ስምረት እና ቃንጪ ሃቃ ፓርቲዎች በትግራይ ክልል የምርጫ እንቅስቃሴ አለመጀመሩ እንዳሳሰባቸው ገለጹ

ዴሞከራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) እና የትንሳኤ ስርዓት ቃንጪ ሃቂ (ቃንጪ ሃቂ) ፓርቲዎች የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ወቅታዊ እንቅስቃሴ እና በክልሉ የምርጫ ዝግጅት አለመጀመር እንዳሳሰባቸው ለ”ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ቃንጪ ሃቂ ህወሓት ከጦርነቱ በፊት የነበረው ምክር ቤት ወደ ሥራ እንዲመለስ ያሳለፈውን ውሳኔ “ከጦርነት አዋጅ ያልተናነሰ ተግባር ነው” ሲለው፣ ስምረት በበኩሉ “የጊዚያዊ አስተዳደሩ የሥልጣን ዘመን መራዘም በክልሉ ምርጫ እንደማይካሄድ ማሳያ ነው” ብሏል።

የስምረት ጽሕፈት ቤት የሚዲያና ኮምኒኬሽን ተወካይ አቶ ሓለፎም ነርአ፣ “የግዚያዊ አስተዳደሩ [ሥልጣን] ለአንድ ዓመት የመራዘሙ ዓላማ በምርጫው እኔ [ህወሓት] ከሌለሁበት በክልሉ አይከናወንም እያለ በመሆኑ፣ ትግራይ መንግሥት የሌለበት ክልል መሆን ስሌለበት የተደረገ ውሳኔ ነው” ብለዋል። ይሁንና ህወሓት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሠ ወረደ የሥልጣን ጊዜ በአንድ ዓመት መራዘሙን መቃወሙ ይታወሳል።

አቶ ሓለፎም ግን “በጄነራል ታደሠ ወረደ የሚመራውን ጊዚያዊ አስተዳደርም ቢሆን በህወሓት ፍላጎት የተመረጠ ነው” ይላሉ። በሌላ በኩል፣ “ውሳኔውን የማይቀበሉ ከሆነ፣ በደብዳቤ ‘አንቀበልም’ ይባላል እንጂ፣ በ2012 የነበረውን መንግሥት ወደ ነበረበት እንመልሳለን የሚሉት በየትኛው የሕግ አግባብ ነው?” ሲሉም ጠይቀዋል።

የቃንጪ ሃቂ ሊቀመንበር ደጋፊ ጉደፋይ በበኩላቸው “በህወሓት የተወሰነው ውሳኔ “ከጦርነት አዋጅ ያልተናነሰ ተግባር ነው” ሲሉ ኮንነውታል።

ህወሓት በትግራይ ክልል ከስድስት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ የተመረጠው የክልሉ ምክር ቤት “ወደ ስራ እንዲመለስ” ሲል ውሳኔ ባሳለፈበት ወቅት፣ የትግራይ መንግሥት አስፈጻሚ አካል “ሁሉንም አቅሞች ያካተተ” እና “አቃፊ” ሆኖ እንዲቋቋም ወስኛለሁ ማለቱም ይታወሳል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕውቅናው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የተሰረዘው ህወሓት፣ ውሳኔዎቹን ያስተላለፈው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ  አደግረኩት ባለው መደበኛ ስብሰባው ነው።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከጦርነቱ በፊት የነበረውን እና በ2012 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ውጤት ዕውቅና አይሰጥም። ይልቁንም አዲስ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ክልሉን የሚመራ “አካታች ጊዚያዊ አስተዳደር” እንዲቋቋም ይደነግጋል።

የጊዚያዊ አስተዳደሩ ሁለተኛ ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሠ ወረደም የህወሓትን ውሳኔ “የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚያፈርስ ነው” በማለት ተቃውመውታል።

