የአዲስ አበባ ከተማ ካሉት 23 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች መካከል ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በሦስት የምርጫ ክልሎች ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ሳያቀርብ ቀረ። ብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎቹን ካላቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ሁለቱ፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መሪ እና ምክትላቸው የሚወዳደሩባቸው ናቸው።
ብልጽግና ፓርቲ በመጪው ግንቦት ወር 24፣ 2018 በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ፤ አዲስ አበባን በመወከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለከተማይቱ ምክር ቤት የሚወዳደሩ ዕጩዎቹን የማስተዋወቂያ መድረክ ያካሄደው ከአንድ ሳምንት በፊት መጋቢት 3፤ 2018 ነበር። በከተማ ደረጃ ከተካሄደው ከዚህ መድረክ በኋላ የፓርቲው ዕጩዎች በየሚወዳደሩባቸው ክፍለ ከተሞች በመገኘት በተመሳሳይ መርሃ ግብሮች ሲሳተፉ ቆይተዋል።
ገዢው ፓርቲ ለዘንድሮ ምርጫ የአዲስ አበባ የፓርላማ መቀመጫ ካቀረባቸው 20 ዕጩዎች መካከል 16ቱ በስድስተኛው ዙር ምርጫ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ያልነበሩ መሆናቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፓርቲው ካሰራጫቸው መረጃዎች ተገንዝባለች። ከእነዚህ አዲስ የፓርላማ ተወዳዳሪዎች መካከል አምስቱ ሚኒስትሮች ሲሆኑ ሦስቱ ደግሞ ሚኒስትር ዴኤታዎች ናቸው።
ከሚኒስትሮቹ የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተመራጮች መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ ይገኙበታል። ከአዳዲሶቹ ተመራጮች መካከል የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃበታ እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ይገኙበታል።
ለዘንድሮ የአዲስ አበባ የፓርላማ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ ዶ/ር ሳሙኤልን ጨምሮ ስምንት የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸውን ተወዳዳሪዎችን አቅርቧል። የሦስተኛ ዲግሪ ባለቤቶችን ለውድድር የማቅረብ አካሄድ፤ በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ የወቅቱ ገዢ ፓርቲ ተገዳዳሪ በነበረው የቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ አባላት ከታየ በኋላ በሌሎችም ፓርቲዎች በስፋት ሲዘወተር ቆይቷል።
ብልጽግና ፓርቲ በባለፈው ምርጫ ወቅት ለአዲስ አበባ የፓርላማ መቀመጫዎች ካስመረጣቸው 22 አባላቱ መካከል አስሩ የዶክትሬት ዲግሪ የነበራቸው ናቸው። በዚሁ ምርጫ ከተመረጡ የገዢው ፓርቲ የፓርላማ አባላት መካከል ሁለቱ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያላቸው ነበሩ።
በ2013ቱ ምርጫ ከተመረጡት የብልጽግና የአዲስ አበባ የፓርላማ አባላት መካከል ዘንድሮም በድጋሚ ለውድድር የቀረቡት አራቱ ብቻ ናቸው። በአዲስ አበባ ዳግም ለተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የሚወዳደሩት ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ፣ ሰሀረላ አብዱላሂ፣ ያስሚን ወሀበረቢ እና መሀመድ ከማል አልሩሲ መሆናቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያጠናቀረችው መረጃ ያሳያል።
ባለፈው ምርጫ ገዢው ፓርቲ ተወዳዳሪ ሳያቀርብ የቀረበት የምርጫ ክልል አንድ ብቻ ሲሆን ዘንድሮ ይህ ቁጥር ወደ ሦስት አድጓል። በ2013ቱ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ ዕጩውን ያላወዳደረበት፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለፓርላማ የተመረጡበት ምርጫ ክልል 28 ነበር።
