የዲጂታል የመራጮች ምዝገባ ተስፋና ስጋት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎች እና የመራጮች ምዝገባ የሚያካሄድበትን የዲጂታል ሥርዓት በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚተገበር አስታውቋል። ቦርዱ ይህ ሥርዓት የምርጫ ሂደቱን ለማዘመን፣ ለማቀላጠፍና የጊዜና የጉልበት ብክነትን ለማስቀረት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። በሌላ በኩል በዲጂታል ምዝገባ ስርዓቱ ከታገዘው  የዕጩዎች ምዝገባ ተሞክሯቸው በመነሳት  አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሂደቱ ላይ ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ።

ለመሆኑ የዲጂታል የመራጮች ቴክኖሎጂ ምንድን ነው? በምርጫ ሂደት ውስጥ ያሉ ዋና ተዋንያን በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለሂደቱ ምን አይነት ግምገማ አላቸው? በተለይም ከስርዓቱ አዲስነት፣ በከፊል ከመተግበሩ፣ እንደ ኢንተርኔት ተዳራሽነት ካሉ የመሰረተ ልማት እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክኅሎት (digital literacy) ክፍተቶች፣ ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ እና ከሳይበር ደህንነት ጋር የተያያዙ ስጋቶችስ የትኞቹ ናቸው?

የዲጂታል የመራጮች ምዝገባ ተስፋዎች

እንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሆነ አዲስ የሚተገበሩት የዲጂታል መመዝገቢያ ቴክኖሎጂዎች መራጮችና እጩዎች በምዝገባ ሂደት ሊያጋጥሟቸው የሚችልን መጉላላት፣ የሚያጠፉትን ጊዜና ጉልበት፣ በምዝገባ ሂደት ሊያጋጥማቸው የሚችልን ማንኛውም ተፅዕኖ ለማስቀረት ያለሙ እንደሆኑ ነው።  

በተለይም አካል ጉዳተኞች (ዓይነ-ሥውራን) ራሳቸውን በራሳቸው መመዝገብ እንዲችሉ፣ መራጮች ቋሚ የመራጭነት መለያ ቁጥር እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ እንዲሁም የመረጃ አመዘጋገብና አደረጃጀትን ቋሚና ዘመናዊ ለማድረግ በማሰብ የመራጮችን ምዝገባ በከፊል የምርጫ ክልሎች በዲጂታል የታገዘ እንዲሆን እንዳደረገ ቦርዱ ገልጿል።

በዚህም መሰረት የዲጂታል የመራጮች ምዝገባ በሁለት መንገድ የሚካሄድ ይሆናል። የመጀመሪያው መራጮች “ምርጫዬ” የተባለውን የሞባይል ስልክ መተግበሪያ በመጠቀም ራስን በራስ የሚመዘግቡበት አማራጭ ሲሆን ሁለተኛው በምርጫ ጣቢያዎች የቦርዱን ታብሌት በመጠቀም በተመሳሳይ መተግበሪያ በምርጫ አስፈጻሚዎች አማካኝነት የሚከናወን ነው። 

በምርጫው ሰሌዳ መሰረት ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7 2018 ዓ.ም ሊካሄድ ታስቦ የነበረውና አሁን ደግሞ ከዝግጅት ጋር በተያያዙ የተለያዩ ምክንያቶች ከየካቲት 28፣ እስከ መጋቢት 28፣ 2018 ዓ.ም ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የመራጮች ምዝገባ በከፊል በዲጂታል ስርዓት የሚካሄድ ይሆናል።

ክልል/ከተማ አስተዳደርየመራጮች ምዝገባ በማንዋል የሚካሄድባቸው ምርጫ ጣቢያዎች ብዛትየመራጮች ምዝገባ በዲጂታል የሚካሄድባቸው ምርጫ ጣቢያዎች ብዛትየምርጫ ጣቢያ ብዛት 2018 (7ሃገራዊ ምርጫ)
ድሬዳዋ0315315
ሲዳማ1,2721,0142,286
አዲስ አበባ01,7391,739
ማዕከላዊ ኢትዮጵያ632,9282,991
ደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች5283,4754,003
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ1,0327721,804
ጋምቤላ39751448
ቤንሻንጉል ጉሙዝ554214768
ኦሮሚያ13,3834,78418,167
አፋር1,68401,684
ሶማሌ3,7093764,085
ሐረሪ0305305
አማራ11,4013111,432
ትግራይ2,1305692,699
ድምር36,153 (68.6%)16,573 (31.4%)52,726

የመራጮች ምዝገባ በማኑዋል እና በዲጂታል የሚካሄድባቸው የምርጫ ጣቢያዎች (ምንጭ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ)

የዲጂታል የመራጮች ምዝገባው ለምን በከፊል ጣቢያዎች ይተገበራል?

