አቶ ዳውድ ኢብሳ በ “ፀጥታ ስጋት” ምክንያት በዘንድሮው ምርጫ እንደማይወዳደሩ ኦነግ አስታወቀ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ፕሬዝዳንት አቶ ዳውድ ኢብሳ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ በዕጩነት እንደማይወዳደሩ ድርጅቱ ገለጸ።

የኦነግ የዲሲፒሊን እና ቁጥጥር ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ ዲሮ ለ “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፣ አቶ ዳውድ የሚወዳደሩበት ሆሮ ጉድሩ አካባቢ ያለው የፀጥታ ስጋት ለውሳኔው ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። ይሁን እንጂ በፕሬዝዳንቱ የምርጫ ክልል ሌሎች ብቁ ዕጩዎችን በማግኘት የመተካት ሥራ መከናወኑን ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል።

ኦነግ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት “ከፖለቲካው ተገፍቻለሁ” በሚል እና አባላቱ ታስረውበት እንደነበር በመጥቀስ ሳይሳተፍ መቅረቱ ይታወሳል። ዘንድሮ ወደ ምርጫው የተመለሰው ግን የፖለቲካ ምኅዳሩ ስለተሻሻለ ሳይሆን፣ ቢያንስ በአዲስ አበባ የነበረውን አንድ ቢሮ መክፈት በመቻሉ እና ከምርጫ ቦርድ ጋር ለመገናኘት “ጠባብ መንገድ” ስለተፈጠረለት መሆኑን አቶ አለማየሁ ገልጸዋል።

እንደ ሊቀ መንበሩ ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት የሌለው ሲሆን፣ ሌሎች የተወሰኑ አመራሮችም “በግል ምክንያት” በዕጩነት አልቀረቡም።

ኦነግ 230 ቢሮዎቹ ተዘግተውበት በአሁኑ ወቅት ክፍት የሆነው የአዲስ አበባው ቢሮ ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ አለማየሁ፣ ይህም ብዙ ዕጩዎችን ለማቅረብ እንቅፋት እንደሆነባቸው አስረድተዋል።

በዚህም ለ7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ 128 ዕጩዎችን ብቻ ያቀረበ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ግማሽ ያህሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ 50 የሚሆኑት ለኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በአማራ ክልል – ከሚሴ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ እና ሐረሪ ክልል የሚወዳደሩ ናቸው።

በድርጅቱ አመራሮች መካከል ተፈጥሮ ስለነበረው አለመግባባት ማብራሪያ የሰጡት አቶ አለማየሁ፣ “ፓርቲያችን ውስጥ የተፈጠረ ውስጣዊ ችግር አልነበረም። ይልቁንም የተወሰኑ አባላት ከመንግሥት ጋር ተነጋግረው የራሳቸውን መንገድ ተከትለዋል” በማለት የመከፋፈሉን ዜና አስተባብለዋል። እነዚህ ወገኖች “ኦነግ የእኛ ነው” በሚል ከምርጫ ቦርድ ጋር ሲካሰሱ መቆየታቸው “ውዥንብር ፈጥሮ ነበር” ም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ጦርነት እየተካሄደ ተቀባይነት ያለው ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል የገለጹት አቶ አለማየሁ፣ “ለኦነግ መንቀሳቀስ ችግር የሆነው እራሱ መንግሥት፣ በተለይም የታችኛው የሥልጣን እርከን ኦነግን በሌላ ዓይን በማየቱ ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።

በዚህም ምክንያት የምርጫ ቅስቀሳቸው “በሚዲያ ብቻ የተገደበ” መሆኑንና ይህም በሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ሆኖም ኦነግ “ችግሮች ቢኖሩም ከምርጫው የመውጣት ፍላጎት” የለውም በማለት የድርጅቱን የፖለቲካ ዓላማ እና አራት (የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበረሰብ እና የደኅነነት) ምሰሶዎች ያሉት ማኒፌስቶውን ለሕዝብ ለማስተዋወቅ እንደሚጠቀምበት አስታውቀዋል።

ኦነግ በ1960ዎቹ አጋማሽ የተመሠረተ፣ የኦሮሞ ሕዝብን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መብቶች ለማስከበርና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ለማረጋገጥ የቆመ ድርጅት ስለመሆኑ ይናገራል።

ድርጅቱ በግማሽ ምዕተ ዓመት ዕድሜው ደርግን ለመጣል በትጥቅ ትግል ከታገሉ ድርጅቶች አንዱ ሲሆን፣ በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ከኢሕአዴግ ቀጥሎ ትልቅ ውክልና ያገኘ ፓርቲም ለመሆን በቅቶ ነበር። ይሁንና ከኢሕአዴግ ጋር በነበረው አለመግባባት ሳቢያ በመጀመሪያው ምርጫ ሳይሳተፍ በመውጣት የትጥቅ ትግሉን ለመቀጠል እንደተገደደ ይናገራል።

ኦነግ ምንም እንኳን የአገር ወይም የክልል መሪነት ዕድል ባያገኝም፣ የኦሮሞ ፖለቲካን በመቅረፅ ረገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ የፖለቲካ ፓርቲ ነው። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]