ለ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች “አከራካሪ” በተባሉት አምስቱ የምርጫ ክልሎች፡- ሁመራ፣ አዲ ረመጽ፣ ጠለምት፣ ኦፍላ ኮረም እና አላማጣ የምርጫ ክልሎች ውስጥ ያሉ አካባቢዎች የመራጮች ምዝገባን ጨምሮ ምንም ዓይነት የምርጫ እንቅስቃሴ እየተካሄደ አለመሆኑን የአካባቢው የመረጃ ምንጮች ገለጹ።
ከየካቲት 28 ጀምሮ ላለፉት ሦስት ሳምንታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ሊያካሒድ በዕቅዱ በያዘው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በአገር አቀፍ ደረጃ እያከናወነ ባለበት ወቅት፣ እነዚህ “አከራካሪ” አካባቢዎች ላይ የምርጫ ሁኔታ ምን እንደሚመስል “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መረጃ ለማሰባሰብ ሞክራለች። በዚህም “አከራካሪ” በሚባሉት የአማራና የትግራይ አካባቢዎች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ብቻ ይደረጋል የተባለው የመጪው ምርጫ ዝግጅትን በተመለከተ ምንም ዓይነት የምርጫ እንቅስቃሴ እየተካሄደ አለመሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
በሁመራ ከተማ የሚሰሩና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ባለሙያ በተለይ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የምርጫ እንቅስቃሴ እና የመራጮች ምዝገባ እንቅስቃሴ አልተጀመረም። ሌላዋ በሁመራ ከተማ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው እስካሁን በዞኑ ውስጥ ምንም ዓይነት የምርጫ እንቅስቃሴ አለመኖሩን ገልጸውልናል። ይህንን አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የዞኑ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ገብረእግዚአብሔር ደሴ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአካባቢው የምርጫ እንቅስቃሴ አለመጀመሩን አረጋግጠውልናል።
በተመሳሳይ በአላማጣ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳዊት ቢሻው ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር እንደገለጹት በኦፍላኮረምና አላማጣ የምርጫ ክልሎች እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የምርጫ እንቅስቃሴ አልተጀመረም። አስተያየት ሰጪው አክለው እንደገለጹት በኦፍላ ኮረምና አላማጣ የምርጫ ክልሎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይካሄዳል የተባለው የምርጫ እንቅስቃሴ እስካሁን ድረስ የዕጩዎች ቅስቀሳም ይሁን የመራጮች ምዝገባ እንቅስቃሴ እየተካሄደ አይደለም።
ሌላኛው አወዛጋቢ ከሚባሉት ቦታዎች ውስጥ አንዱ በጸለምቲ ወረዳ የሚገኘው የጸለምቲ ምርጫ ክልል ሲሆን በዚህ አካባቢ የምርጫ ሥራ አለመኖሩን በወረዳው ዋና ከተማ በሆነችው በማይጸብሪ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት አቶ እንዳላማው አደመ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች “አከራካሪ” የሆኑ አካባቢዎች “የይገባኛል ጥያቄው” እስከሚፈታ ድረስ፣ “ከትግራይ ክልል ውጪ ሆነው” ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ብቻ ምርጫ እንዲካሄድባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ ትዕዛዝ እንደሰጠው የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በዚህም ቀድሞ በምዕራብ ትግራይ ሥር የሚገኙት ሁመራ፣ አዲ ረመጽ እና ጠለምት የተባሉ ሦስት የምርጫ ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ትግራይ ሥር የሚገኙት ኦፍላ ኮረም እና አላማጣ የተባሉ ሁለት፣ በድምሩ አምስት የምርጫ ክልሎች የፓርላማ ምርጫ እንደሚካሄድባቸው አሳውቆ ነበር።
ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ካሳወቀ በኋላ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የዴሞክራሲያዊ ስምረት ፓርቲ (ስምረት)ን ጨምሮ በትግራይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ተቃውሞ ማስነሳቱ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ስምረት ፓርቲ ውሳኔውን በመቃወም ጉዳዩን የካቲት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ ውሳኔው ላይ ፍርድ ቤቱ ጊዜያዊ ዕግድ እንዲያሳልፍ ያደረገ ቢሆንም፣ ፓርቲው መጋቢት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ ሕጋዊ መሠረት የሌለው በመሆኑ ክርክሩን እንደማይቀጥል ገልጾ ክሱን አቋርጧል። በዚህም ፍርድ ቤቱ እግዱን ማንሳቱ ይታወሳል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