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በቅርቡ እንደገለጹት ዲጂታል የመራጮች ምዝገባው ከመሠረተ ልማት፣ በጀትና የሰው ኃይል አቅርቦት አንጻር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሁሉም የምርጫ ክልሎች መተግበር ያዳግታል። ስለዚህ በተለዩና ወደ 17 ሺህ የሚጠጉ ወይም ከአጠቃላዩ 30 ከመቶ በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ይህንን የዲጂታል የመራጮች ምዝገባን ተግባራዊ የሚደረግባቸው አካባቢዎች ቢያንስ ከ3ጂና ከዚያ በላይ የሆነ የኢንተርኔት ሽፋንና የመብራት አገልግሎት ያላቸውን ብቻ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ስጋት  

ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎችን ምዝገባ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ ታግዞ ከጥር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲያካሄድ ቆይቷል። በፓርቲዎች ጥያቄ መሰረትም ምዝገባው በ15 ቀን ተራዝሞ የካቲት 1 ቀን መጠናቀቅ ሲገባው እስከ የካቲት 16 ሲካሄድ ቆይቷል። በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ባጋጠማቸው ሁኔታ ላይ ተመርኩዘው እንዲሁም ከቴክኖሎጂው አዲስነት ጋር በተገናኘም የመራጮች ምዝገባ ላይ ስጋት እንዳላቸው አንዳንድ ፓርቲዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነቢሃ መሐመድ ለ“ምርጫ 2018  – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት አንዳንድ የምርጫ ሂደቶች በዲጂታል እንዲካሄዱ ከዚህ በፊት የፓርቲው ፍላጎት እንደነበረና 6ተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎም በተደረጉ ውይይቶች የተነሳ ሃሳብ መሆኑን አስታውሰዋል። 

በዚህም መነሻ የምርጫ ቦርድ ጅምርን አድንቀዋል። ነገር ግን ከዝግጅት ረገድ ክፍተት እንዳለ ነቢሃ ጠቁመዋል። “ከ1500 በላይ እጩዎችን ለፓርላማና ለክልል ምክር ቤቶች እናስመዘግባለን ብለን እየሰራን ባለንበት ወቅት ሲስተሙ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ አግኝተነዋል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚደረግ ምርጫ ጥርና የካቲት ላይ ወደ ምዝገባ መገባቱ ዘግይቷል። ምክንያቱም ከዲጂታል ምዝገባው ቀድሞ የፓይለት [የሙከራ] ስራ መሰራት ነበረበት፤ ሲስተሙ በጣም አክሰሱ [ተደራሽነቱ] ዝቅተኛ ነው” ሲሉም ነቢሃ አክለዋል።

በተለይም ፓርቲው በሲስተሙ እጩዎቹን በሚያስመዘግብበት ጊዜ “የኦቲፒ [የአንድ ግዜ የይለፍ ቃል] መልዕክት ወደ ዕጩዎች የተንቀሳቃሽ ስልክ” ስለሚላክ ዕጩዎቹም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከመገኘታቸውና ከኢንተርኔት መሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ የፓርቲው የዕጩዎች መመዝገቢያ ሲስተም አስተዳዳሪዎች መልዕክቱን ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል። በተመሳሳይ እጩዎችን በማስመዝገብ ሂደት ሲስተሙ ተደጋጋሚ ጥረቶችን ውድቅ ያደርግ እንደነበርና እነዚህ ተደራራቢ እክሎች የግዜና የሀብት ብክነት እንዳስከተሉ ነቢሃ አብራርተዋል።

