በ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለመወዳደር መጀመሪያ ላይ ከተመዘገቡት 48 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ስድስቱ ከፉክክሩ ውጪ መደረጋቸውንና በዚህም ሳቢያ በዘንድሮው ውድድር ላይ የሚሳተፉት 42 ፓርቲዎች ብቻ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል።
ሁለት ጥምረቶችን እና አንድ ግንባርን ጨምሮ 48ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀደም ሲል የዕጩዎች ምዝገባ አከናውነውና የምርጫ ምልክቶቻቸውን መርጠው የነበረ ቢሆንም፣ በፓርቲዎቹ ውስጣዊ ችግሮች እና በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ሳቢያ የስድስቱ ተሳትፎ ሊሰረዝ ችሏል።
ቦርዱ የመራጮች የድምፅ መስጫ ወረቀት በውጭ አገር አሳትሞ ማጠናቀቁን ተከትሎ፣ ምርጫው በእነዚህ 42 ፓርቲዎች መካከል ብቻ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል።
ከምርጫው ውጪ ከሆኑት መካከል መሠረታቸውን በትግራይ ክልል ያደረጉ ሦስት ፓርቲዎች ይገኙበታል። የዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት)፣ የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ እና የትንሳኤ ሥርዓት ቃንጪ ኃቂ ፓርቲዎች በትግራይ ክልል ዘንድሮ ምርጫ የማይካሄድ በመሆኑ ከውድድሩ ወጥተዋል።
ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ እና ትንሳኤ ሥርዓት ቃንጪ ኃቂ በምርጫው ለመወዳደር ዕጩዎቻቸውን አስመዝግበው የነበረ ቢሆንም፣ የክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ እንዳይወዳደሩ እንዳደረጋቸው ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” መግለጻቸው ይታወሳል።
ትንሳኤ ሥርዓት ቃንጪ ኃቂ ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6፣ እንዲሁም ለክልል ምክር ቤት 10 በጥቅሉ 16 ዕጩዎችን አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ ስምረት ፓርቲ በበኩሉ በኤርትራ ቁጥጥር ሥር ከሆኑት አካባቢዎች ውጪ በመላው ትግራይ ዕጩዎችን ማቅረቡን ገልጾ የነበረ ቢሆንም ከምርጫው ውጪ ሆኗል።
ምርጫ ቦርድ ሚያዚያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በትግራይ ክልል ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ምንም ዓይነት ሥራ አለመጀመሩን ቢያሳውቅም፣ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ “ትግራይ በፌደራልም፣ በክልል ደረጃም መወከል አለባት። አሁንም ቦርዱ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል” ማለታቸውና አስቻይ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ሂደቱ እንደሚቀጥል መግለጻቸው ይታወሳል።
ከመሠረታዊ የጸጥታ ችግሮች በተጨማሪ፣ የውስጥ አመራር ክፍፍል እና አስተዳደራዊ ሕጎች ያልተከተሉ ሦስት ፓርቲዎች ከምርጫ ውድድሩ አስወጥተዋቸዋል።
በፓርቲው አመራሮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት በተቀሰቀሰ የፍርድ ቤት ክርክር 309 የሚሆኑ ዕጩዎቹ የታገዱበት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) አንደኛው ነው። የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመጋቢት ወር 2018 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ በሁለቱም ወገኖች የቀረቡት ዕጩዎች የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ያልተከተሉ በመሆናቸው ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ አዲስ ዕጩ ባለመቅረቡ ፓርቲው ከምርጫው ውጪ መደረጉን በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ንዋይ የተፈረመው ደብዳቤ ያመላክታል።
ሌላኛው ተሰራዥ ፓርቲ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) ሲሆን፣ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ ከ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መውጣቱን የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ ኡማን ኒኬሎ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ዋና ጸሐፊው ፓርቲው ለምርጫው 141 ዕጩዎች አዘጋጅቶ 121ዱን በዲጂታል ሲስተም አስመዝግቦ የነበረ ቢሆንም፣ ዕጩዎቹ እንዳልተካተቱ ጠቅሷል። ጋሕነን በፍርድ ቤት ለመጠየቅ ከቦርዱ የተሰጠ ደብዳቤ ባለመኖሩ የተሰረዙበት ምክንያት ግልጽ እንዳልሆነላቸው ዋና ጸሐፊው አመልክተዋል።
በመጨረሻም የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ (ሲፈፓ) በበጀት ኦዲት ክርክር ምክንያት ከውድድሩ ውጪ ሆኗል። ምርጫ ቦርድ ሚያዚያ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ ፓርቲው የኦዲት ሪፖርት ሳይቀርብና ሳይረጋገጥ የዕጩዎች ምዝገባ ማከናወን የማይችል በመሆኑ በ2016 ዓ.ም. የወሰደው የመንግሥት በጀት ኦዲት ተደርጎ እንዲቀርብ ጠይቆ ነበር።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር የምርመራ ሥራውን አከናውኖ ውጤቱን መጋቢት 25 ቀን ለቦርዱ ያሳወቀ ቢሆንም፣ ቦርዱ በአሁኑ ሰዓት የድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመት ሙሉ በሙሉ በመጠናቀቁ የፓርቲውን የዕጩዎች ምዝገባ ጥያቄ ማስተናገድ እንደማይችል ማሳወቁን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማረጋገጥ ችላለች። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




