ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዕጩዎችን ያስመዘገቡ ፓርቲዎች እነማን ናቸው?
ለ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዕጩዎችን ያስመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር ይፋ ሆኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከቀናት በፊት ባወጣው መረጃ መሠረት፤ ገዢው ብልፅግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (የአምስት ፓርቲዎች ስብስብ) ፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) እንዲሁም ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት (የስምንት ፓርቲዎች ስብስብ) ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዕጩዎችን በማስመዝገብ በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በግል ተወዳዳሪዎች የቀረቡ አጠቃላይ ዕጩዎች ቁጥር 10,432 ደርሷል። ከእነዚህ ውስጥ 3,041 (29%) ዕጩዎችን በማስመዝገብ ብልፅግና ፓርቲ ቀዳሚ ሲሆን፤ ኢዜማ 1,248 (12%) እንዲሁም ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት 1,053 (10%) ዕጩዎችን ለውድድር አቅርበዋል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ዕጩዎችን በማቅረብ ረገድም ገዢው ብልፅግና ፓርቲ 461 ዕጩዎችን በማስመዝገብ ከጠቅላላው 547 የፓርላማ ወንበሮች 84 በመቶ ለሚሆኑት ዕጩ ማቅረብ ችሏል። በተመሳሳይ ኢዜማ 293 ዕጩዎችን በማስመዝገብ ለ54 በመቶ የፓርላማ ወንበሮች ተወዳዳሪዎችን አቅርቧል።
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ እንዲሁም ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት ለፓርላማ ወንበሮች ያቀረቧቸው ዕጩዎች ከፓርላማው የወንበሮች ብዛት ግማሽ (50%) በታች ናቸው።
በአጠቃላይ የዕጩዎች ቁጥር አምስተኛ ደረጃ ላይ የነበረው ሰላም ለኢትዮጵያ ጥምረት፣ ለፓርላማ ባቀረባቸው ዕጩዎች ብዛት በወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተበልጦ ወደ ስድስተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




