ከ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ዕጩዎችን የማስመዘገቡ ሂደት በዲጂታል መከናወኑ እና ለመመዝገብ የብሔራዊ መታወቂያ እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡ፣ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሊያስመዘግቡ ካቀዱት የዕጩዎች ቁጥር ያነሰ ለማስመዝገብ እንዳስገደዳቸው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ፓርቲያቸው አባል ሆኖ የሚወዳደርበት ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት “ዕጩዎችን በማስመዝገብ ሂደት ውስጥ ትብብሩ የገጠመው ችግር የብሔራዊ መታወቂያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዕጩዎቻችን የቀበሌ መታወቂያ እንዳያድሱ” መደረጋቸውም ጭምር ነው ብለዋል።
በተለይም በርካታ ዕጩዎችን እንዳስመዘገቡ በገለጹት የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ይህ ዓይነቱ ችግር ትብብሩን በስፋት እንደገጠመው ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። “በዚህም ምክንያት ኢሉ አባቦራ እና ደንቢ ዶሎን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች 70 ዕጩዎቻችንን ሳናስመዘግብ ቀርተናል” ቅሬታቸውን አስረድተዋል።

መጋቢ ብሉይ አብርሃም፣ ትብብሩ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በድምሩ 1,700 ዕጩዎችን ለማስመዝገብ አቅዶ አሁን ላይ በተጨባጭ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡት 1,223 መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ በማስገባታቸው አሁንም በምዝገባ ሂደት ላይ ያሉ 177 ዕጩዎች መኖራቸውን እና፣ ይሄም ቁጥሩን ወደ 1,400 ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሔርም በተመሳሳይ “አባሎቻችን የብሔራዊ መታወቂያ ባለማውጣታቸው ምክንያት ዕጩዎችን ለማስመዘግብ ተቸግረናል” ብለዋል። በዚህም ምክንያት የዕጩዎቹ ቁጥር ከ1,100 ወደ 167 ማሸቆልቆሉን የፓርቲው ሰብሳቢ አስታውቀዋል። “የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለችግሩ መፍትሄ እንዲሰጠን ደጋግመን ብንጠይቅም ለማስተካከል ፍቃደኛ አልሆነም፤” ካሉ በኋላ አክለውም፣ “ዞሮ ዞሮ እየሞከርን ነው” ሲሉ ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ኢብአፓ በተለይ በአፋር ክልል 200 ዕጩዎችን ለማስመዝገብ አቅዶ ቢያቀርብም፣ የምዘገባ ሂደቱን ያለፉት ግን 4 ብቻ መሆናቸውን ሰብሳቢው አቶ ዘሪሁን አስረድተዋል። ይህም የሆነው የፓርቲው አባላት የብሔራዊ መታወቂያ ባለማውጣታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ሌላኛው “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ሊቀ መንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደምም በበኩላቸው፣ “በብሔራዊ መታዋቂያ ምክንያት 250 የሚሆኑ ዕጩዎቻችን ሳይመዘገቡ ቀርተዋል” ብለዋል።
ነእፓ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 1,500 ዕጩዎችን ለማስመዝገብ አቅዶ አባሎቹ የብሔራዊ መታወቂያ ባለመያዛቸው እና ቤሌሎችም ባልጠቀሳቸው ምክንያቶች የዕጩዎች ቁጥር ወደ 884 ዝቅ እንዳለበት አስታውቋል። ሊቀ መንበሩ እንደተናገሩት “መጀመሪያ የምርጫው ሂደት በዲጂታል መንገድ እንደሚከናወን ብንረዳም፣ ለመመዝገብ ግን የብሔራዊ መታወቂያ ግድ መሆኑን አላወቅንም ነበር” ሲሉ ሂደቱን ተችተዋል። በዚህም ሳቢያ ነእፓ የዲጂታል ምዝገባ ስርዓቱ በፈጠረው ክፍተት ምክንያት ለማስመዝገብ ያቀደውን የዕጩዎች ቁጥር ማሳካት እንዳልቻለ ዶ/ር አብዱልቃድር አመልክተዋል።

“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከብሔራዊ መታወቂያና ከምዝገባ ሂደት ጋር ተያይዞ የትብብር ለኢትዮጵያ፣ ነእፓ እና ኢብአፓ አመራሮች ላቀረቡት ቅሬታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ምላሽ ለማካተት ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም አልተሳካም። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]




