካከራሉ። የአዲስ አበባ ምክር ቤት 20 የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ጋምቤላ 4 የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ዕጩዎቻቸውን ያቀረቡበት የክልል ምክር ቤት በመሆን እጅግ ዝቅተኛ ፉክክር ያስተናግዳል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