አቶ ሓለፎም ነርአ፣ ውሳኔውን “የህወሓት ሰዎች በክልሉ ጦርነት እንዲጀመር ከሚያደርጉት ፍላጎታቸው አንፃር የተወሰነ ውሳኔ ነው” ያሉ ሲሆን፣ እንደ ማሳያም “የወጣቶች አፈሳ በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል፤ አልሄድም ያለውን ወጣት ደግሞ በጥይት ጭምር እየመቱት ይገኛሉ” በማለት ክስ ሰንዝረዋል።

“በክልሉ የሰላማዊ ፖለቲካ በሮች እየተዘጉ ነው” ያሉት አቶ ሓለፎም፣ “የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት አቃፊ መንግሥት ይቋቋም የሚል ነው፤ ነገር ግን የክልሉ መንግሥት ከ99 በመቶ በላይ በሚሆኑ የህወሓት ሰዎች ተሞልቷል” ብለዋል። በተጨማሪም፣ የስምረት ፓርቲ ከግማሽ በላይ ከፍተኛ አመራሮች የቀድሞ የህወሓት የምክር ቤት አባላት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ “የቀድሞ አስተዳደር ይመለስ ማለት”፣ እነሱም “አብረው ይመለሱ እንደማለት ነው” ካሉ በኋላ፣ “ይህ እንዲሆን ደግሞ አይፈቅዱም” ብለዋል።

ስምረት ሚያዚያ 13 ቀን 2018 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም በሀገር ውስጥ እና በውጭም ያሉ ሁሉንም አካላት ያሳተፈ አካታች ጊዚያዊ አስተዳር መቋቋም እንዳለበት ገልጿል።

ምርጫ ቦርድ ህወሓት በልዩ ሁኔታ ዳግም ከተመዘገበ በኋላ፣ በስድስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ እና አዳዲስ አመራሮችን እንዲመርጥ ጠይቆት ነበር። ነገር ግን ህወሓት በምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ማግኘት የቻለ ጉባዔ ሳያደርግ በመቅረቱ ግንቦት 5 ቀን 2017 ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ምዝገባውን በይፋ ሰርዞታል።

ሚያዚያ 15 ቀን 2018 ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ቦርዱ ከህወሓት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ገልጸዋል። በተጨማሪም በትግራይ ክልል ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ምንም ዓይነት ሥራ አለመጀመሩን ገልጸዋል። ሰብሳቢዋ፣ “ትግራይ በፌደራልም፣ በክልል ደረጃም መወከል አለበት። አሁንም ቦርዱ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል። አስቻይ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ሲሄዱ ደግሞ የምርጫ ሂደቱ ይቀጥላል” ብለዋል።

የትንሳኤ ስርዓት ቃንጪ ሃቂ ፕሬዝዳንት አቶ ደጋፊ ጉደፋይ በበኩላቸው “ፓርቲያችን ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዕጩዎች ያስመዘገበ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ክልል ከምርጫው አስቀድሞ ሁሉን ያካተተ የሽግግር መንግሥት ይመስረት የሚል አቋም አለን” በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል።

“አሁንም ከምርጫ ራሳችንን አላገለልንም” ያሉት አቶ ደጋፊ፣ ምርጫ ቦርድም ይሁን መንግሥት በግልጽ በክልሉ ‘ምርጫ አይደረግም’ ባይሉም ሁኔታዎቹ ምርጫ ለማከናወን አስቻይ አለመሆናቸውን መመልከት [ግን] ይቻላል” የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል።

ቃንጪ ሃቂ ፓርቲ 16 ዕጩዎችን እንዳቀረበ ገልጾ፣ እነዚህም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6፣ እንዲሁም ለክልል ምክር ቤት 10 ዕጩዎች ማስመዝገቡን ገልጿል። ስምረት ፓርቲ በበኩሉ በመላው ትግራይ ዕጩዎችን ማቅረቡን አቶ ሓለፎም የገለጹ ሲሆን፣ “ያላቀረብነው የኤርትራ ሠራዊት በሚቆጣጠራቸው የትግራይ ግዛቶች ብቻ ነው” በማለት ለ“ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።