የኢዜማው አዲሱ መሪ እዮብ መሳፍንት ስለ ፓርቲያቸው የምርጫ ዝግጅት ይናገራሉ!

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደረጃ 299 ዕጩዎችን እንዳስመዘገበ የሚናገረው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በመጪው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ድምፅ ለማግኘት እየሠራ እንደሆነና ይህ የማይሳካ ከሆነም እንደ ሁለተኛ አማራጭ በፓርላማ “የተለየ ድምፅ የሚያስተጋባ አብላጫ መቀመጫ የያዘ ተቃዋሚ ፓርቲ ለመሆን” እንዳቀደ የፓርቲው አዲሱ መሪ እዮብ መሳፍንት አስታወቁ።

ኢዜማ በቅርቡ ፓርቲውን ለ7 ዓመታት በመሪነት የመሩትን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋንና ምክትላቸውን በአዲስ አመራር የተካ ሲሆን እዮብ መሳፍንት የፓርቲው አዲሱ መሪ ሆነው ተመርጠዋል። እዮብ የአዲሱን አመራር ዕቅድ እና የፓርቲውን የምርጫ 2018 እንቅስቃሴን አስመልክተው በተለይ “ለምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደገለጹት ከባለፈው ምርጫ ግምገማ እና ስህተት በመነሳት እንዲሁም “እስከ ጥግ መወጠር የለብንም” ብሎ በማመን ፓርቲው የትኩረት አቅጣጫውን እንደለየ ተናግረዋል።

እዮብ መሳፍንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘላቂ ልማት (Sustainable Development) የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሠሩ ያሉ ሲሆን፣ በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በፖለቲካ ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪዎችን፣ እንዲሁም በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ይዘዋል። እዮብ ከ17 ዓመት በላይ በሕግ ባለሙያነት አገልግለዋል። ከፓርቲው ምስረታ ጀምሮ የአስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት እዮብ በማከልም “ከባለፈው ስህተቶቻችን በጣም በርካታ ነገሮች ተምረናል” በተለይ ያለአግባብ ላለመለጠጥ “ትኩረቶቻችንን ለይተናል” ያሉ ሲሆን “በፌዴራል ፓርላማ ደረጃ ኢዜማ መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል የዕጩዎች ቁጥር ማስመዝገቡን” ጠቁመዋል።

ከገዢው ፓርቲ ጋር እንደሚፎካከር ዋነኛ አካል “መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ድምፅ ለማግኘት የአቅማችንን ሁሉ ለመጣር” ይህም ባይሳካ “እንደ ፕላን ቢ [ሁለተኛ ዕቅድ] በፓርላማ ውስጥ በቂ ቁጥር ያለው የሕዝብን ድምፅ ሊያሰማ የሚችል ወይም ከገዢ ፓርቲ የተለየ ድምፅ የሚያስተጋባ ሜጀር ኦፖዚሽን (አብላጫ መቀመጫ የያዘ ተቃዋሚ) ፓርቲ ለመሆን እየሠራን ነው” ሲሉም አክለዋል።

“በአጠቃላይ 1,258 ዕጩዎችን አስመዝግበናል” ያሉት እዮብ ከዚህ ውስጥ “299ኙ በፓርላማ የሚወዳደሩ” መሆናቸውን ጠቁመዋል። “መንግሥት ለመመሥረት የሚያስፈልገው 275 ወንበር ነው” ያሉት እዮብ ፓርቲው ይህንን ቁጥር ለማሸነፍ የሚያስችል የዕጩዎች ቁጥር ማቅረቡን ጠቅሰዋል።

ከፌዴራሉ ፓርላማ ባለፈ የክልል ምክር ቤቶች በተለይም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ላይ የፓርቲውን ዕቅድ አስመልክቶም እዮብ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። አጠቃላይ የክልል ዕጩዎች ቁጥር እንዳልተደራጀ ሆኖም ኢዜማ “ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት በሁሉም ክልሎች” እንደሚወዳደር ገልጸዋል። “በሁሉም ክልሎች የምንወዳደረው መንግሥት ለመመሥረት ነው። በቂ [የዕጩዎች] ቁጥር የሌሉን ክልሎች ይኖራሉ፣ መንግሥት ለመሆን [የምንወዳደረው] የትኞቹ ክልሎች ላይ ነው የሚለውን እያየን [ወደፊት] መረጃ እንሰጣለን” ብለዋል።