በዲጂታል ሲስተሙ አማካኝነት ሙሉ የሚፈለገውን መረጃ ለማካተት አዳጋች እንደነበርና መረጃውን ለማካተት ተመልሶ “ወደ ማኑዋል” ሲስተም መመለስም ግድ ሆኖ ነበር ያሉት ነቢሃ “ለሚቀጥለው እንደልምድ፣ እንደትምህርት ካልሆነ በስተቀር እጅግ አድካሚና አሰልቺ የዕጩዎች የምዝገባ ሂደት ነበር” ሲሉ ግምገማቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በመራጮች ምዝገባ ሂደትም ላይ ተመሳሳይ ስጋት እንዳለባቸው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ነቢሃ ገልጸዋል። “የማህበራዊ መሰረታችን አዲስ አበባ ብቻ አይደለም። [ሌሎች አካባቢዎች ያለ] ማህበረሰብንም ያጠቃልላል። ይህ የማህበረሰብ ክፍልም ግዴታ መራጭ ሆኖ መመዝገብ አለበት” ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ስጋታቸውን ሲገልጹም “ይህ  በ10 ሺዎች የሚቆጥሩ ዕጩዎችን ለማስመዝገብ ያስቸገረ ሲስተም” በዲጂታል ይመዘገባል ተብሎ ከሚጠበቀው በሚሊዮኖች የሚቆጠር የመራጮች ቁጥር አንጻር ሲታይ “ለኛ ይህ ትልቅ ስጋት ነው” ሲሉ ነቢሃ በሚሊዮኖች የሚቆጠረው የመራጮች ምዝገባ እክል እንዳይገጥመው ስጋታቸውን ገልጸዋል።

“መራጩ በተባለው ዲጂታል ሲስተም ይመዘገባል ወይ? ዕውቀቱ ምን ያህል አለው? ምን ያህል ቴክኖሎጂ በእጁ አለ? ምን ያህልስ ውጤታማ ነው? የሚለውን በዕጩዎች ምዝገባ ላይ ካየነው ተሞክሮ አጠያያቂ ነው የሚሆነው” ሲሉ ያላቸውን የስጋታቸውን ምንጭ ገልጸዋል።

ስለዚህ ቦርዱ የመመዝገቢያ ሥርዓቱንና  የሰው ሃይል ማሳደግ እንዳለበት እንዲሁም የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ከምን ጊዜውም በላይ በመራጮች ምዝገባ ወቅት የአገልግሎት ጥራት ማሳደግ እንዳለባቸውና “በተቻለ መጠን እንደዚህ አይነት ስራዎች ሲሰሩ የፓይለት [የሙከራ] ስራዎች ቀድመው መሰራት እንዳለባቸው” አሳስበዋል።   

የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር አማኑኤል ሞጊሶ በበኩላቸው እንደገለጹት እጩዎችን ለማስመዝገብ ባካሄዱት ጥረት በመነሳት የዲጂታል ምዝገባው ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ተናግረዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ሥርዓቱ አዲስ ከመሆኑም አንጻር በፖለቲካ ፓርቲዎች የመረጃ አቀራረብ ላይ ክፍተቶች ነበሩ። ሆኖም፣ የቴክኖሎጂው ዋነኛ ዓላማ ጊዜ መቆጠብና ሂደትን ማሳጠር ቢሆንም በምርጫ ቦርድ በኩልም በአፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ረገድ ክፍተቶች ነበሩ ሲሉ አማኑኤል አክለዋል። 

አማኑኤል ከምዝገባ በኋላ “የአፕሩቫል [የማጽደቅ] ሂደቱ ረጅም ነበር። ከዕጩ በኋላ በአራት ደረጃ ማለትም በኦፐሬሽንና በፖለቲካ አድሚኖች፣ እንዲሁም በአረጋጋጭና/ቬሪፋየርና በሰብሳቢዋ መረጋገጥ ነበረበት። ከሰው እጥረት ይሁን በሌላ ሥርዓቱ በጠበቅነው ልክ አልሄደም። በኔ በኩል ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ ባላውቅም ግን ክፍተት ነበር” ብለዋል። በተጨማሪም ከሙሉ ትግበራው በፊት በፖለቲካል ፓርቲዎች የሙከራ ትግበራ መደረግ ነበረበት ሲሉም አክለዋል።

በሌላ በኩል ግን ሥርዓቱ ብዙ መረጃዎችን ያቀለለበት ሁኔታ መኖሩንም አማኑኤል ጠቁመዋል። “ለምሳሌ ከፋይዳ ጋር መያያዙ የደህንነት ጉዳዩ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ማለትም ፋይዳ ከሌላ የመንግስት ድርጅት ጋር የተያያዘ ስለሆነና ይህ ተቋም የኛን መረጃ ማግኘት ይችላል አይችልም የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ ለኛ የጠቀመን የእያንዳንዱን ዕጩ ፕሮፋይል፣ ፎቶና ሌሎች መረጃዎችን ከፋይዳ መውሰድ ተችሏል። ስለዚህ የዕጩን መረጃ ከማግኘት አንጻር ጠቅሞናል” ሲሉ አክለዋል።

