የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ራስን በራስ ለመመዝገብ በተዘጋጀውና “ምርጫዬ” በተሰኘው የመራጮች ምዝገባ መተግበሪያ የሚመዘገቡ “የተወሰኑ መራጮች ቋሚ የመራጮች ቁጥር እንዳገኙ ምዝገባው የተጠናቀቀ አድርገው በመውሰድ ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ” አለመውሰዳቸውን አሳወቀ።
ዛሬ የካቲት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ቦርዱ ባወጣው መግለጫ “አብዛኛው “ምርጫዬ” መተግበሪያን በመጠቀም ራስን በራስ በመመዝገብ ሂደት ቋሚ የመራጭነት ቁጥር ያገኙ መራጮች፤ የምዝገባውን ሂደት በመቀጠል” እንዲሁም በሲስተሙ አማካኝነት “ምርጫ ጣቢያቸውን መርጠው ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚያገለግለውን ካርድ” እንዳገኙ ገልጿል።
ሆኖም “የተወሰኑ መራጮች ግን ቋሚ የመራጮች ቁጥር እንዳገኙ ምዝገባው የተጠናቀቀ አድርገው በመውሰድ ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ ከሲስተሙ ላይ አለመውሰዳቸውን ለመረዳት ተችሏል” ሲል ቦርዱ በመግለጫው አሳውቋል።

እንደቦርዱ ገለጻ መራጮች ራስን በራስ በመመዝገብ ሂደት ቋሚ የመራጭነት ቁጥር አገኙ ማለት ምዝገባውን አጠናቀዋል ማለት አይደለም። “ቋሚ የመራጭ መለያ ቁጥር ያገኛቹ መራጮች በሲስተሙ በመግባትና ሂደቱን በመቀጠል ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመምረጥ የሚያስፈልገዎን የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ ቦርዱ ያሳውቃል” ሲል አክሏል። ቦርዱ የመራጭ መለያ ቁጥር “ለየትኛውም ዓይነት ምርጫ የሚያገለግል ቋሚ የመራጭ መለያ ቁጥር” እንደሆነ ገልጾ ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ “ለመምረጥ” የሚያስፈልገው “የመራጭነት ካርድ” እንደሆነ አብራርቱል።
ሆኖም ምዝገባውን ለማጠናቀቅ የሞከሩ መራጮች ምዝገባው በሂደት ላይ እንደሆነና “እስኪጸድቅ 48 ሰዓታት ሊውስድ ስለሚችል እባክዎ ይጠብቁ” የሚል መልዕክት በመተግበሪያው አማካኝነት እንደሚደርሳቸው የ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ታዝባለች።

ቦርዱ በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ ራስን በራስ ለመመዝገብ የሚውለውን “የብሔራዊ መታወቂያቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪ በሚል ያወጡ ዜጎች ቁጥር ተገማች ከሆነው የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር አንጻር ከፍ ያለ ሆኖ በመገኘቱ፤ ቦርዱ መራጮች ለመመዝገብ የሚያቀረቡት ሠነድ ላይ ተጨማሪ ማጣራት አድርጎ” የመራጭነት ካርዱን ለመራጮች እንደሚለክ ገልጿል።
በትላንትናው ዕለት የተጀመረው የዲጂታል መራጮች ምዝገባ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ መስተዳደሮች እንዲሁም ሐረሪ ክልል ክልል ሙለ ለሙሉ የሚተገበር ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች በተመረጡ ጣቢያዎች ላይ ብቻ የሚከናወን መሆኑን ቦርዱ አሳውቁል። በዲጂታል ምዝገባ በማይካሄድባቸው ሌሎች ጣቢያዎች ሁሉ፣ የመራጮች ምዝገባ እንደተለመደው በመዝገብ (በማኑዋል) የሚቀጥል ይሆናል። [ምርጫ 2018 – በኢትዮጵያ ኢንሳይደር]





