የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ቁሳቁሶች እሸጋ መርሀ ግብርን ለመገናኛ ብዙኃን አባላት አስጎበኘ

‎የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ተኛውን ሀገራዊ ምርጫንና በተለይም የመራጮች ምዝገባን ለማካሄድ አስፈላጊ የሆኑ የምርጫ ቁሳቁሶችን የእሸጋ መርሃ ግብር በመጪዉ አሁድ እንደሚያጠናቅቅ ገለጸ። ቦርዱ ዛሬ የካቲት 13 ቀን 2018 ዓ.ም በየኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነትና የሎጂስቲክስ አገልገሎት ቅጥር ግቢ በሚገኘዉ መጋዘን የሚካሄደውን የምርጫ ቁሳቁሶች እሸጋ መርሀ ግብርን ለመገናኛ ብዙኃን አባላት አስጎብኝቷል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት የቦርዱ የምርጫ ሎጂስቲክስ ኃላፊ መላኩ አሉላ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በአሁኑ ጊዜ ቦርዱ የምርጫ ቁሳቁሶችን በሦስት መጋዘኖች አከማችቶ ለስርጭት ዝግጁ እንዲሆኑ የማሸግ ሥራን በማከናወን ላይ ይገኛል። ቦርዱ በአጠቃላይ ወደ 52720 አካባቢ የምርጫ ጣቢያዎች አሉት። በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች የሚሰራጩ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁሶች በ8200 ካሬ ላይ ባረፉ ሦስት መጋዘኖች በማሸግ ላይ እንደሆነ የቦርዱ የምርጫ ሎጂስቲክስ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡ በየኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነትና የሎጂስቲክስ አገልገሎት ቅጥር ግቢ በሚገኘውና 2200 ካሬ ሜትር ላይ ባረፈው  መጋዘን  ከሀገር ውስጥና በተለይም ከውጭ ሀገር የተገዙ የምርጫ ቁሳቁሶች እሸጋ በመካሄድ ላይ ነው።

መላኩ እንዳሉት በየኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነትና የሎጂስቲክስ አገልገሎት ቅጥር ግቢ በሚገኘው መጋዘን የሚታሸጉት የምርጫ ቁሳቁሶች በአማራ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ክልሎች ለሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ነው፡፡ ሌላው 3600 ካሬ ላይ ባረፈውና ቃሊቲ አካባቢ በሚገኘው መጋዘን በኦሮሚያና ሀረሪ ክልሎች፣ እንደሁም በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች እሸጋ እየተካሄደነም ገልጸዋል፡፡ እንደመላኩ ገለጻ የሌሎቹ ቀሪ ሰባት ክልሎች ደግሞ በቃሊቲ አካባቢ በሚገኘውና 2600 ካሬ ላይ ባረፈው መጋዘን እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ‎አስከአሁን የእሸጋ ሥራው 40 ከመቶ አካበቢ የተጠናቀቀ ሲሆን በመጪው እሁድ ሙሉለሙሉ ተጠናቆ የምርጫ ቁሳቁሶቹ ለስርጭት ዝግጁ እንደሚሆኑ የቦርዱ የምርጫ ሎጂስቲክስ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡በእቅዱ መሰረት የእሸጋ ሥራው በርቀት ለሚገኙ ክልሎችና የምርጫ ጣቢያዎች ቅድሚያ እንደሰጠ የጠቀሱት መላኩ በአሁኑ ወቅት “የሶማሌንና የአፋር ክልሎችን 100 ከመቶ አጠናቀናል” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም 30 ከመቶ አካባቢ በሚሆኑት የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ በዲጂታል የሚካሄድ ሲሆን ለዚህም ታብሌቶችን ጨምሮ አስፈላጊ ቁሳቁሶች እሸጋም እየተካሄደ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እንደ መላኩ ገለጻ ከሆነ የምርጫ ቁሳቁሶቹም በፊት የመራጮች ምዝገባ ከሚካሄዱባቸው አምስት ቋንቋዎች በተጨማሪ በሲዳምኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ቁሳቁሶችም ተካተውባቸዋል ብለዋል፡፡