6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም የብልጽግና የበላይነት የታየበት ስለሆነ ኢዜማ በአሁኑ ምርጫ ይህንን ለመቀየር ምን ዓይነት ዕቅድ ይዟል በሚል በ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በ2013 በተደረገው ምርጫ “እኔ እስከሚገባኝ ከብልጽግናም ግምት (expectation) ውጭ ያልተጠበቀ ድምፅ ብልጽግና አግኝቷል” ያሉት እዮብ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በተለይም በወቅቱ የነበረው “ሀገራዊ ሁኔታና የጦርነት ድባብ፣ ‘በጦርነት መሀል ፈረስ አይቀየርም’ እንደሚባለው መራጩ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን” ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የብልጽግና ሁሉንም ነገር “ጠርንፎ የመያዝ ባህሪ” ላይ የተቃዋሚዎች ድክመት ታክሎበት “ብልጽግና ያልጠበቀውን ድምፅ” እንዲያገኝ እንዳስቻለው አብራርተዋል።

ኢዜማ የ2018ቱን 7ኛ ሀገራዊ ምርጫ እንቅስቃሴ የጀመረው በዚህ መሠረት ላይ እንደሆነ የገለጹት እዮብ አሁንም አንዳንድ ሁኔታዎች እንዳልተቀየሩ ጠቁመዋል። “አሁንም ገዢው ፓርቲ በጣም ጠርናፊ ፓርቲ ነው። መድረክ ላይ ወጥቶ 16 ሚሊዮን አባላት አሉኝ የሚል ፓርቲ ነው። ይህ የዴሞክራሲም ሆነ የጥንካሬ መገለጫ አይደለም” ሲሉም እዮብ አብራርተዋል። “ገዢ ፓርቲ ሆነህ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን አባል ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ዴሞክራሲን የሚያቀጭጭ እንጂ እንዲያድግ የሚያደርግ አይደለም” ሲሉም ትችታቸውን ገልጸዋል።

“ስለዚህ ወደ ምርጫ የገባነው ይህ እንዳልተቀየረ አምነን ሆኖም ግን አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲመጣና በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ እሠራለሁ እንደሚል ፓርቲ ከምርጫ ውጭ ሌላ አማራጭ ስለሌለ ነው” ሲሉም አክለዋል።

በተጨማሪም ገዢውን ፓርቲ ተጠቃሚ በሚያደርግ ሁኔታ ተቃዋሚዎች እርስ በእርሳቸው ድምፅ የመነጣጠቅ ሁኔታ አለ ለሚለው ጥያቄ “ተቃዋሚዎችን አንድ ዓይነት አድርጎ ማቅረቡ” ትክክል እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

“በእርግጥ ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አጀንዳ እና ቢያንስ ተቀራራቢ ፕሮግራም እያላቸው ነው የተለያዩ ፓርቲ የሆኑት” ያሉት እዮብ “አብዛኛው እርስ በእርስ [የተለያዩት] እኔ ነኝ መሪ በሚል በግለሰቦች ሽኩቻ ምክንያት” መሆኑንም ጠቁመዋል።

“ሁሉም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አንድ ዓይነት አይደለም። ከአንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለን ልዩነት ከገዢው ፓርቲ ጋር ካለን ልዩነት በጣም ይበልጣል” ሲሉም አብራርተዋል። “ስለዚህ መርህ አልባ በሆነ መልኩ ተቃዋሚ ናቸው በሚል ብቻ አብረን የምንሠራበት ወይም አንዳንድ ቦታዎች ላይ ላለመፎካከር ጥረት የምናደርግበት ነገር አይኖርም” ሲሉም አስምረዋል።

እንደ እዮብ ገለጻ በቀጣዩ አምስት ዓመት ፓርቲው ከያዛቸው ዕቅዶች አንዱ በትብብር ሊሠራ ከሚችላቸው ኃይሎች ጋር በመቀራረብ መሥራት እንደሆነም ገልጸዋል። ሆኖም ምርጫን በሚመለከት “ኢዜማ ዕጩ ባቀረበባቸው ቦታዎች ላይ በሙሉ ለማሸነፍ ነው የምንሠራው” ያሉ ሲሆን “ማሸነፍ ስንል ደግሞ ገዢውን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሚፎካከሩን ፓርቲዎችን ጭምር ነው” ሲሉ አክለዋል።