በዚህ መነሻ የመራጮች ምዝገባን በሚያካሄድበት ወቅት ምርጫ ቦርድ አቅሙን ማሳደግ እንዳለበት አማኑኤል ገልጸዋል። አማኑኤል “የመራጮች ምዝገባ በቁጥር ከፍተኛ ስለሚሆን ብዙ የሲስተም ሰራተኛ ያስፈልጋቸዋል። በፈረቃ ቀንም ማታም የሚሰሩበት ሁኔታ ቢፈጠርም መልካም ይሆናል” ብለዋል።

“በሃምሳዎች ለሚቆጠሩ ፓርቲዎች የእጩዎችን ምዝገባ በአንድ ወር ማጠናቀቅ ካልተቻለ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መራጮችን ለመመዝገቡ ከፍተኛ ተግዳሮቶች ሊያጋጥም ይችላል” ሲሉም አማኑኤል አክለዋል። 

የዲጂታል መራጮች ምዝገባ በዓለም ዐቀፍ ተቋማት ዕይታ

በአለም አቀፉ የዴሞክራሲና የምርጫ ድጋፍ ተቋም ወይም በምህጻረ ቃሉ International Idea ድህረ ገጽ ላይ ‘ስለ ባዮሜትሪክ የመራጮች ምዝገባ ልታውቁ የሚገባችሁ አምስት ነገሮች’ በሚል በታተመው ጽሑፍ እንደተገለጸው በዲጂታል የሚካሄድ ወይም የባዮሜትሪክ የመራጭ ምዝገባ የመራጮችን ልዩ የአካል ባህሪያትን/መለያን በመመዘንና በመተንተን ማንነታቸውን እና ለመምረጥ ብቁ መሆናቸውን የሚያረጋገጥበት ሂደት ነው።

ቴክኖሎጂው የማንነት ስርቆትን፣ ከአንድ ጊዜ በላይ መምረጥን እና ሌሎች ከድምጽ መስጠት ጋር የተገናኙ የማጭበርበርና የማታለል ዘዴዎችን መከላከልን አላማው ያደረገ ነው። ነገር ግን፣ ቴክኖሎጂው የመራጮች መዝገብን እና የምርጫ ታማኝነትን በተሻለ ሁኔታ ለማረጋገጥ አመቺ ሁኔታን ቢፈጥርም ከእንከን ግን ሙሉ ለሙሉ የጸዳ አይደለም።

በመሰረታዊነት የባዮሜትሪክ መራጭ ምዝገባ መራጩን ለመለየት እንደ የፊት ገጽታ ወይም የጣት አሻራ ያሉ የአካል ልዩ ባህሪያት ወይም መገለጫዎችን ይጠቀማል። ብዙ ጊዜ ስካን የተደረገ ፊርማ የመራጩ ባዮሜትሪክ መረጃ አካል ይሆናል። እነዚህ በካሜራ ወይም በሴንሰር የተሰበሰቡ መረጃዎች ከመራጩ/ጯ ግለሰብ ስም እና የትውልድ ቀን ጋር በመጣመርና በመረጃ ቋት በመሰብሰብ የመራጩ/ጯን መገለጫ (voter profile) ይፈጥራል። በምርጫ እለትም የባዮሜትሪክ የመራጮች ማንነት ማረጋገጫን (Bio-metric Voter Identification) በመጠቀም የመምረጥ ሂደቱን እንዲተገበር ያደርጋል።ለምሳሌ፣ በምርጫ ጣቢያ በኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች በመደገፍ የመራጩን የጣት አሻራ ስካን በማድረግ ሊሆን ይችላል።