ይህ የምርጫ ክልል በየካ ክፍለ ከተማ የሚገኝ ነው። በዘንድሮው ምርጫ ገዢው ፓርቲ በየካ ክፍለ ከተማ ባሉት ሦስቱም የፓርላማ መቀመጫዎች ላይ ዕጩዎቹን አቅርቧል። በዚህ ክፍለ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ክልሎች የሚወዳደሩት የብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎች፤ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ፣ የፌደራል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተሯ ዶ/ር ለሊሴ ነሜ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ አይሻ መሐመድ ናቸው።
ገዢው ፓርቲ በመጪው ምርጫ ዕጩዎቹን ያላቀረበባቸው፤ በጉለሌ፣ በቂርቆስ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ከተሞች የሚገኙ ምርጫ ክልሎች 11፣ 18 እና 23 ናቸው። በጉለሌው ምርጫ ክልል 11 ባለፈው ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ አግኝተው ለፓርላማ የተመረጡት ፕ/ር ሂሩት ወልደማርያም ነበሩ።
በግንቦቱ ምርጫ በዚህ የምርጫ ክልል ከሚወዳደሩት ዕጩዎች መካከል የቀድሞው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተመራጩ ዶ/ር አበባው ደሳለው ይገኙበታል። ዶ/ር አበባው በድጋሚ የፓርላማ መቀመጫ ለማግኘት ለውድድር የሚቀርቡት፤ የአምስት ፓርቲዎች ቅንጅት የሆነውን “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነትን” በመወከል ነው።
ብልጽግና ፓርቲ ተወዳዳሪውን ለፓርላማ በማያቀርብበት ምርጫ ክልል 18 ደግሞ አዲሱ የኢዜማ መሪ አቶ ኢዮብ መሳፍንት ዕጩ ሆነው መቅረባቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ ኢዮብ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን በመተካት የኢዜማ አዲሱ መሪ ሆነው የተመረጡት ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነበር።
የኢዜማው መሪ በሚወዳደሩበት የምርጫ ክልል፤ ባለፈው ምርጫ ብልጽግና ፓርቲን በመወከል ለፓርላማ የተመረጡት አቶ ዛዲግ አብርሃ ነበሩ። የአፍሪካ ልህቀት አመራር አካዳሚን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ የሚገኙት አቶ ዛዲግ፤ ከዘንድሮው የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ የፓርላማ ተወዳዳሪዎች ዝርዝር ውጭ ሆነዋል።
ገዢው ፓርቲ ዕጩውን በማያወዳድርበት በሌላኛው የአዲስ አበባ የፓርላማ መቀመጫ ተመራጭ የነበሩት ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬም ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሟቸዋል። በባለፈው ምርጫ የኢዜማው ፕሮፌሰር ብርሃኑን አሸንፈው የነበሩት ዶ/ር ዲላሞ፤ አዲስ አበባን ትተው በሀዲያ ዞን በሶሮ 02 የምርጫ ክልል ለመወዳደር በዕጩነት ቀርበዋል።
ዶ/ር ዲላሞ በአሁኑ ወቅት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በመስራት ላይ ናቸው። እርሳቸው በለቀቁት የአዲስ አበባ የፓርላማ መቀመጫ ላይ ከሚወዳዳሩት ዕጩዎች ውስጥ የኢዜማው ምክትል መሪ አቶ ንጋቱ ወልዴ እንደሚገኙበት “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጣለች።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ምርጫ ክልል 23 የሚወዳደሩት አቶ ንጋቱ፤ እንደ አቶ ኢዮብ ሁሉ የኢዜማ ምክትል መሪ ሆነው የተመረጡት ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ጥር መጨረሻ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ቀጣዩ ምርጫ የበዙ የተቃዋሚ ፓርቲ ድምጾች የሚሰሙበት እንዲሆን መንግስታቸው “አውድ ማስፋት ብቻ ሳይሆን ይሁነኝ ብሎ ይሰራዋል” ማለታቸው የሚታወስ ነው። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