በፓርላማ ንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን መቀመጫ እስከ 10 እጥፍ ለማሳደግ እንደሚሠሩ ጠቅሰው ነበር። ይህ “በሕዝብ ድምፅ ላይ የተመሠረተን ሒደት በዕቅድ መሥራት የሚቻል ጉዳይ ነው ወይ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ እዮብ በሰጡት ምላሽ “የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ‘ስፔሲፊክ’ ቁጥር ለማስቀመጥ አይመስለኝም፣ እኔ ‘ተስፋ የማደርገው ከዚህ በአስር እጥፍ ይጨምራል ብዬ ነው’ ለማለት ይመስለኛል” ብለዋል።

ሆኖም “በግሌ በዕቅድ መሠራት አለበት ብዬ ነው የማምነው” ያሉት እዮብ “እንደ ኢዜማ ብልጽግና ራሱን አቅቦ የተለያዩ ድምፆች እንዲሰሙ ማመቻቸት ከአንድ ገዢ ፓርቲ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ብለን ነው የምናምነው። አፈናዎቹን ገታ ካደረገ፣ በየቦታው የሚጠረንፋቸውን ጥርነፋዎቹን ላላ ካደረገ” ይህም የእቅዱ አካል እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

“አሁን ምርጫ ተጀመረ በተባለ ጊዜ እንኳን የኢዜማ በርካታ አባላት ታስረዋል” ያሉት እዮብ “እንደዚህ ዓይነት እስሮችን ማቆም ቢችልና ምኅዳሩን ለሁሉም እኩል ቢያደርግ በራሱ ጊዜ ልዩ የሆኑ ድምፆች ወደ ፓርላማ ይመጣሉ” ሲሉም አብራርተዋል።

ኢዜማ ከብልጽግና መንግሥት ጋር በትብብር መሥራቱ የራሱን ርዕዮትና ፕሮግራም ከማስተዋወቅ እንዲሁም የገዢው ፓርቲን ክፍተቶች ከማሳየትና ከመተቸት አንጻር ክፍተት ፈጥሯል በሚል ለሚነሳው ትችትም ምላሻቸውን ሰጥተዋል። ይህ “አረዳድ ትክክል ነው ብለን አናምንም” ያሉት እዮብ “ኢዜማ የታነጸበት መሠረት ከዚህ ቀደም የነበሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በገመገመ መልኩ” መሆኑን እና በግምገማውም ፓርቲው ከለያቸው ክፍተቶች መካከል “ሁሉን ነገር መቃወም ፖለቲካ” እንዳልሆነም ገልጸዋል።

እዮብ ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ “ስለዚህ ማንም ይሁን ማን በዋናነት ከቆምንላቸው አምዶች… እንዲሁም መሠረታዊ የሀገር መዳኛ መንገዶች ናቸው ብለን ከምናምናቸው በተጻራሪ የቆመ ማንኛውንም ገዢም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲ ያለምንም ሪዘርቬሽን እና ማወላወል የምንተችበት፣ መስመሩ ትክክል እንዳልሆነ የምናስረዳበት” ሁኔታ ይኖራል ብለዋል። ፓርቲው ትችቱን የሚያቀርበው ግን “በሠለጠነ እና በሐሳብ ላይ ብቻ በተመሰረተ መልኩ እንደሚሆን” መተማመን ላይ ደርሶ ምስረታውን እንዳካሄደም ጠቁመዋል።

“ገዢውም ሆነ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሀገር የማይጠቅሙ ነገሮች አድርገዋል” ብሎ ባመነ ቁጥር ሁሉ ፓርቲው “በዝምታ እንዳላለፈ” ጠቁመው ለዚህም “ያወጣናቸውን መግለጫዎች እና ጥናታዊ ጽሑፎች” ወደ ኋላ ሄዶ ማየት ይቻላል ሲሉ ጠቁመዋል።

ዓለም የፖለቲካ አካሄድ እየተቀየረ መሆኑን የጠቆሙት እዮብ “በፊት የነበሩ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል የምናያቸው” እና ዓለም የምትመራባቸው ሥርዓት ተብለው የተቀመጡት የ“ሊበራሊዝምም ሆነ የዴሞክራሲ መሠረታዊ መርሆች እንኳን ጥያቄ ውስጥ የገቡበት ዘመን ነው” ብለዋል።

በማከልም የአንድ ሀገር ትልቅነት የሚለካው “በውስጥ ባለው አቅም ብቻ የሆነበት ዘመን ነው” ያሉት እዮብ “ኃያልና ጉልበተኛ የሚባሉ ሀገራት የፈለጉትን የሚያደርጉበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፣ ዓለም አቀፉ rules based order ወይም በሕግና በመርህ የሚመራው የዓለም አቀፍ ሥርዓት እየፈረሰ ያለበት ሁኔታም እንደሆነ” ጠቁመዋል።