በሌላ በኩል የዲጂታል የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ የሚነሱ ስጋቶች መኖራቸውም አልቀረም። ለምሳሌ በአንዳንድ አካባቢዎች ከባህል እሳቤዎች ጋር ተያይዞ ጥርጣሬ ሊያስነሳ ይችላል። ከዚህ በፊት እንደታየው  በአንዳንድ ሀገራት ከሀይማኖት ጋር በተያያዘ ሴቶች የፊት ገጽታቸውን የሚሸፍኑብት ሁኔታ ሲኖር ይህም በዲጂታል የመራጮችን ፎቶ ለመውሰድ እንዲሁም በምርጫ ቀን ጥቅም ላይ ለማዋል ተግዳሮት የሆነባቸው ግዜያት እንደነበሩ ጽሑፉ ያትታል።  ሌላው አከራካሪ ጉዳይ የባዮሜትሪክ መራጭ ምዝገባ ውስብስብነት እና ለመተግበር የሚፈልገው ጊዜ፣ ክህሎት እና ሀብት ብዙውን ጊዜ ከምርጫ አስተዳዳሪው አካል ውጭ ከሌላ የመንግስት ወይም የግል ተቋም ድጋፍ የሚፈልግ መሆኑ ነው። ይህም የመራጮች የግል መረጃ ከምርጫ አስተዳዳሪው ውጪ ለሌላ ሦስተኛ አካል ተደራሽ ማድረጉ ለተለያየ ዓላማ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል የሚል ስጋትን መፍጠሩ አልቀረም። ይህንንም ለማስቀረት የምርጫ አስተዳዳሪ አካላት በበላይነትና በነቃ ሁኔታ ሂደቱን መከታተል እንዳለባቸውም ባለሙያዎች ይመክራሉ።  

ባዮሜትሪክ የመራጮች ምዝገባና ሳይበር ደህንነት

በአለም አቀፉ የምርጫ ስርአት ፋውንዴሽን (IFES)፣ ዲኤአይ (DAI) እና በቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ አለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ የተዘጋጀው የሳይበር ደህንነት እና የመራጮች ምዝገባ የተሰኘ ጥናት የመራጮች ምዝገባ የመረጃ ቋት የባዮሜትሪክ መረጃዎችን እና ሌሎች የግል መለያ መረጃ (personal identification Information) ማካተቱ ልዩ ለሆኑ የሳይበር ደህንነት እና የአስተዳደር ስጋቶች ተጋላጭ ያደርጉታል። 

ስለዚህ የምርጫ አስተዳደር ተቋማት የውስጥ ኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና የሳይበር ደህንነት አቅማቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ጥናቱ ይመክራል። ይህ ካልሆነ የሳይበር ጥቃት ፈፃሚዎች የመራጮችን ሙሉ ባዮሜትሪክ መረጃ በመዝረፍ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ አደጋ የሚጥል መረጃ በእጃቸው ሊያስገቡ ይችላሉ።

እስከ ዛሬ ድረስ፣ በመራጮች ምዝገባ ሥርዓቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች የምርጫ ውጤቶች ላይ መሠረታዊ በሆነ መንገድ ተጽእኖ ያደረጉ ባይሆንም እንደጥናቱ ከሆነ እየጨመረ የሚሄዱት የሳይበር ጥቃቶች ውስብስብነት እና የመራጮች ምዝገባ ቴክኖሎጂ ትግበራ ወደፊት የስጋት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ የባዮሜትሪክ የመራጮች ምዝገባ ሥርዓቶች በጥቂት አጋጣሚዎች ተስፋ እንደተደረገባቸው ተደጋጋሚ የመራጭ ምዝገባን መከላከል እንዲሁም በምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን በትክክል መለየት ያለመቻላቸው ተስተውሏል። ይህም በጥቂት አጋጣሚ መሆኑ በአጠቃላይ የምርጫው ውጤት ላይ ተጽእኖ ባያሳድሩም ክፍተት እንዳለባቸው ግን አሳይቶ አልፏል። 

በመራጮች ምዝገባ የመረጃ ቋት ውስጥ ያለውን መረጃ ዒላማ የሚያደርጉ ቡድኖች የመንግስት አካላትን ጨምሮ ምርጫው ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ የሚለው ጥናቱ ይህም የምርጫው ተዓማኒነት ላይ ጥላ እንዲያጠላ ያደርጋል ሲል ይተነብያል። 

በሁለቱም ጥናቶች እንደተጠቆመው ከትግበራ በፊት ዲጂታል የመራጮች ምዝገባን ዓላማ እና ግቦች ለዜጎች ግልጽ ማድረግ እጅግ ወሳኝ ነው። በተለይም እንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሉ የምርጫ አስተዳዳሪው አካላት በእጅ ወይም በማኑዋል የሚካሄደውን የመራጮች ምዝገባ ሥርዓት ድክመቶችን መገምገምና የዲጂታል ምዝገባ እነዚያን ክፍተቶች እንዴት ሊያሻሽል እንደሚችል መተንተን አለባቸው። በተለይም ከሰው ሃይልና ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክኅሎት አንጻር ከፍተኛ ዝግጅትና ጥንቃቄን እንደሚሻም ይገልጻሉ።

[ምርጫ 2018 – በኢትዮጵያ ኢንሳይደር]