በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ ለሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ 56 የፖለቲካ ፓርቲዎች በዲጂታል መንገድ ዕጩዎቻቸውን በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ። ከፓርቲዎቹ መካከል 15ቱ በጥምረት እና በግንባር የተደራጁ መሆናቸውንም አስታውቋል።
ቦርዱ ይሄን ያስታወቀው፤ መጪውን ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል የጸጥታ ሁኔታን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ጥር 25፤ 2018 ባዘጋጀው ውይይት ላይ ነው። በውይይቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ስለተደረገው እና ዕጩዎች በዲጂታል መንገድ ምዝገባ ስለሚያካሄዱበት አሰራር አጠር ያለ ገለጻ አድርገዋል።
“ዕጩዎች ድሮ ምርጫ ክልል ድረስ በመሄድ ሰነዳቸውን ይዘው ነበር ምርጫ ለመሳተፍ ምዝገባ የሚያደርጉት። አሁን ግን በቢሯቸው፣ በምቹ ስፍራቸው ሆነው ዕጩዎቻቸውን እንደሚዘግቡ ቦርዱ ይሄንን ሲስተም አበልጽጎ፣ አልምቶ፣ ስራ ላይ አውሎ ከጥር 1 ጀምሮ ፓርቲዎች እየተመዘገቡ ይገኛል” ብለዋል ሜላትወርቅ።
ምርጫ ቦርዱ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት በተናጠል የቀረቡ 41 የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ዕጩዎቻቸውን ለማስመዝገብ የሚረዷቸው እና ራሳቸው የቀጠሯቸው “አድሚኖች” አካውንት ተከፍቶላቸው ምዝገባ እያካሄዱ እንደሚገኙ ሰብሳቢዋ አስረድተዋል። በጥምረት እና በግንባር የተደራጁ 15 የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተመሳሳይ መልኩ ምዝገባ እያካሄዱ መሆኑንም አመልክተዋል። ( ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)