እዮብ “ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ይህንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለ ሥርዓትን መቋቋም እና ሀገር ሆነን መቀጠል ካለብን በአንድነት መቆም አለብን ብለን እናምናለን” ያሉ ሲሆን “በዚህ መርህ ላይ ተመስርተን ከገዢውም ሆነ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መሥራት ሁለተኛው መርሃችን ነው” ሲሉ አክለዋል።

እዮብ የጸጥታው ጉዳይ ምርጫው ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ አስመልክቶ በኦሮሚያ ያለው ሁኔታ እንደተሻሻለ ገልጸው በአማራ ክልል ግን አሁንም አስጊ የጸጥታ ሁኔታ እንዳለ ጠቁመዋል። “በጣም አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ትጥቅ ያነሱ ኃይሎች ሳይቀር ‘ምርጫ አትወዳደሩ’ የሚል ማስፈራሪያ በይፋ እየሰጡ ነው” ያሉት እዮብ በጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች “ሰው በነጻነት እንዳይመርጥ በይፋ ማስፈራሪያ እየተሰጠ ምርጫው ከምንም ተፅዕኖ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ዴሞክራሲያዊ ነው ለማለት አስቸጋሪና አዳጋች ያደርገዋል” ብለዋል።

“ነገር ግን ደግሞ ሁሉንም ነገር ጨለማ አድርጎ ማቅረብ በእኛ በኩል ትክክል አይደለም። ብዙ ቦታዎች ላይ አማራ ክልልም ምርጫ ማድረግ ይቻላል” ሲሉም አክለዋል። “አሁን ባለው የጸጥታ ችግርና የዓለም ሁኔታ አማራጭ መንግሥት ለመመሥረት ምርጫ እንጂ ሌላ መንገድ የለም” ያሉት እዮብ “አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት የሽግግር መንግሥት በሚል መንግሥት ሁሉን ነገር አሳልፎ ይሰጠኛል የሚል ተላላ ምክንያት ካላመጣን በቀር መንግሥት ሊመሠረት የሚችለው በምርጫ ብቻ ነው” ሲሉም አስምረውበታል።

በፓርቲው ውስጥ ስለተካሄደው የአመራር ለውጥ በተመለከተ እዮብ “ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እና ሀገር ያስፈልገናል ብለን ካሰብን ዴሞክራሲን በፓርቲ ውስጥ መለማመድና ማሳየት አለብን” ብለዋል።

ፓርቲው የመሪውን የአመራርነት ጊዜ በ10 ዓመት ቢገድብም የቀድሞው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በ7 ዓመት የተሰናበቱበትን ምክንያት ሲገልጹም “ሦስት ቀሪ ዓመት” የነበራቸው ቢሆንም በውስጥ አመራሩ ተስማምቶበት “ወደ ምርጫ እንደሚገባ ፓርቲ ምርጫውን ተከተሎ አዲስ አመራር ቢመጣ የተሻለ ይሆናል ብለን በማመን እንዲሁም ከዚህ በኋላ የሚመጡት መሪዎች ከሀገራዊ ምርጫው ጋር ተያይዞ በየ5 ዓመቱ እንዲመረጡ ለማድረግ በማሰብ” የተደረገ እንደሆነ አብራርተዋል።

በአዲሱ አመራር “በኢዜማ መርህና ፕሮግራም ላይ የተቀመጡ መሠረታውያን የምንላቸው በተለይ የዜግነት ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ እና ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም ባሉበት የሚቀጥሉ ይሆናል” ሲሉም እዮብ አክለዋል።

በተጨማሪ እዮብ “አዲስ አመራር እንደመምጣቱ የምንለውጣቸው ነገሮች ይኖራሉ” ያሉ ሲሆን በተለይ “በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ፓርቲውን ጠንካራ፣ ተፎካካሪ እና ተገዳዳሪ ፓርቲ አድርጎ መሥራት ላይ ትኩረት የምናደርግ ይሆናል” ብለዋል። ይህንንም የፓርቲው “የመሪ ክንፍ ከሊቀ መንበር ክንፉ ጋር በመናበብ ኢዜማን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም እና ቀጣይነት ያለው ትውልድ ተሻጋሪ ፓርቲ መሆኑን ማሳየት ትኩረት የምናደርግበት ጉዳይ ነው” ሲሉም አክለዋል። [ምርጫ 2018 – በኢትዮጵያ ኢንሳይደር]