የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት መጨረሻ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚወዳደሩ ዕጩዎች ምዝገባ የሚያከናወኑበትን ጊዜ እስከ የካቲት 16፤ 2018 አራዘመ። ቦርዱ የምዝገባ ጊዜውን ያራዘመው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋሙ ባዘጋጃቸው የተለያዩ መድረኮች ላይ እና በጽሁፍ ጭምር ባቀረቡት ጥያቄ መሆኑን አስታውቋል።
ምርጫ ቦርድ ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ይፋ ባደረገው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ፤ የዕጩዎች ምዝገባ የሚከናወነው ከጥር 1 እስከ የካቲት 1 ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነበር። በዚህ መሰረት ምዝገባው የሚጠናቀቀው ከነገ በስቲያ እሁድ ቢሆንም፤ ቦርዱ ዛሬ አርብ ጥር 29 ምሽት ባወጣው መግለጫ ለዕጩዎች የተሰጠው ጊዜ በሁለት ሳምንት መራዘሙን አመልክቷል።
ቦርዱ በዛሬው መግለጫው፤ ከዚህ ወር መጀመሪያ አንስቶ ሲካሄድ በቆየው የዕጩዎች ምዝገባ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል፤ 15 የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ በሁለት የተለያዩ ቅንጅቶች እና በአንድ ግንባር ስር ሆነው ተወዳዳሪዎችን ማስመዘገባቸውን ገልጿል። የግል ዕጩዎችም በተመሳሳይ መልኩ ምዝገባ እያከናወኑ መሆኑንም ጠቁሟል።
የዕጩዎቹ ምዝገባ ሲከናወን የቆየው፤ ቦርዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ባደረገው የዲጂታል ምዝገባ ስርዓት ነው። ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ይፋ የተደረገው ይህ ስርዓት “ለአካታችነት” እና “ተደራሽነት” ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ “የዕጩዎችን እና የመራጮችን ጊዜ እንደሚቆጥብ”፤ “አላስፈላጊ ምልልሶችን እንደሚያስቀር” እና “ወጪ ቆጣቢ” እንደሆነ ምርጫ ቦርዱ በወቅቱ አስታውቆ ነበር።
ሆኖም በዲጂታል ስርዓት ዕጩዎቻቸውን ለማስመዝገብ የሞከሩ ሰባት ፓርቲዎች፤ የዲጂታል ስርዓቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን “ከፉክክር ሜዳው በማውጣት ህዝብን አማራጭ አሳጥቶ ለመግዛት የታሰበ የፖለቲካ ሴራ ነው” ሲሉ በዚህ ወር አጋማሽ ባወጡት መግለጫ ነቅፈውታል። ፓርቲዎቹ በዚሁ መግለጫቸው፤ በዲጂታል ስርዓቱ ውስጥ የተቀመጡ ግዴታዎች ዕጩዎችን ለማስመዘገብ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የየፓርቲው የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ዕጩዎችን በሚመዘግቡበት ጊዜ “የኔትዎርክ ችግር” ደጋግሞ እያቋረጣቸው መሆኑን ተቃዋሚዎቹ በዚሁ መግለጫቸው አንስተው ነበር። በዲጂታል ስርዓቱ ለምዝገባው በተሰጠው አጭር ጊዜ ውስጥ የዕጩዎችን ዝርዝር ከፋይዳ መታወቂያቸው ጋር ለማስተሳሰር “እጅግ አዳጋች” መሆኑንም ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አክለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መግለጫ፤ ምርጫ ቦርድ የዕጩዎች ምዝገባ በይፋ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሂደቱ ላይ አጋጠመን ለሚሉት የቴክኒክ ችግሮች “አፋጣኝ መልስ” ለመስጠት ሲያደርግ የነበረውን “ጥረት” “ያላገናዘበ ነው” ሲል ተቋሙ ከቀናት በኋላ ምላሽ ሰጥቶ ነበር። ቦርድ በዛሬው መግለጫውም፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች ምዝገባ ለሚያካሂዱላቸው “የሲስተም አስተዳዳሪዎች” በሁለት ዙር ስልጠና መስጠቱን አስታውሷል።
የቦርዱ የአይ.ሲ.ቲ እና የፖለቲካ ፓርቲ ጉዳይ የስራ ክፍል ባለሙያዎች፤ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሲስተም አስተዳዳሪዎች እና በራሳቸው ምዝገባ ለሚያከናውኑ የግል ዕጩዎች “ሞያዊ እገዛ” እያደረጉ መሆኑንም ተቋሙ በዛሬው መግለጫው አስገንዝቧል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎችን በማስመዝገብ ሂደት “የተስተዋሉ” ችግሮችንም ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው ዘርዝሯል።
ከእነዚህ ውስጥ “የዕጩ መረጃዎችን በተደጋጋሚ መቀያየር” እና “ያልተሟላ መረጃ ማቅረብ” የሚሉት ይገኙበታል። በምርጫ ህጉ ላይ የተቀመጡትን የዕጩነት መስፈርቶች “ያለማሟላት” ችግርም በምዝገባ ሂደቱ ላይ መታየቱን ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ላይ አንስቷል። የዕጩዎች ምዝገባ አሁንም እየተከናወነ ቢሆንም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ የካቲት 1 በሚቆየው የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ዕጩዎቻቸውን አስመዝግበው ማጠናቀቅ እንደማይችሉ ማስታወቃቸውን ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ጠቅሷል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው “የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ” እስከ የካቲት 1 የሚቆየው የዕጩዎች ምዝገባ እንዲራዝምላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው ላይ አመልክቷል። ፓርቲዎቹ በይፋዊ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ በተቀመጠው መሰረት ዕጩዎቻቸውን አስመዝግበው ማጠናቀቅ እንደማይችሉ የገለጹት፤ ምርጫ ቦርድ ባዘጋጃቸው የተለያዩ መድረኮች እና በጽሁፍ ጭምር እንደሆነም አትቷል።
በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ እና የግል ዕጩዎች መመዝገብ ያልቻሉባቸውን ምክንያቶች “ከግምት ውስጥ በማስገባት”፤ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ገደቡን እስከ የካቲት 16፤ 2018 ማራዘሙን በመግለጫው ላይ አስታውቋል። በይፋዊ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳው መሰረት፤ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ ዕጩዎችን ዝርዝር ለህዝብ ይፋ ማድረግ የነበረበት ከመጪው ሳምንት ረቡዕ የካቲት 4 ጀምሮ ባሉት ዘጠኝ ቀናት ውስጥ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]