ቦርዱ በየጣቢያው ላሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች እንዴት የመራጮች ምዝገባ እንደሚካሄድ በተለያዩ ደረጃዎች ሥልጠናዎችን የሚሰጥ ይሆናል፡፡ መላኩ እንዳሉት ለእነዚህ ሥልጠናዎች የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችም በምርጫ ሎጂስቲክስ ሥራ ክፍል በኩል ወደ 7 ሺህ በሚጠጉ ሳጥኖች የሚታሸጉም ይሆናል፡፡ የምርጫ ቁሳቁሱን ደህንነት በተመለከት “እያንዳንዱ ሳጥን ሲታሸግ የጥራት ማረጋገጥ ይከናወንበታል፣ እያንዳንዱ ሳጥንም ቁጥር ባለው ኮድ እንዲታሸግ ይደረጋል” ብለዋል፡፡ የእሽጎቹን ጥራትም የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት እንደሚያረጋግጥ ጠቅሰዋል፡፡ ስርጭትን በተመለከተም ከአዲስ አበባ ማዕከላት እስከምርጫ ክልል ድረስ ያለው ስርጭት ሙሉበሙሉ በቦርዱ የሚከናወን  መሆኑንም መላኩ ጠቅሰዋል፡፡ ከምርጫ ክልል እስከምርጫ ጣቢያ ያለው ስርጭት በክልል መንግስታት ድጋፍ አማካኝነት የሚከናወን ሲሆን “ሌላው የስርጭቱ ሙሉ ቁጥጥር ግን በቦርዱ አማካኝነት ይከናወናል” ብለዋል፡፡ እንደመላኩ ገለጻ ቦርዱ ለስርጭቱ በአብዛኛው የምድር መጓጓዣን የሚጠቀም ሲሆን በተጨማሪም የአየር መጓጓዣንም በተለይም በርቀት የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎችን ለመድረስ ጥቅም ላይ እንደሚያውል ገልጸዋል፡፡ የምርጫ አስፈጻሚ የሥልጠና ቁሳቁሶች ሙሉበሙሉ በአየር መጓጓዣ የሚሰራጩ ይሆናል፡፡ በጋምቤላ ክልል ወደምትገኘው የአኮቦ የምርጫ ክልል የሚደረጉ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት በጀልባ የሚከናወን መሆኑን በተጨማሪ ጠቅሰዋል። እንደመላኩ ገለጻ በአሁኑ ጊዜ የምርጫ አስፈጻሚዎች የሥልጠና ቁሳቁሶች ስርጭት በመካሄድ ላይ ሲሆን ለመራጮች ምዝገባ የሚሆኑ ቁሳቁሶች ስርጭት በሚቀጥለው ሳምንት ይከናወናል፡፡ የዲጂታል ታብሌቶች ስርጭትም ለጥንቃቄ ሲባል ለብቻቸው ታሽገው በልዩ ምዝገባና ርክክብ በተመሳሳይ ጊዜ ስርጭታቸው ይከናወናል ብለዋል፡፡ የጸጥታ ጉዳይ ያለባቸው አካባቢዎችን አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ መላኩ በሰጡት ምላሽ የሎጂስቲክስ ክፍሉ እሸጋውን ሙሉለሙሉ እንደሚያካሄድና የስርጭቱ ጉዳይ በቦርዱ የኦፐሬሽን ክፍልና ቦርዱ በሚመሩት ሂደት የሚወሰን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ሰሌዳ መሰረት ከየካቲት 7 አስከ መጋቢት 7 2018 ዓ.ም ሊካሄድ ታስቦ የነበረውን የ7ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በጊዜው ሰሌዳ መሰረት የታቀዱትን ሥራዎች አከናውኖ ለመጨረስ ባለመቻሉ መራዘሙን ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የመራጮች ምዝገባ የተራዘመበት ምክንያትም የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላና የመጋዘን ዝግጅት የወሰዱትን ጊዜ መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሀይሉ ጠቅሰው ነበር።በዚህም መሰረት የመራጮች ምዝገባው ከየካቲት 28፣ እስከ መጋቢት 28፣ 2018 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል፡፡ 

[በ“ምርጫ 2018-ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠናቀረ]